1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አከራካሪው የደቡብ አፍሪቃ የመሬት ይዞት ተሀድሶ እቅድ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2011

በደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድ ስርዓት ከተገረሰሰ ከ24 ዓመታትም በኋላ እኩልነት በተጓደለው የመሬት ድልድል አሰራር ላይ ብዙም የተቀየረ ነገር የለም። እና በወቅቱ የሀገሪቱ መንግሥት የመሬት ድልድልን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ለውጥ ለማድረግ እያሰላሰለ በዚሁ መሀል፣ በተንታኞች ትዝብት፣ ዋና የሚባሉ ጥያቄዎቹን ችላ ያለ ይመስላል። 

https://p.dw.com/p/36SiP
Südafrika Mahikeng Auschreitungen Cyril Ramaphosa
ምስል Getty Images/AFP/M. Safodien

የመሬት ድልድል አሠራር ላይ ብዙም የተቀየረ ነገር የለም


ይህን የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ሀሳብ ተከትሎ በክዋዙሉ ናታል ግዛት የሚገኙት የዙሉ ብሔረ ሰብ ንጉሥ ጉድዊል ዝዌሌቲኒ ሰሞኑን አንድ ያልተለመደ ሀሳብ አቅርበዋል። ወደ ሶስት ሚልዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ባለቤት የሆኑት ባህላዊው መሪ ነጮች ገበሬዎች እሳቸው በኢንጎንያማ ተቋም ስር የሚያስተዳድሩትን  የአያት ቅድም አያታቸውን መሬት እንዲያለሙላቸው ርዳታ ጠይቀዋል። ይህ ንጉሥ ዝዌሌቲኒ ያቀረቡት ሀሳብ በተለይ  ለመሬት አልባዎቹ ጥቁሮቹ የሀገሪቱ ዜጎች የእርሻ መሬት ለማከፋፈል እቅድ ለያዘው ለገዢው የደቡብ አፍሪቃ ፓርቲ፣ ኤ ኤን ሲ «መሬቴን አትንኩብኝ» በሚል የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል። የዙሉው ባህላዊ ንጉሥ በደርባን ባሰሙት ንግግር ወቅት መንግሥት መሬታቸውን እንደማይነካባቸው  የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ በጽሁፍ እንዲያረጋግጡላቸው ጠይቀዋል። ሌሎች ባህላዊ መሪዎችም ቢሆኑ መንግሥት የሀገሪቱን የእርሻ መሬት ከባለቤቶቹ ፣ አንዳችም ካሳ ሳይከፍል በመውሰድ ለመሬት አልባዎቹ  ዜጎች  ለማከፋፈል ማሰላሰል የያዘበትን እቅድ በቸልታ እንደማያዩት ተናግረዋል።  እነዚህ መሪዎች እና ዝዌሌቲኒ በአንድነት ከደቡብ አፍሪቃ መሬት መካከል 13 ከመቶውን ይቆጣጠራሉ።  ይህ እቅዱ ተግባራዊ ለማድረግ የሕገ መንግሥት ለውጥ አስፈላጊ መሆን አለመሆኑን አንድ የምክር ቤት ኮሚቴ በማጣራት ላይ ነው። ኮሚቴው ባለፈው መስከረም ወር ለማቅረብ አስቦት የነበረውን   የምርመራ ውጤት፣ ከሕዝብ የቀረቡለትን እጅግ ብዙ  ሀሳቦች እና ጥያቄዎችን በጠቅላላ ማየት ባለመቻሉ ውጤቱን ይፋ የማድረጉን  ሂደት ወደ ህዳር ወር አስተላልፎታል።  
በፕሬዚደንት ራማፎዛ አመለካከት መሰረት፣ የሚወረሰው መሬት በተለይ እስከዛሬ ድረስ ባለቤት የሌላው ነው።  ዝዌሊቲኒን የመሳሰሉ ባህላዊ መሪዎች ያልታረሰ የእርሻ መሬታቸውን አሁን ለነጭ ገበሬዎች  የሚያሳርሱበት ሁኔታ መንግሥት መሬት ለመውረስ በያዘው እቅድ እንዳይነኩ ሊያደርጋቸው የሚችል አንድ መንገድ ሊሆን ይችላል። አፍሪ ፎረም የተባለው የነጮች እርሻ ድርጅት ሊቀ መንበር ካለ ኪሪል  የንጉሥ ዝዌሊቲኒን የርዳታ ጥሪ የተቀበሉ ሲሆን፣ ዝዌሊቲኒ ይህንኑ ትብብር በውል ፊርማ እንዲያረጋግጡላቸው እንደሚፈልጉ ነው ካለ ኪሪል የገለጹት። ትብብሩ የሁለቱን ውሁዳን ቡድኖች ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማ እንዳለው  በደቡብ አፍሪቃ የሄለን ሱዝማን ተቋም  የፖለቲካ ተንታኙ አንቶን ፎን ዳዛይን  ከDW  ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት በኩል የእርሻ መሬት ብቻ የማግኘቱ ፍላጎት ብቻ አይደለም  የተጠናከረው። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ደቡብ አፍሪቃውያን ስራ ፍለጋ ብለው ከገጠሩ ወደ ከተሞች ይሄዳሉ። ያም ቢሆን ግን፣  ስራ የማግኘት ም ሆነ ሁነኛ መኖሪያ የማግኘት እድላቸው ጠባብ በመሆኑ  ከከተሞች ወጣ ብሎ  በተስፋፉት ጎስቋሎቹ ሰፈሮች ከመኖር የተሻለ ነገር አያጋጥማቸውም። መንግሥት በከተሞች  እና በከተሞች መዳረሻ ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ እና የተጓደለውን  ማህበራዊውን እኩልነት ለማስተካከል  ታድያ መሬት እንደሚያስፈልገው  ነው ፎን ዳዛይን የተናገሩት። ይህን ለማድረግ ግን ምንም እንኳን ካለፉት ብዙ ወራት ጀምሮ ክርክሩ ቢቀጥልም፣ ሕገ መንግሥቱን መለወጥ እንደማያስፈልግ  ፎን ዳዛይን አስረድተዋል።
« በኔ አስተያየት ሂደቱን ለማስቀጠል ሕገ መንግሥቱ የግድ መለወጥ አለበት ብዬ አላስብም።  አሁን የሚሰራበት ሕገ መንግሥት ለተወሰነ ምክንያት ሲባል መሬት የሚወረስበትን ሁኔታ ይፈቅዳል። ይሁን እንጂ፣ ሰዎች ከገጠሩ ወደ ከተሞች በብዛት የሚሄዱበት ሁኔታ በፖለቲከኞች ላይ  ግፊቱን አጠናክሯል።  እና ጉዳዩ  ጥቁሮቹ ደቡብ አፍሪቃውያን  መሬታቸውን ከተነጠቁበት ታሪካዊ እውነታ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ የተጓደለውን ማህበራዊ እውነታመቀነስ ከሚቻልበትም ገሀድ ጋር ተያይዞ መታየት ይገባዋል። »
ባለፉት 20 ዓመታት ይህን የመሬት ጉዳይ በተመለከተ ምንም የተሰራ ነገር የለም ፣  ፎን ዳዛይን እንደሚሉት ፣ ይህ የሆነው መንግሥት ለመሬት ተሀድሶ  0,3% በጀት ብቻ በመመደቡ ነው።  ሙስና፣ የፖለቲከኞች በጎ ፈቃድ መጓደል እና የመንግሥቱ እቅድ ላይ ግልጸ አለመሆንም ተጨማሪ ችግር ሆኖ ያዩታል።  መንግሥት የትኛውን መሬት ነው የሚወርሰው? ከዚሁ ርምጃ የሚጠቀመው ማን ነው? ከመሬታቸው ለሚነሱት ርዳታ ይቀርባል፣ ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽ አላገኙም፣  በዌስትካፕ ዩኒቨርሲቲ የመሬት ጉዳዮች አጥኚ ቤን ካዝንስም የመንግሥት እቅድ ላይ ግልጽነት እንደተጓደለ ነው የሚያምኑት።  

eco@africa Rehabilitierung von Land in Südafrika
ምስል DW
Südafrika König der Zulu Goodwill Zwelithini kaBhekuzulu
ምስል Getty Images/AFP/R. Jantilal

« ከታህሳሱ ጉባዔ በፊት ራማፎዛ ካሳ ሳይከፈል መሬት የመውረሱን ሀሳብ መቃወማቸውን እና ይህን አስተሳሰብ ለመታገል ሙከራ ማድረጋቸውን እናውቃለን።  ይሁንና፣ በዚያው በታህሳሱ ጉባዔ ላይ ይህን ሀሳብ እንደ ፓርቲው ፖሊሲ እንዲቀበሉ በገዢው ኤ ኤን ሲ መገደዳቸውንም እናውቃለን።  » 
በደቡብ አፍሪቃ በ2019 ዓም ምርጫ ይደረጋል። ጁልየስ ማሌማ በሚመሩት የተቃዋሚው የኤኮኖሚያዊ ነጻነት ታጋዮች ፓርቲ  ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ የመሬት ድልድል ተሀድሶ ለማድረግ የገቡትን ቃል አጥብቆ ይቃወማል። ይከው ፓርቲ መንግሥት የነጮች ገበሬዎችን ሰፋፊ  የእርሻ መሬት በጠቅላላ እንዲወርስ ነው የሚሟገተው።    ለመሬት ማደላደሉ እና ማከፋፈሉ ተሀድሶ  የሕገ መንግሥት ለውጥ ወይም ማሻሻያ ማድረግ ካስፈለገ ይህ እውን ይሆን ዘንድ ሁለት ሶስተኛውን የእንደራሴዎች ድምጽ ማግኘት የግድ ይላል፣ ይህንን ለማግኘት ደግሞ ኤኤ ኤን ሲ እና ኤ ኤፍ ኤፍ መስማማት ይኖርባቸዋል። ይህ ዓይነት ስምምነት መፈጠሩ ግን አጠያያቂ ነው የማይታሰብ ነው እንደ ቤን ካዝንስ አስተያየት። በዚህም የተነሳ የመሬት ተሀድሶ ጉዳይ ከምርጫ 2019 በፊት የሚጀመር አይጀመርም  ተብሎ ነው የሚገመተው። ከዚህ በተረፈም በአሁኑ ጊዜ ጥያቄው   ስጋቱ የቀነሰ እንደሚመስል ካዝንስ ገልጸዋል።
« በአሁኑ ጊዜ ሁኔታዎች ተረጋግተዋል። በመካከለኛው መደብ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል እና የግሉ ዘርፍ መጀመሪያ ላይ ተደናግጠው ነበር። አሁን ግን ስጋታቸው እየቀነሰ መጥቷል። ሂደቱ እንደተነቃቃ ይታያቸዋል። ይህን ከነጮቹ ገበሬዎች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል። ብዙዎቹም፣  በተለይ ከፕሬዚደንቱ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ ለማህበራዊ ችግሮች በጋራ መፍትሔ በማፈላለጉ ሂደት ውስጥ እንደተካተቱ ነው የሚሰማቸው።» 
ከደቡብ አፍሪቃ ለም የእርሻ መሬት መካከል 80% የተያዘው በ15% ነጮች ገበሬዎች ብቻ ነው።

Südafrika Attacken auf weiße Farmer
ምስል Getty Images/AFP/G. Khan

አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺቭኮቭስኪ

ማንተጋፍቶት ስለሺ