1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 አሳሳቢው  ልውጥ የኮረና ተዋህሲ

ረቡዕ፣ ኅዳር 22 2014

በዓለም ዙሪያ ስጋትን የፈጠረ አዲስ ልውጥ የኮሮና ተዋህሲ መገኘቱን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ  «ኦሚክሮን» ሲል  የሰየመው ይህ አዲስ የኮሮና ተዋህሲ  ከዚህ በፊት በኮሮና ተይዘው  ያገገሙ  እና  በተሳካ ሁኔታ የተከተቡ ሰዎችንም ሊይዝ ይችላል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/43iHX
Symbolbild Corona Covid Variante Omicron B.1.1.529
ምስል DADO RUVIC/REUTERS

አሳሳቢው ልውጥ የኮረና ተዋህሲ

የዓለም ህዝብ ከኮሮና ክትባት በኋላ ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ በመጠባበቅ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የዓለም የጤና ድርጅት በ15ኛው የግሪክ ፊደል  «ኦሚክሮን» ብሎ የሰየመው አዲስ ልውጥ የኮሮና ተዋህሲ መገኘቱን ያለፈው ሳምንት መጨረሻ  ይፋ አድርጓል። በሳይንሳዊ አጠራሩ  B.1.1.529 በመባል የሚጠራው ይህ  አዲስ የኮሮና ተዋህሲ ከዚህ በፊት ከነበሩት የመተላለፍ ባህሪው  ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያዎች በመግለፅ ላይ ናቸው ። በዚህ የተነሳ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ይህንን አዲስ ተዋህሲ  አሳሳቢ ሲል መመደቡን የድርጅቱ የቴክኒክ አማካሪ ቡድን አባል የሆኑት ዶክተር ማርያ ቫን ከርሆቭ ገልፀዋል።
«ከደቡብ አፍሪካ ባገኘነው የተለዬ  መረጃ መሰረት፤ ይህ ልውጥ ተዋህሲ አሳሳቢ ተብሎ መመደብ እንዳለበት ባለሙያዎች ዓለም አቀፉን የጤና ድርጅት መክረዋል። እናም ዛሬ  «ኦሚክሮን» የሚባለው « B 1.1. 529»  ልውጥ አሳሳቢ መሆኑን እናሳውቃለን። ስለዚህ ኦሚክሮን « B 1.1. 529 አሳሳቢ ልውጥ ነው።ምክንያቱም አንዳንድ አሳሳቢ ባህሪያት አሉት።» 
ስለ አዲሱ የኮሮና ተዋህሲ  አመጣጥ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ተመራማሪዎች የተለያዩ መላ ምቶችን ያስቀመጡ ሲሆን፤ ከነዚህም አንዱ ተዋህሲው የተለወጠው በኤች አይ ቪ/ኤድስ  ምክንያት ከተዳከመ የመከላከል አቅም የመጣ ሊሆን እንደሚችል በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሥነ-ህይወት ተመራማሪው  ፕሮፌሰር ፍራንሷ ባሎክስ ጠቁመዋል።ነገር ግን ይህ ጉዳይ  በመላምት ደረጃ የተቀመጠ እንጅ የተረጋገጠ አለመሆኑን ባለሙያው አመልክተዋል።  B.1.1.529 ልውጥ ተዋህሲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በጎርጎሪያኑ ህዳር 11 ቀን 2021 ዓ/ም በቦትስዋና ሲሆን፤ቆይቶም በአጎራባቿ ሀገር ደቡብ አፍሪካ በተለይም በተለይም  በጋውቴንግ አውራጃ  እንዲሁም በጆሃንስበርግ እና በፕሪቶሪያን ከተሞች መገኘቱ ታውቋል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በደቡብ አፍሪቃ ጋውቴንግ ግዛት ውስጥ በኮቪድ-19 ከተያዙት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በአዲሱ ልውጥ ተዋህሲ የተጠቁ ሊሆኑ ይችላሉ።በሀገሪቱ ስምንት ግዛቶች ሳይዛመት እንዳልቀረ  የሚነገርለት ይህ ተዋህሲ የደቡብ አፍሪቃ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ጆሴፍ ፋላ  እንደሚሉት በሰፊው ይዛመታል የሚል  ስጋት አሳድሯል።
«ካለፉት 21 ወራት ካየነው ልምድ በመነሳት  አካሄዱንና እንቅስቃሴውን መተንበይ እንችላለን ። እንደተናገርኩት በተለይ ልክ «ዴልታ» በጋውቴንግ በጀመረበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ፤ ሰዎች የበለጠ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት  በትም ቦታ ሊከሰት እንደሚችል  የበለጠ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።" 
ይህ  አሳሳቢ ተዋህሲ በአጭር  ጊዜ  ውስጥ ከደቡብ አፍሪቃ ውጭ  ጀርመንን ጨምሮ  በተለያዩ  20  የዓለም  ሀገሮች  በመከሰቱ  በርካታ ሀገራት ከደቡበ አፍሪቃና ከአጎራባች ሀገራት ለሚመጡ መመንገደኞች  ገደብ ጥለዋል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት  አዲሱ ተዋህሲ ከተላላፊነቱ በተጨማሪ አሳሳቢ የሆነበት  ሌላው ምክንያት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ ራሱን የሚለዋውጥ መሆኑ ነው።በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናትም ተዋህሲው «ስፔክ» ፕሮቲን በተሰኘው የተዋህሲው ዘረ-መል ውስጥ 32 ጊዜ ራሱን መለዋወጡን ተመራማሪዎች  ገልፀዋል። ይህም ስምንት ለውጦችን ካሳየው እና  በተላላፊ ነቱ  ከፍተኛ ነው ከተባለው ከዴልታ ልውጥ ተዋህሲ  ጋር ሲነፃፀር  ልዩነቱ ሰፊ  ነው ።
የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት «ስፔክ ፕሮቲን» ውስጥ በተደጋጋሚ የታየው ራስን የመለዋወጥ ባህሪ አዲሱ ተዋህሲ  ምን ያህል አደገኛ ነው  የሚለውን በአሁኑ ወቅት በትክክል ማረጋገጥ ባይቻልም፣ ይህ ባህሪው  የሰውነታችን  በሽታ ተከላካይ ሥርዓት ተዋህሲውን እንዳይዋጋ ሊያደርገው   ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። በዚህ የተነሳ  «ኦሚክሮን» በክትባትም ይሁን በተፈጥሮ ከሚገኝ በሽታ የመከላከል ምላሽ ሊያመልጥ እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች መኖራቸውን ባለሙያዎች ገልፀዋል። ያ ማለት ከዚህ በፊት በኮቪድ-19  የተያዙ እና ያገገሙ ሰዎችን እንዲሁም በተሟላ ሁኔታ ክትባቱን የወሰዱ  ሰዎችን ሊያጠቃ እንደሚችል  በጀርመን የተዋህሲያን ተመራማሪ የሆኑት  ወልፍጋንግ ፕራይዘር ገልፀዋል።
«ደህና፣ ይህ« B 11 529 »ተዋህሲ በከፍተኛ ቁጥር ራሱን የመለዋወጥ ባህሪ አለው። ምንም እንኳ የታካሚ ማዕከላትን በመመልከት እንዲሁም በመስክ ጥናት ስለ ተዋህሲው ብዙ ማስረጃ ባይኖረንም፤በቤተ-ሙከራ ጥናቶች በተገኘው ራሱን የመለዋወጥ ባህሪ እና ከሌሎች ልውጥ ተዋህሲያን ባህሪያት በመነሳት መተንበይ እንችላለን።ስለዚህ ይህ ተዋህሲ ከሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት ሊያመልጥ ይችላል የሚል ስጋትም አለ። ያ ማለት ታመው ያገገሙ ሰዎችን ሊያጠቃ ይችላል። በተሳካ ሁኔታ የተከተቡ ሰዎችንም ሊይዝ ይችላል።እንዲሁም በቀላሉ የሚተላለፍ ይመስላል።»
ኦስትሪያ ቪየና በሚገኘው የሞለኪውላር ባዮቴክኖሎጂ ተቋም ባለሙያ እና በአዳዲስ ልውጥ የኮሮና ተዋህሲያን ላይ ምርምር የሚያደርጉት ዶ / ር ኡልሪክ ኢሊንግ  በበኩላቸው አዲሱ ተዋህሲ  ከዴልታ በ 500% የበለጠ ተላላፊ ሊሆን ይችላል የሚል  ግምት መኖሩን ገልፀዋል ።ያ በመሆኑ «ኦሚክሮን »  ቀደም  ካሉት ተዋህሲያን  በበሽታ ደረጃ  የበለጠ ከባድ ባይሆን እንኳ፤  በፍጥነት በመሰራጨት  ባህሪው የሀገራትን ብሄራዊ የጤና ስርዓት ጫና ውስጥ ሊከት እንደሚችል ተመራማሪው ገልፀዋል። 
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ተመራማሪዎች ቀደም ሲል በተገኙት «ቤታ»  እና «ዴልታ» በተባሉ ልውጥ የኮሮና ተዋህሲያን ላይ  ምርምሮችን  ያደረጉ ሲሆን፤በአዲሱ «ኦሚክሮን» ላይም ባህሪያቱን በውል ለመረዳት ተመሳሳይ የምርምር ጥረቶች ተጀምረዋል።በመሆኑም በእነዚህ ምርምሮች የተጠናከረ ሳይንሳዊ መረጃ  እስኪቀርብ ድረስ ቀደም ሲል በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የተቀመጡ የመከላከያ መንገዶች አጠናክሮ መቀጠል ተጋላጭነትን መቀነስ መፍትሄ መሆኑን ዶክተር ማርያ ቫን ከርሆቭ አሳስበዋል።
«ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሱን። ማንኛውንም መረጃ ይፋ እናደርጋለን። ነገር ግን እራሳችሁንና  እና የምትወዷቸውን ሰዎች ለመጠበቅ ልታደርጓቸው የምትችሏቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።ሰዎች እንደሚጨነቁ እንረዳለን።መልካሙ ነገር እነዚህን ተዋህሲያን ለመለየት  በዓለም ዙሪያ የክትትል ስርዓቶች አሉን።ይህ ልውጥ ተዋህሲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተገኘ ቢሆንም፤ የሳይንስ ሊቃውንት  እርምጃ መውሰድ  እንድንችል ጥናቶችንና መረጃዎችን  እያጋሩን  ነው። እንደ ግለሰብ በጣም አስፈላጊው ነገር ተጋላጭነትን መቀነስ ነው።»
በሌላ በኩል የአዲሱን ተዋህሲ ስርጭቱን መግታት ባይቻልም መቀነስ ይቻላል በሚል የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከሰባት ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚደረገውን ጉዞ ለጊዜው ለማቆም ያለፈው አርብ ተስማምተዋል።አሜሪካም ከዜጎቿ በስተቀር ከነዚህ የአፍሪቃ ሀገራት የሚመጡ መንገደኞችን ከልክላለች። ነገር ግን ቀድሞውኑ ኢኮኖሚያቸው በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙት የአፍሪቃ ሀገራት ይህ መሰሉ ውሳኔ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ በመሆኑ፤ከዚህ ይልቅ ለአፍሪቃ ሀገራት ፍትሃዊ የክትባት አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ የተሻለ መፍትሄ መሆኑን  የሚያሳስቡም በርካቶች ናቸው።

Covid-19 - Neue COVID-19-Variante Omicron
ምስል Pavlo Gonchar/Zumapress/picture alliance
SARS-CoV-2 Variante Omicron und COVID-19 Impfstoffe
ምስል Andre M. Chang/Zuma/picture alliance

ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ