1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመናዊቷ የመርከብ ካፕቴን እሥር

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2011

ራኬተ ያለፍቃድ የኢጣልያን የባህር ክልል በመጣስ በኢዲሱ የኢጣልያ ህግ ጠንከር ያለ ቅጣት ሊጠብቃት ይችላል።ቅጣቱ ለሲዎችም መትረፉ አይቀርም።የራኬተ መታሰር ብዙ ስደተኞች በሜዴትራንያን ባህር ላይ ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑ አይቀርም ይላል ሲዋች።የርስዋ መታሰር ሌሎች ካፕቴኖችን ስጋት ውስጥ መክተቱ አይቀርምና።

https://p.dw.com/p/3LTfL
Italien Kapitänin Carola Rackete
ምስል Reuters/G. Mangiapane

የጀርመናዊቷ የመርከብ ካፕቴን እሥር


የ31 ዓመት ጀርመናዊት ወጣት ናት።ስደተኞችን፣በተለይም በባህር ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩትን በጉዞ ላይ ከሚያጋጥማቸው የመስጠም አደጋ ትታደጋለች።SEA WATCH የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መርከብ ሾፌር፣ ካፒቴን ካሮላ ራኬተ።ራኬተ በኢጣልያ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋለች ዛሬ 4 ቀን ሆናት።እርስዋ የምትቀዝፈው የSEA WATCH መርከብ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ከመስጠም አደጋ በማዳን የሚታወቅ የኔዘርላንድስ መርከብ ነው።መርከቡ ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት በለንቋሳ ጀልባ ከሊቢያ የባህር ጠረፍ የተነሱ 53 ስደተኞችን ከመስጠም ታድጎ ወደ ኢጣልያ ሊወስዳቸው ሞክሮ ነበር።ይሁን እና የኢጣልያ ባለሥልጣናት ከመካከላቸው የጤና እክል ያለባቸው 13ቱ ስደተኞች ብቻ ወደ ኢጣልያ እንዲገቡ ፈቅደው ሌሎቹ ግን የሚቀበላቸው ሀገር እስኪገኝ ድረስ እንዳይገቡ ይከለክላሉ።አርብ እለት ፊንላንድ፣ፈረንሳይ፣ጀርመን ሉክስምበርግ እና ፖርቱጋል ስደተኞቹን ለመከፋፈል ቃል ቢገቡም ኢጣልያ ስደተኞቹን አላስገባችም።ከሁለት ሳምንት በላይ በባህር ላይ ለመቆየት የተገደዱትን የ40 ስደተኞች ስቃይ እና እንግልትን መቋቋም የተሳናት የመርከብዋ ካፕቴን ራኬተ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ለእስር ያበቃት ውሳኔ ላይ ትደርሳለች።መርከቦች እንዳያልፉ ለመከልከል የቆመውን የኢጣልያ የጉምሩክ ፖሊስ ጀልባ ጥሳ ስደተኞቹን የጫነችውን መርከብ ወደ ላምፔዱዛ ወደብ ወሰደች።ስደተኞቹም ኢጣልያ መግባት ቻሉ።ይህ የራኬተ እርምጃ በኢጣልያ መንግሥት «ወንጀል» ሲባል በሌላው አውሮጳ ደግሞ በሰብዓዊነት ተወድሶ ጀግና የሚል ስም አትርፎላታል።ራኬተን ጀግና ከሚሉት መካከል የኢጣልያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርን ወደቦችን የመዝጋት ፖሊሲ የሚቃወሙት ግራ ክንፍ ኢጣልያውያንም ይገኙበታል።ድርጊቱን የጦርነት ምግባር ያለው የኢጣልያ መንግሥት ራኬተን ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ስር አውሏታል።የታሰረችው መርከቦች እንዳያልፉ ለመከላከል የቆመ ወታደራዊ መርከብን ጥሶ በማለፍ ነው።ራኬተ የኢጣልያን የባህር ኃይል ህግ በመጣስ  በሁለት የክስ ጭብጦች ተጠያቂ ተብላለች።የመጀመሪያው የወታደራዊ መርከብን ትዕዛዝ አለመቀበል ሁለተኛው ደግሞ ለባለሥልጣናቱን ትዕዛዝ እምቢተኛ መሆን ነው።ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ እንዲሻገሩ በማድረግ ክስም ምርመራ እየተካሄደባት ነው።ስደተኞችን የሚታደጉ መርከቦችን እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚቃወሙት የኢጣልያው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቲዮ ሳልቪኒ የራኬተን ድርጊት በእጅጉ ኮንነው የተፈጸመውም ወንጀል ነው ሲሉ ነበር የከሰሱት።
« ነጭ ሀብታም እና ጀርመናዊ ነኝ ፣ጊዜዬን እንዴት እንደማሳልፍ አላውቅም የምትለው ወጣቷ እመቤት ታስራለች።እና ምን አደረገች? ላምፔዱዛ የጉምሩክ ፖሊሶችን የያዘችውን ተቆጣጣሪ ጀልባ  በለሊት ለማስጠም ሞክራለች።የሚገርመው ህይወት እናድናለን እያሉ በሥራ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለሞት አደጋ ያጋልጣሉ።ይህን በግልጽ የሚያሳዩ ቪድዮዎች አሉ። ማንም ከአሁን በኋላ ሊያስመስል አይችልም።ማንም ሊዋሽም አይችልም።እነዚህ ወንጀለኞች ናቸው።»
ሌሎች አውሮጳውያን ግን ካሬተ ጀግና እንጂ ወንጀለኛ አይደለችም እያሉ ነው።የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሲዋች ቃል አቀባይ ጂዮርጂና ሊናርዲ እንደሚሉት ካሮላ ካሬተ ከተያዘች በኋላ ሳይቀር ለስደተኞቹ ነበር የምትጨነቀው።እርምጃውን የወሰደችውም ምርጫ በማጣቷ ነው።
«ካሮላ እነዚህን ሰዎች ወደ መሪት ለማምጣት መስዋዕትነት ከፍላለች።ስትታሰር ሰዎቹ ከመርከቡ ወርደዋል?እያለች ትጠይቅ ነበር።ይህን ብቻ ነበር ማወቅ የምትፈልገው ለራስዋ ባለመጨነቅዋ ብቻ አይደለም፤ስለስጋች ነው።ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ሌላ ምንም አማራጭ አልነበራትም ማድረግ ያለባትን ነው ያደረገችው።ሃላፊነቱንም ትወስዳለች።እስከ መጨረሻው እንግዛታለን።እኛ ለርስዋ ቅርብ ነን።ድርጊትዋንም እንረዳለን።» 
ባለፈው ቅዳሜ በኢጣልያ የፀጥታ ኃይሎች ከላምፔዱዛ የታሰረችው ራኬተ ከተያዘችበት ስፍራ ወደ አርጀንቲኖ ተወስዳ ለሦስት ሰዓታት ተጠይቃለች።ጠበቃዋ ሊዮናርዶ ማሪኖ እንዳሉት በወቅቱ ራኬተ ውሳኔዋን ተከላክላለች።በመርከቧ ላይ የነበሩት ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ እንደነበሩ እና የጉምሩክ ፖሊሱን ጀልባ ሳታየው ድንገት እንደነካችውም ማሪኖ ተናግረዋል። ጉዳይዋን የተመለከቱት የአርጀንቲኖ አቃቤ ህግ በሰጡት መግለጫ የካሬተን እርምጃ አላስፈላጊ ሆነ ተብሎ እና በፍላጎት የተፈጸመ ብለውታል። 
«የተወሰደው እርምጃ፣በተለይ የፖሊስ ጀልባን ከድንጋይ ጋር ማጋጨት በአሉታዊነት የሚታይ ነው።ይህ በእኛ እይታ ሆነ ተብሎ እየታወቀ የተፈጸመ ድርጊት ነው። አስፈላጊ ሆኖ የተወሰደ እርምጃ አይመስለንም።እርምጃውን ለመውሰድ የሚያደርስ ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ምክንያቱም መልህቁን ከወደቡ አቅራቢያ እንዲጥል የተደረገው ሲዋች የህክምና ድጋፍ አግኝቷል።አስፈላጊ ለሆኑት ማናቸውም እገዛዎች ከባህር ኃይሉ እና ከፖሊስ ባለሥልጣናት ያልተቋረጠ ግንኙነት ነበረው።» 
ራኬተ የኢጣልያን ህግ በመተላለፍ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተላለፈባት እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እሥራት እና 50ሺህ ዩሮ ያህል የገንዘብ ይጠብቃታል ተብሏል።የጀርመን መንግሥት ኢጣልያ ራኬተን እንድትለቅ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ሲያስተላልፍ ነበር።ትናንት ብራሰልስ ቤልጅየም በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ ጎን የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኢጣልያውን አቻቸውን ጁሴፔ ኮንቴን ስለራኬተ ጉዳይ ቢጠይቋቸውም ጉዳዩ በሃገሪቱ የፍትህ አካል የተያዘ በመሆኑ የኢጣልያ መንግሥት ጣልቃ ሊገባ አይችልም ሲሉ እንደመለሱላቸው ተናግረዋል። የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጉዳዩን ኢጣልያ በተለየ ሁኔታ ልታየው እንደሚገባ አሳስበዋል።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በበኩላቸው የራኬተ ድርጊት ሰብዓዊ ተግባር እንጂ ወንጀል አይደለም ሲሉ በማስረዳት የኢጣልያ መንግሥት ራኬተን እንዲለቅ ጥረት ማድረጋቸውን ተanግረዋል። 
«የሰው ህይወት ማትረፍ ወንጀል ሊሆን አይችልም።ከሰብዓዊ ተግባር ውጭ ምንም ሊሆን አይችልም፤እንደዚያም ነው ሊታይ የሚገባው።ተቃራኒው ወንጀል ሲሆን ነው።ለዚህም ነው ኢጣልያ ውስጥ የሚሆነውን መረዳት ያልቻልነው።ይህ ሁኔታ እንዲቆም ለማገዝ የተቻለውን ሁሉ አማራጭ እንዲጠቀሙ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ የሮም ኤምባሲን ጠይቄያለሁ።ፍርድ ቤት ይህን ጉዳይ ማየቱን እቀበላለሁ።ሆኖም ሰዎችን ከባህር ላይ መታደግ የወንጀል ድርጊት አይደለም፤ሰብዓዊ ተግባር እንጂ።»

Außenminister Deutschland Afghanistan Heiko Maas Salahuddin Rabbani
ምስል picture-alliance/AA/C. Karadag
Lampedusa Hafen Sea Watch 3 Anlandung Bootsflüchtlinge
ምስል picture-alliance/Photoshot
Italien Innenminister Salvini
ምስል picture_alliance/dpa/ZUMA Wire/S. Guidi

የተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች ግለሰቦችና የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ሳይቀር ለራኬተ አድናቆታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።የራኬተ ጀብዱ ናኝቶ የጀርመኑ የእርዳታ ድርጅት ሲዋች ካሬተ ከታሰረች በኋላ ከአንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ተዋጥቶለታል።ከዚህ ውስጥ ሁለት የጀርመን ታዋቂ የቴሌዢዥን ፕሮግራም አዘጋጆች ባስተላለፉት ጥሪ የተሰበሰበው ከ735 ሺህ ዩሮ በላይ ገንዘብ ይገኝበታል።በሌላ የኢጣልያ ፌስቡክ አማካይነት ከ410 ሺህ ዮሮ በላይ ገንዘብ ገቢ ማድረግ ተችሏል። የሲዋች ቃል አቀባይ ሩበን ራኬተ ገንዘቡ ከህግ ጋር ለተያያዙ ለካሬተ የወደፊት ወጭዎች መሸፈኛ እና  በኢጣልያ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ስር የወደቀው ሲዋች መርከብ ካልተመለሰ ሌላ አዲስ መርከብ ለመግዣ እንደሚውል ገልጸዋል።ለኢጣልያው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጉዳዩን ያስተናገዱበት መንገድ የፈለጉት ውጤት ላይ አድርሷቸዋል።በአቋማችን በመጽናታችን ስደተኞቹ ኢጣልያ እንዳይገቡ ብቻ ሳይሆን እንዳይቀሩ ማድረጉ ተሳክቶልናል ዓይነት መልዕክት ነበር በመጨረሻ ያስተላለፉት።
«ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው 41ዱ ስደተኞች በፈረንሳይ በፊንላንድ በሉክስምበርግ በፖርቱጋል እና በጀርመን ይሰተናገዳሉ።የኢጣልያ መንግሥት ሰሞኑን የወሰደው እርምጃ አውሮጳን እና እነዚህን ሀገራት ለማንቃት አገልግሏል።ምክንያቱም ከኛ እንደቀደሙት ወደቦቻችንን ከፍተን ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች በግልጽ ኢጣልያ ነበር የሚቆዩት።» 
ራኬተ ከወንጀል ክሱ ሌላ ያለፍቃድ የኢጣልያን የባህር ክልል በመጣስ በሚያስቀጣው በኢዲሱ የኢጣልያ ህግ ጠንከርያለ ቅጣት ሊጠብቃት ይችላል ቅጣቱ ግን በርስዋ ብቻ የሚወሰን አይሆንም ለሲዎችም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል።ሲዋች እንደሚለው የራኬተ መታሰር ብዙ ስደተኞች በሜዴትራንያን ባህር ላይ ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑ አይቀርም። እንደ ድርጅቱ የርስዋ መታሰር ሌሎች ካፕቴኖችን ስጋት ውስጥ መክተቱ አይቀርምና።ይህ በእንዲህ እንዳለ ካሮላ ራኬተ ዛሬ ልትፈታ ትችላለች የሚሉ ዘገባዎችም እየወጡ ነው። 

Italien Rettungsschiff Sea-Watch 3 im Hafen von Lampedusa
ምስል Reuters/G. Mangiapane

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ