1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አካል ጉዳተኞችን የሚያግዙት የእህትማማቾቹ ፈጠራ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19 2014

ወጣት ሱመያ ሁሴን እና አፍራህ  ሁሴን ይባላሉ። ወጣቶቹ አካል ጉዳተኞችን በሚያግዙ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች ላይ ያተኮሩ  እህትማማቾች ናቸው።አፍራህ አካል ጉዳተኞች ያለምንም ችግር ደረጃ መውጣት እና መውረድ የሚያስችል ሴንሰር የተገጠመለት ተሽከርካሪ ወንበር፤ሱመያ ደግሞ ማየት ለተሳናቸው ፅሁፍን ወድ ድምፅ የሚቀይር ቴክኖሎጅ አበልጽገዋል።

https://p.dw.com/p/4AW6i
Äthiopien Addis Ababa | Technik Studenten Sumeya Hussen und Afrah Hussen
ምስል Privat

አካል ጉዳተኞችን የሚያግዙት የእህትማማቾቹ ፈጠራ


ወጣት ሱመያ ሁሴን እና  አፍራህ  ሁሴን  ይባላሉ። ወጣቶቹ አካል ጉዳተኞችን በሚያግዙ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች ላይ ያተኮሩ  እህትማማቾች ናቸው።ሱመያ  ከጅማ ዩንቨርሲ በኤለክትሪክ እና ኮምፒዩተር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን፤በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩንቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን በመከታተል ላይ ትገኛለች።ታናሽ እህቷ አፍራህ ሁሴንም  በዚሁ ዩንቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነች።
በአስራዎቹ መጨረሻ  እና በሀያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኙት እነዚህ ወጣት እህትማማች ሴቶች የፈጠራ ሀሳብ የጀመሩት ተወልደው ባደጉበት አርባ ምንጭ ከተማ ሲሆን  በወላጆቻቸው ስራ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ሲዛወሩ ደግሞ የየተሻለ ዕድል በማግኘታቸው ይህንን የፈጠራ ሀሳባቸውን አጠናክረው ገፉበት።ለዚህም የወላጆቻቸው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃሉ።አፍራን እንደምትለው በተለይ አባታቸው።  
«የቤት ውስጥ እቃዎች ሲበላሹ እና «ፋዘር» ሲጠግን  ይህ «ካፓሲተር» ነው እያለ ያሳየንን ነበር። እና ያ የበለጠ እንድንሠራ ይገፋፋን ነበር።» በማለት ገልፃለች። ከዚያም 7ተኛ ክፍል እያለች የመጀመሪያውን የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጅ መስራቷን ገልፃለች።
ሱመያ በበኩሏ የእናታቸው በእነሱ ላይ የነበራቸው መስራት  ይችላሉ የሚለው ዕምነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ትገልፃለች።«እንደመነሻ ብዬ የማስበው የቤተሰብ ሁኔታ ነው። ቤት  አሁን ሶስት ነን ሶስታችንም ሴቶችን ነን። እና ውጤታችን ጥሩ ነበር።  ውጤታችንን አይተው ወላጆቻችንን ከሰዎች ጋር ሲያወሩ አይ ሴቶች ናቸው  አሁን ትንሽ ከፍ ስኪሉ ነው። ከዛ በኋላ ትምህርቱን ይተዉታል።  የሚል «ኮሜንት» ይሰጣቸው ነበር ለወላጆቻቸን።  «ማዘር»ግን የኔ ልጆች ወንዶችን ያስንቃሉ። እንዲህ የሚባሉ አይደሉም ትል ነበርና። እሷ በኛ ላይ ያላት እምነት እንድንጠነክር አድርጎናል።  ሌላው  አባታችን ሁልግዜ የሚነግረን ነገር ነበር። ምን ይለናል አንድ ሰው እንዴት ነው እውቀት ሳይጨምር  አንድ ቀን የሚያልፍበት እንዴት ነው ይል ነበር።»በማለት ሱመያ የወላጆቿን ድጋፍ ገልፃለች። 
በዚህ ሁኔታ በወላጆቻቸው ድጋፍ የተበረታቱት ሱመያ እና አፍራህ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን መስራት ችለዋል።ከነዚህም ውስጥ አፍራህ ያበለፀገችው አካል ጉዳተኞች ያለምንም ችግር ደረጃ መውጣት እና መውረድ የሚያስችል ሴንሰር የተገጠመለት ተሽከርካሪ ወንበር  አንዱ ነው። 
«እኛ ሀገር «ዊል ቸር» ሁሉ  «ማንዋል» የሚሰራው ።» ካለች በኋላ የእሷ ተሽከርካሪ ወንበር  ከሌሎች የሚለይበትን   ዘርዝራለች።  «ምንድን ነው በምቾት እንዲሄዱ፣ ያለ ሰው እገዛ  ደረጃ ሲኖር ደረጃ ይወጣል።» የኛ  ሀገር  መሰረተ ልማት ደካማ ስለሆነ ያንን ያማከለ ነው።» ብላለች።ተሽከርካሪ ወንበሩ ባለስድስት እግር በመሆኑ ሚዛኑን ለመጠበቅ እንደሚያስችል ተናግራለች። የፍጥነትን የሚቆጣጠር እና ከኋላ የሚመጣን ተሽከራካሪም ይሁን ሌላ ነገር ቀድሞ የሚጠቁም ሴንሰር ስላለው ከአደጋ የሚጠብቅ መሁኑንም አክላለች።
ከዚህ በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የሀኪሞችን የስራ ጫና የሚቀንስ እና የፅኑ ህሙማንን ሁኔታ ተከታትሎ ለሀኪሞች በተንቀሳቃሽ ስልክ መረጃ የሚሰጥ መተግበሪያም ሰርታለች።በቅርቡ ለሽልማት ያበቃት «ስማርት ቴብል»የተሰኘ በትምህርት ቤቶች እና በቤተ መፃህፍት ሊቀመጥ የሚችል ለትምህርት መርጃ መሳሪያነት የሚያገለግል እና የትምህርት ስርዓቱን የተሻለ ለማድረግ  የሚጠቅም የፈጠራ ሀሳብም አላት።
ታላቅ እህቷ ሱመያ ደግሞ ጅማ ዩንቨርሲቲ በነበረችበት ወቅት ከሌሎች ጓድኞቿ ጋር በመሆን ማየት ለተሳናቸው ወገኖች የሚያገለግል  ፅሁፍን ወደ ድምፅ መቀየር የሚችል ቴክኖሎጅ አበልፅጋለች።ይህ ቴክኖሎጅ ሱመያ እንደምትለው ለአጠቃቀም ቀላል የበይነመረብ ግንኙነት የማይፈልግ እና በአማርኛ ቋንቋ ጭምር  የተዘጋጀ ነው።
«ምንድነው ሚያደርገው «ዲቫይሱ» እንተርኔት አይፈልግም  ሀይል  ብቻ ነው የሚፈልገው። ማንኛውም ሬዲዮ መጠቀም የሚችል ሊጠቀመው ይችላል። ቀላል የሆኑ  ቁልፎችን ነው ያሉት።»ካለች በኋላ  ለምሳሌ tየድምጽ መጨመርያ ና መቀነሻ አለው። እንደገና ሴቭ ማድረግ ቢፈለግ «media storage» ላይ  ሴቭ የሚያደርግበት እንዲሁም ቋንቋ የሚመረጥበት «በተን» አለው። ለጊዜው እንግሊዘኛ እና አማርኛ ቋንቋ ነው ያለው።» ካለች በኋላ «የኛ ማህበረሰብ ስናይ በተለይ ወደ ሀገር ቤት  ያለው ማህበረሠብ ምን ያሀል ስማርት «ዲቫይስ» ተደራሽ ነው። ምን ያህል ኢንተርኔት  ያገኛል ሚለውን ስናይ፤ ጥያቄ ምልክት ነው። ይህን በማሰብ ነው ለተጠቃሚው ቀላል እንዲሆን የተደረገው ።» በማለት አስረድታለች።
ለመሆኑ ወጣቶቹ የፈጠራ ስራዎቻቸው በአካል ጉዳተኞች ላይ እንዲያተኩሩ ያደረጋቸው ምክንያት ምንድነው?
«መጀመሪያ ወደ ወደዚህ እንድናተኩር ያደረገን አሁን ላይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በተለያዩ ዘርፎች ይሰራሉ።» ለመሳሌ እርሻ ላይ ጤና ላይ እናያለን ያን ያህል  ባይሆን እንኳን ግን የተወሰነ መሻሻል አለ።»ካለች በኋላ በአካል ጉዳተኞች ላይ ያለው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ እዚያ ላይ ማተኮራቸውን ሱመያ ገልፃለች።

Äthiopien Addis Ababa | Technik Studenten Sumeya Hussen und Afrah Hussen
ምስል Privat
Äthiopien Addis Ababa | Technik Studenten Sumeya Hussen und Afrah Hussen
ምስል Privat
Äthiopien Addis Ababa | Technik Studenten Sumeya Hussen und Afrah Hussen
ምስል Privat

አፍራህም የአህቷን ሀሳብ እንዲህ ስትል ትጋራለቸ።«በየትኛውም ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን  መፍጠር ይቻላል። ብዙ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል በሌሎች ዘርፎች። እኔን ደሞ  «ሞትቬት» ያደረገኝ 10ኛ ክፍል ሳለሁ በጣም ጎበዝ የሆነ የትምህርት ቤቱ ሰቃይ ተማሪ ነበረ ።« ዊል ቸር »ተጠቃሚ ነው።ትምህርት ቤቱ   ደረጃ አለው። እና  አይወጣም ሁሌ «ክላስ» ውስጥ  ነው። ወላጆቹ ናቸው መጥተው  ሚወስዱት። ተማሪው  ሁሉ ዕረፍት ሲወጣ  ብቻውን « ክላስ» ውስጥ  የሚቀመጠው።» በማለት በአካል ጉዳተኞች ላይ ብዙ ፈጠራዎች  እንደሌሉ ገልፃለች።
ወጣቶቹ በእነዚህ ስራዎቻቸው የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ በሞዴልነት ደረጃ የተቀመጡትን እነዚህን  ስራዎቻቸውን በሰፊው ተመርተው ወደ ተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው። ሱመያ እንደምትለው ይህንን ስራቸውን ለማሳካትም የተለያዩ የግንኙነት መረቦችን በመጠቀም ከተለያዩ አካላት ጋር ቀረቤታ በመፍጠር እገዛ እና ድጋፍ የማግኘት ሀሳብ አላቸው። 
«ወደዚህ ደረጃ ስንመጣ የመጀመሪያው   ዋና ነገር ብለን ያሰብነውን «ኔትዋርካችን»  መስፋት አለበት የሚል ነው። ምክንያቱም በተለያየ ቦታ ላይ መደገፍ የሚፈልጉ ብዙ አይነት ሰዎች ይኖራሉና። እኛም አለ መድረሳችን እና «ኤክስፖዝ» አለመሆናችን  ነው ብለን እናምናለን።» ካለች በኋላ መንግስታዊ   ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ውድድሮችን በመጠቀም  ተመሳሳይ  ዓላማ ካላቸው ሰዎች ጋር እንገናኛለን ብለን እናስባለን በማለት ገልፃለች። 
በዚህ ሁኔታ ዕቅዳቸውን  በማሳካት ለወደፊቱ ምርቶቻቸውን በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ የማድረግ ሀገራቸውንም ህብረተሰቡንም የማገልገል ሰፊ ህልም አላቸው።ወጣቶቹ ዕቅዳቸው እንዲሳካ እየተመኘን የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በዚህ ተጠናቋል።

Äthiopien Addis Ababa | Technik Studenten Sumeya Hussen und Afrah Hussen
ምስል Privat

ሙሉ ዘግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ