1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ

እሑድ፣ ነሐሴ 9 2013

በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና መንግስት አሸባሪ በሚለው በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት ቅርጽና አድማሱን አስፍቷል። በሁለቱም ኃይላት አመራር በኩል የተሰጡ መግለጫዎች እና እንቅስቃሴዎች የጦርነቱ መልክ መቀየርን የሚያሳዩ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3yyVG
Äthiopien Tigray-Krise | Armee
ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

«ምንም የተጀመረ የውስጥ ድርድርም፤ የውጭ ድርድርም እንደሌለ ላረጋግጥ እፈልጋለሁ»

በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና መንግስት አሸባሪ በሚለው በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት ቅርጽና አድማሱን አስፍቷል። በሁለቱም ኃይላት አመራር በኩል የተሰጡ መግለጫዎች እና እንቅስቃሴዎች የጦርነቱ መልክ መቀየርን የሚያሳዩ ናቸው። ሕወሓት ከመንግስት ጋር ለመደራደር ያስቀመጣቸው ቅድመ ኹኔታዎች  እስካልተሟሉ ድረስ በጦርነቱ እንደሚገፋበት ዐስታውቋል። ከዚያም ባሻገር በጦርነቱ የሚሳተፈው የታጠቀው ኃይል ብቻ ሳይኾን ሕዝቡም በሙሉ  ሠራዊት ነው ሲል ተደምጧል።

በፌዴራል መንግስቱ በኩልም እድሜ እና አቅሙ የሚፈቅድላቸው ኢትዮጵያውያን በመላ «ሀገርን ለመከላከል» በተባለው ዘመቻ እንዲሳተፉ ነሐሴ 4 ቀን፣ 2013 ዓም በተጻፈ መግለጫ «ሀገራዊ ጥሪ» ተላልፏል። የሕወሓት ኃይል የሚሰነዝረውን፦ «ጥቃት ሕዝባዊ መልክ እንዲይዝ» እያደረገ መሆኑን የገለጠው መንግስት ይህን «መመከት የሚገባውም በዚያ አግባብ ነው፤ የመላ ሕዝባችንን የማያዳግም ምላሽ ሊያገኝ ይገባል» ብሏል በክተ  ጥሪው። ጦርነቱ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ወጥቶ በአማራ እና አፋር ክልሎችም ተስፋፍቷል። የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፤ ብዙዎች ቆስለዋል፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ በገፍ ከቀዬያቸው መፈናቀላቸው ተዘግቧል።

ሕወሓት እና ብልጽግና ፓርቲን የመሰረቱት የቀድሞ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ከገቡበት ቅራኔ ወጥተው ራሳቸውን ከግጭት እና ከደም አፋሳሽ ድርጊት እንዲያቅቡ በርካት ሙከራዎች ተደርገዋል። ግጭት ጦርነቱ አድማሱን ሳያሰፋ በፊትም ቅራኔውን በሽምግልና  ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረቶችም ተደርገዋል። አንዳቸውም ግን አልተሳኩም።

ዩናይትድ ስቴትስ፦ «ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ» በዚህ ሳምንትም ጥሪ አስተላልፋለች። ባሳለፍነው ሐሙስ፦ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ወሳኝ ባሉት በዚህ ወቅት በምሥራቅ አፍሪቃ የአሜሪካ ላዩ መልእክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሊልኩ መወሰናቸው ተሰምቷል። ከሰሞኑ ደግሞ ራሱን «የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሠራዊት» ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት አሸባሪው ሸኔ የሚለው ቡድን ከህወሃት ጋር በወታደራዊ ትብብር አብሮ ለመስራት መስማማቱን ሲናገር፤ ሕወሃት ደግሞ ቡድኑን ጨምሮ «በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም አላቸው ካላቸው ቡድኖች ጋር» እየተወያየ መሆኑን ዐስታውቋል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ አሁን የገባችበትን መጠነ ሰፊ ጦርነት የመሸከም አቅሙ ይኖራት ይኾን? የዩናይትድ ስቴትስ የተደራደሩ ጥሪስ ምን ምላሽ ይኖረው ይኾን? «አሳሳቢው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ»፦ የእንወያይ መሰናዶዋችን የሚያጠነጥንበት ርእሰ ጉዳይ ነው።  በውይይቱ 3 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው። 

ሙሉ ውይይቱን ከድምፅ ማእቀፉ ማድመጥ ይቻላል