1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ እስክንድር ነጋ ከእስር ተፈቱ፤ የእነ አቶ ጃዋር ፍቺ እየተጠበቀ ነው

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 29 2014

አንድ አመት ከስድት ወር ገደማ እስር ላይ የቆዩት አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል መፈታታቸውን ፖርቲያቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አረጋግጧል። ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ከተገደለ በኋላ የታሰሩት የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ፍቺ እየተጠበቀ ነው።

https://p.dw.com/p/45H2Q
Kombobild Eskinder Nega und Jawar Mohammed

አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከእስር ተፈቱ። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት ፖለቲከኞች የተፈቱት ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ በእስር ከቆዩ በኋላ ነው። 

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የቂሊንጦ እስር ቤት የነበሩት አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል መፈታታቸውን ፖርቲያቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አረጋግጧል። ባልደራስ "እውነተኛ የዲሞክራሲ ታጋዮች፣ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች ከግፍ እስር ተፈተዋል" ብሏል።

ፓርቲው በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጫቸው ፎቶ ግራፎች ሁለቱ ፖለቲከኞች ከትከሻቸው ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ጣል አድርገው ታይተዋል። 

አቶ እስክንድር ነጋ ከሌሎች የፓርቲው አባላት ጋር የታሰሩት ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ከተገደለ በኋላ የተፈጠረውን ኹከት ተከትሎ ነበር።

ከድምፃዊው ግድያ በኋላ በአዲስ አበባ ከታሰሩ መካከል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ይገኙበታል። አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለ ከእስር ይፈታሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።