1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ ልደቱ በ 100 ሺህ ብር ዋስ እዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጠ

ማክሰኞ፣ መስከረም 12 2013

የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ  ትዕዛዝ  ሰጠ።  የዛሬውን የችሎት ውሎ የተከታተሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ ፕሬዚደንት አቶ አዳነ ታደሰ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ልደቱ ዛሬ ወይም ነገ ይፈታሉ።

https://p.dw.com/p/3ir8e
Äthiopien Pressekonferenz EDP in Addis Abeba
ምስል DW/G. Tedla

የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ  ትዕዛዝ  ሰጠ።  የዛሬውን የችሎት ውሎ የተከታተሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ ፕሬዚደንት አቶ አዳነ ታደሰ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት  ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12 ከሰዓት በተካሄደዉ ችሎት ነው። 
« አዳማ ላይ ምስራቅ ሸዋ አቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበት ጉዳዩ ሲታይ ነበረ ፤ ባለፈዉ አርብ ጉዳዩን እንደገና ሲያይ የነበረዉ የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕጎችን እና የጠበቂቻችንን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፤ ሰኞ በጉዳዩ ላይ ተመካክረን ዛሬ ዉሳኔ እንሰጣለን ፤ ባለዉ መሰረት ዛሬ የተሰየመዉ ችሎት አቶ ልደቱ በዋስ ተለቀዉ ጉዳያቸዉን እንዲከታተሉ ፤ በፍትህ ሂደቱ ላይ የሚያስከትለዉ  ጉዳት የለም ስለዚህ አቶ ልደቱ በ100 ሺህ ብር ዋስ ወጥተዉ ጉዳያቸዉን ዉጭ ሆነዉ እንዲከታተሉ በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስከረም 20 በመስጠት የዛሬዉ ችሎት ተጠናቆአል። ስለዚህ አቶ ለልደቱ 100 ሺህ ብር ለማቅረብ በመንቀሳቀስ ላይ ነን ፤ ቢሮ ማስጨረስ ያለብንን ጉዳዮች ለማስጨረስ እየሰራን ነዉ። ከተቻለ አቶ ልደቱ ዛሬ መስከረም 12 ከእስር ወጥተዉ ቤታቸዉ ያድራሉ፤ ካልሆነ ነገ መስከረም 13 ይለቀቃሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ  አንጋፋዉ ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌዉ የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶችን አሰባስበህ በገንዘብ ረድተሃል በሚል በቁጥር ስር ከዋሉ በኋላ ጉዳያቸዉ  በቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ሲታይ ቆይቶ፤ በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ ልደቱ አያሌዉን በነጻ ቢያሰናብታቸዉም  ፖሊስ አቶ ልደቱ አያሌዉን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከ17 ቀናት በላይ ተጉላልተዋል ሲሉ  አቶ አዳነ ታደሰ ተናግረዋል። አቶ ልደቱ የጉዳዩን ኢ ፍታዊነት በመታዘብና በፍትህ ስርዓቱ ላይ ተስፋ በመቁረጥ ጠበቆቻቸዉን እስከማሰናበት መድረሳቸዉን የተናገሩት አቶ አዳነ ታደሰ  ከዚያ በኋላም ፓርቲያቸዉ ከጠበቁቻቸዉ ጋር በመመካከር አካልን ነፃ የማዉጣት ክስ ለመመስረት ዝግጅት ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል። 

 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ