1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት በድሬደዋ 

ማክሰኞ፣ መስከረም 18 2014

የኮቪድ 19 ዴልታ ዝርያ መኖሩን ያረጋገጠው የጤና ሚንስቴር መረጃ ይፋ ከሆነበት ጊዜ በተቆጠሩ አጭር ግዜያት ቫይረሱ በፍጥነት ከተስፋፋባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ድሬደዋ አንዷ ናት፡፡ የመስተዳድሩ ጤና ቢሮ የቅርብ የምርመራ ውጤት መረጃዎችን መሰረት አድርጎ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/40ycO
Äthiopien Dire Dawa
ምስል Mesay Tekelu/DW

አሳሳቢዉ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት በድሬደዋ 

የኮቪድ 19 ዴልታ ዝርያ መኖሩን ያረጋገጠው የጤና ሚንስቴር መረጃ ይፋ ከሆነበት ጊዜ በተቆጠሩ አጭር ግዜያት ቫይረሱ በፍጥነት ከተስፋፋባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ድሬደዋ አንዷ ናት፡፡ የመስተዳድሩ ጤና ቢሮ የቅርብ የምርመራ ውጤት መረጃዎችን መሰረት አድርጎ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሁሉም አካላት ርብርብ መፍትሄ ያልተበጀለት እንደሆን የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብሏል፡፡  
የደሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ሰሞኑን በሰጡት መረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮቪድ 19 ስርጭት በአስተዳደሩ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ወንደሰን ታዪ በአስተዳደሩ የኮቪድ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት አንዱ የሆነው የሳቢያን ጠቅላላ ሆስፒታል ምክትል ዳይሬክተር እና የኮቪድ ህክምና ኮርነር አስተባባሪ ናቸው፡፡ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው በሽታው ከሚገኝባቸው ሰዎች ከሃምሳ በመቶ በላይ ወደ ፅኑ ህክምና የሚገቡ መሆናቸውንና ህፃናት ጭምር በበሽታው እየተያዙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሆስፒታሉ የድንገተኛ እና ፅኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ነርስ አበበ ርዳው በበኩላቸው ከቁጥሩ መጨመር ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች ማጋጠማቸውን ተናግረዋል፡፡
በኮቪድ 19 ተይዘው በፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች መጠኑ ይለያይ እንጂ ኦክስጅን ያስፈልጋቸዋል ሌሎች መድሀኒቶችም እንዲሁ፡፡ አሁን ባለው አሰራር ታካሚው የህክምና ወጭውን መሸፈን ይጠበቅበታል ፡፡ ይሄ ደግሞ የበርካቶችን አቅም የሚፈትን ነው፡፡ እናም አስቀድሞ መከላከሉ ላይ ማተኮር ይገባል የሚል ምክር ለግሰዋል - ዶ/ር ወንደሰን፡፡
የችግሩ አሳሳቢነት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ይሂድ እንጂ በህብረተሰቡ ዘንድ ይህ ነው የሚያስብል ለውጥ አይታይም ፡፡ ዶ/ር ወንደሰን ህብረተሰቡ የኮቪድ ስርጭትን ለመከላከል ሊተገብራቸው የሚገቡ የጥንቃቄ መርሆችን የረሳበት ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል - መዘናጋቱን ሲገልፁ፡፡
የመስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም ህብረተሰቡ ወደ ጤና ተቋም መጥቶ ምርምራ ማድረግ እንደማይፈልግ ጠቅሰው በተለያየ መልኩ በሚደረገው ምርመራ የስርጭቱን መስፋፋት የሚያሳይ መረጃ መኖሩን ተናግረዋል፡፡በከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ ነው ያሉት ህብረተሰብ በበሽታው ከፍተኛ ዋጋ ከመክፈሉ አስቀድሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
በድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ባለሙያ የሆኑት አቶ ትግስቱ የማነ በችግሩ መከላከል ላይ የሚታየው መዘናጋት ህብረተሰቡ  ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአስተዳደር ደረጃ ነው ብለዋል ፡፡
የችግሩ አሳሳቢነት በተለያየ መልኩ የሚታይ ቢሆንም ለመፍትሄው የሚደረግ ተጨባጭ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የማይታይበትን የመከላከል ስራ ለማንቀሳቀስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ውይይት ተካሂዷል፡፡የፀጥታ አካላት ፣ የመንግስት ተቋማት የእምነት ተቋማት እና ሌሎችም በዚሁ መድረክ በጋራ ስለሚሰሩበት ሁኔታ ተነጋግረዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የድሬደዋ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ሊቀብርሀናት ቀለመወርቅ ቢምረው ኮቪድ ቀደም ሲል በእምነት ተቋማት እና በህዝቡ ላይ ያደረሰው አይነት ጫና እንዳይደገም ህዝባችንን እናስተምራለን ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ የኮቪድ ስርጭትን ለመከላከል በተዘጋጀው መመርያ የተቀመጡ አስገገገዳጅ ሁኔታዎች በአግባቡ አለመተግበር ለሚታየው መዘናጋት መባባስ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በዚህ ረገድ ማስተማርን ማስቀደም ተገቢ ነው ያለው ፖሊስ ግንዛቤ ተፈጥሮ ለውጥ ካልመጣ ርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
ከስድስት መቶ ሺህ ከፍ ሊል እንደሚችል ከሚገመተው የአስተዳደሩ ህዝብ አንድ በመቶ የሚሆነው ብቻ ክትባት ማግኘቱን የጤና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል፡፡  
መሳይ ተክሉ 
አዜብ ታደሰ 
 

Äthiopien Dire Dawa
ምስል Mesay Tekelu/DW