1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪው ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት

ሐሙስ፣ መጋቢት 3 2012

በአንጻሩ ደግሞ መንግሥት በራሱ የሚቆጣጠራቸው አንዳንድ የመገናኛ ዘዴዎችን ጨምሮ በግል የተያዙ የመገናኛ ብዙሃን የሐሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግርን የሚያንጸባርቁ ሃሳቦችን እያሰራጩ በቅጽበት ይቅርታ ሲጠይይቁ ይታያል።

https://p.dw.com/p/3ZJQc
Symbolbild | Mikrofon
ምስል Colourbox/R. Schramm

«ሕጉ በነጋሪት ጋዜጣ አለመታተሙ ተግባራዊነቱን አዘግይቶታል ተብሏል»

የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የወጣው አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አለመውጣቱ ህጉን በፍጥነት ለመተግበር አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል ሲሉ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅ እና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በላይሁን ይርጋ ተናገሩ። ሕጉ በፍጥነት ተግባራዊ ቢደረግ እንኳ የአፈጻጸም ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ደግሞ አንድ የሕግ ምሁር ገልጸዋል።
በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀው የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ገና ተግባራዊ አልተደረገም።በአንጻሩ ደግሞ መንግሥት በራሱ የሚቆጣጠራቸው አንዳንድ የመገናኛ ዘዴዎችን ጨምሮ በግል የተያዙ የመገናኛ ብዙሃን የሐሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግርን የሚያንጸባርቁ ሃሳቦችን እያሰራጩ በቅጽበት ይቅርታ ሲጠይይቁ ይታያል። ችግሮቹ ፈጥነው በሕግ ሊገቱ እና የሕዝቡ የመረጃ ነጻነት መብት ሊከበር ሲገባ ሕጉ ዳተኝነት አሳይቷል የሚል ወቀሳ ሲሰነዘር ይሰማል። በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ማርቀቅ እና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ እንደሚሉት በቅርቡ የጸደቀው የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን እና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አለመውጣቱ ሕጉን በፍጥነት ተግባራዊ እንዳይኾን አድርጎታል።
በመኾኑም የሃገሪቱ የወንጀል ሕግ እስከዛሬ ሲያደርግ እንደነበረው ሐሰተኛ መረጃንም ሆነ የጥላቻ ንግግር የህግ ጥሰቶችን እንደየክብደታቸው እያየ ለመፍታት ተገዷል  ይላሉ አቶ በላይሁን።
የሐሰተኛ የመረጃ ስርጭትን እና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ከዓለምአቀፍ ተሞክሮ ተወስዶ የወጣ ነው የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶ/ር መሰንበት አሰፋ ናቸው። ነገር ግን ይላሉ ዶ/ር መሰንበት ፖለቲካን መሰረት አድርገው የሚወጡ የሐሰተኛ መረጃዎችም ኾነ የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠር ሕጉ የአፈጻጸም ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ይገልጻሉ።
   በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 29 የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝ እና የመግለጽ መብትን አረጋግጧል። በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የሚተላለፉ እነዚሁ ሐሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ከመብዛታቸው እና ለቁጥጥር አዳጋች ከመኾናቸው የተነሳ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ  ያስቸግሩ ይኾን የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም ። ሃሳቦቹ የቱንም ያህል ቢበዙ አዲስ የወጣው አዋጅ የትርጉም ችግር ሳያስከትል እንዲተገበር ኾኖ ነው የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ደንኤል በቀለ ናቸው።
በመንግሥትም ይሁን በግል በተያዙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች በስህተት  የሚተላለፉ ሐሰተኛ መረጃዎች መረጃ ፈላጊውጋ መድረሳቸው ተጠያቂነትን የሚያስከትልበት አግባብን በተመለከተ ጥያቄ ያነሳንላቸው ዶ/ር ዳንኤል እንደሚሉት የመገናኛ ብዙሃን እና ሠራተኞቻቸው በህግ በተፈቀደላቸው ማዕቀፍ ውስጥ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ሕጉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፤ ከዚህ አፈንግጠው እና ሆን ብለው ጥፋተንነትን ለሚያስከትሉ ተግባራት ተጠያቂነትን እንዲኖር በህጉ ላይ በግልጽ መስፈሩንም ተናግረዋል። 
በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ተሰደው በውጭ የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል ቀደም ሲል እስር ቤት የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞችም ተፈተዋል። ነገር ግን የመንግሥትን ጨምሮ አንዳንድ የግል የመገናኛ ብዙኃን በጥንቃቄ ጉድለት በሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ነቀፋ እየደረሰባቸው ይገኛል። 
ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ