1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አምነስቲ የሐጫሉ ግድያ ተጣርቶ ገዳዮች ለፍትኅ እንዲቀርቡ ጠየቀ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2012

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጣርቶ ገዳዮች ለፍትኅ እንዲቀርቡ ጠየቀ። በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ ተቃውሞ እንደነበር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አረጋግጧል። “ተቃዋሚዎች ቢበተኑም እንዲህ አይነት ተቃውሞዎች ሊደጋገሙ ይችላሉ” ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ከአካባቢው እንዲርቁ አሳስቧል። 

https://p.dw.com/p/3ebCW
Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ምስል Odaa Award

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ “በአፋጣኝ፣ በጥንቃቄ፣ በሚዛናዊነት እና ገለልተኝነት” መርምረው ተጠያቂዎችን ለፍትኅ እንዲያቀርቡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን “የሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ፍትኅ ሊያገኝ ይገባል” ብለዋል። ምክትል ዳይሬክተሯ ድምፃዊው በኢትዮጵያ ከአምስት አመታት በፊት በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጀምሮ በሙዚቃ ሥራዎቹ ፖለቲካዊ መሻሻያ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የነበረውን የመሪነት ሚና አስታውሰዋል።

ሳራ ጃክሰን “ባለሥልጣናቱ ግድያውን መመርመር ጀምረዋል። ምርመራው አፋጣኝ፣ በጥንቃቄ የሚከናወን ሚዛናዊ እና ገለልተኛ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። በግድያው የሚጠረጠሩትን ለፍትኃዊ ዳኝነት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል። ከግድያው በኋላ አዲስ አበባ ጸጥ ረጭ ብላለች። የሕዝብ መጓጓዣዎች በተለምዶ ላዳ ተብለው ከሚጠሩ ተሽከርካሪዎች በቀር አገልግሎት አቁመዋል። በዋና ከተማዋ የጸጥታ ጥበቃ እጅግ መጠናከሩን ዶይቼ ቬለ ለመረዳት ችሏል። ሱቆች፣ መደብሮች፣ ምግብ ቤቶች የሚሰጡት ግልጋሎት እጅግ ተወስኗል። 

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ ተቃውሞ እንደነበር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለዜጎቹ በሰጠው የጉዞ ማስጠንቀቂያ አረጋግጧል። “ተቃዋሚዎች ቢበተኑም እንዲህ አይነት ተቃውሞዎች ሊደጋገሙ ይችላሉ” ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ከአካባቢው እንዲርቁ አሳስቧል። 

Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ምስል Odaa Award

“የጥይት ተኩስን ጨምሮ የአሜሪካ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ስለ ተቃውሞ እና አለመረጋጋት የደረሱትን ሪፖርቶች እየተከታተለ ነው። ኹከት መቀስቀሱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ በከተማዋ ፖሊስ ቢሰማራም ኹኔታው ተለዋዋጭ ነው” ሲል አስጠንቅቋል። የብሪታኒያ ኤምባሲም በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች እንዲጠነቀቁ ባሳሰበበት መግለጫ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መጠነ ሰፊ ተቃውሞ መኖሩን አረጋግጧል። መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለሰራተኞቻቸው የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ሐጫሉ ሁንዴሳ ትናንት ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልተገለጸ ታጣቂዎች ከተገደለ በኋላ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በሐረር እና በድሬዳዋ ብርቱ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ማክሰኞ ጠዋት ጀምሮ በመላ አገሪቱ የኢንተርኔት ግልጋሎት ተቋርጧል። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ለሰዓታት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው ኢንተርኔት ሥራ ጀምሮ ነበር። ዘግየት ብሎ እንደገና መቋረጡን ዶይቼ ቬለ ለማረጋገጥ ችሏል።  

የኢንተርኔት አገልግሎት አሰጣጥን የሚከታተለው ኔትብሎክስ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ተዘግቷል። በመረጃው መሠረት በመደበኛ እና በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚቀርበው ግልጋሎት ተቋርጧል። ተቋሙ እንዳለው ይኸ ከዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ግልጋሎት መቆራረጥም ሆነ ከቴክኒካዊ ዕክል ጋር የተገናኘ አይደለም። ማክሰኞ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት ግንኙነት 1% እና 2% በመቶ ብቻ የተወሰነ ነው። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን የኢንተርኔት አገልግሎት ተመልሶ ሥራ እንዲጀምር ዛሬ ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል። “ባለሥልጣናቱ በመላ አገሪቱ የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት መልሰው ሥራ በማስጀመር ሰዎች መረጃ እንዲያገኙ እና በነፃነት ለሙዚቀኛው ሐዘናቸውን እንዲገልጹ ሊፈቅዱ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።