1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ማን ናቸው?

ዓርብ፣ ነሐሴ 18 2010

አቶ ሙስጠፋ ሙሐሙድ ዑመር በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የሶማሌ ክልል ጊዜያዊ መሪ ሆነው ተመርጠዋል። አቶ ሙስጠፋ በክልሉ በስልጣን ላይ ያለዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አባል ባይሆኑም በጊዜያዊነት ላለፉት ሁለት ሳምንታት በሥልጣን የቆዩትን አሕመድ አብዲ መሐመድን ተክተው ለመጪዎቹ ሁለት አመታት ክልሉን ይመራሉ። 

https://p.dw.com/p/33d89
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

Who is Mustafa Omer?MMT - MP3-Stereo

በርዕሰ-መሥተዳድርነት እንዲያገለግሉ መመረጣቸው እስከተሰማ ድረስ ከነ ቤተሰቦቻቸው ኬንያ ይኖሩ የነበሩት አቶ ሙስጠፋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሶማሊያ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በመስራት ላይ ነበሩ።  ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ የሕጻናት አድን ድርጅትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል። 
አቶ ሙስጠፋ የተወለዱት ከጅጅጋ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው አዋሬ የተባለች አነስተኛ ከተማ በ1964 ዓ.ም. ነው። ትምህርታቸውን በደገሐቡር እና በሐረር የመድሐኒዓለም ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን በኤኮኖሚክስ አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚያው በኤኮኖሚክስ ከለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ በተልዕኮ ትምህርት አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም የሶማሌ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የዶክተር አብዱል መጂድ ሑሴን መምህራን ማሰልጠኛ ማዕከል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

ከኢትዮጵያ ለምን ወጡ? 

አቶ ሙስጠፋ በቅርቡ ከሥልጣናቸው የተነሱት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር የክልሉን የርዕሰ-መሥተዳድርነት ሥልጣን ሲቆጣጠሩ ነው የሶማሌ ክልልን የለቀቁት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ ተማሪ ሳሉ የአቶ ሙስጠፋ ጓደኛ የነበሩት አቶ ዚያድ አሕመድ የቀድሞው ርዕሰ መሥተዳድር አብዲ መሐመድ ዑመር "ያደርሱባቸው የነበረውን ችግር ሸሽተው" ከነ ቤተሰቦቻቸው ኬንያ ለመግባት መገደዳቸውን ያስታውሳሉ። 
ከሁለት አመታት በፊት አቶ ሙስጠፋ በክልሉ መንግሥት ላይ የሚሰነዝሩትን ተቃውሞ እንዲያቆሙ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ አሻፈረኝ በማለታቸው የምኅንድስና ባለሙያ ወንድማቸው ፋይሰል ኦማር በልዩ ፖሊስ ከደገሐቡር ከተማ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ መገደላቸው ይነገራል። አቶ ዚያድም "ውጪ ያሉት አራማጆች በአብዲ ኢሌ ላይ ወይም በነበረው አገዛዝ ላይ ተቃውሞ ካሰሙ ወይም አንድ ነገር ካደረጉ ቤተሰቦቻቸው ይታሰራሉ ወይም ይገረፋሉ። አቶ ሙስጠፋም ወንድማቸውን ያጡት በዚህ አጋጣሚ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

አቶ ዚያድ የድሮ ጓደኛቸው የሶማሌ ክልልን ለመምራት ይመረጣሉ የሚል ቅድሚያ ግምት አልነበራቸውም። "አልጠበቅኩም። እሱ የውጪ ሰው ነው። የፓርቲ አባልም አልነበረም" ይላሉ። አቶ ሙስጠፋ ከዚህ ቀደም ክልሉን ይመሩ የነበሩት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁ የለውጥ አቀንቃኝ ነበሩ። በክልሉ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጋልጡ የቀድሞውን አስተዳደር የሚሞግቱ ጽሁፎች በሶማሊኛ፣ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ሲፅፉ ቆይተዋል። በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይም የጎላ ተሳትፎ ነበራቸው። 
የሶማሌ ክልል ፖለቲካን በቅርብ የሚከታተሉት አቶ ዚያድ ተመራጩ ፕሬዝዳንት በርካታ እና ውስብስብ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው አልዘነጉም። "የሕግ የበላይነት፣ ሰላም እና መረጋጋት መምጣት አለበት። ሥራ አስፈፃሚው፣ ሕግ አውጪው እና ሕግ ተርጓሚው ሪፎርም ይፈልጋል" ይላሉ አቶ ዚያድ። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ