1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሜሪካኖች ሲወጡ፣ ታሊባኖች ይገቡ

ሰኞ፣ ሐምሌ 5 2013

የአሜሪካና የተባባሪዎችዋ ሐገራት ምርጥ ጦር  እኒያን በየጉጥ ስርጓጉጡ የተወሸቁ ከነብስ ወከፍ ጠመንጃ ሌላ፣ ሌላ ያልታጠቁ፣ ከዘመናዊ  ወታደራዊ ስልትና ሙያ የማይተዋወቁ ሸማቂዎችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ጊዜ ይወስድበታል ብሎ ያሰበ የዚያችን ጉደኛ ሐገር ሕዝብ የጉድ ታሪክን ጠንቅቆ የሚያዉቅ ብቻ ነበር።ኢምንት።

https://p.dw.com/p/3wO7z
Afghanistan US-Soldaten
ምስል AFP/T. Watkins

ታሊባን ከስልጣን ወረደ፣ ታሊባን አሜሪካ ከምትመራዉ ዓለም ጋር 20 ዓመት ተዋጋ፣ ማን አሸነፈ?

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ500 ዓመት እስከ 329፣ ከባቢሎኑ ዳርዮስ እስከ ሜቅዶኒያዉ አሌክሳንደር ታላቁ የነበሩ የዉጪ ኃይላት በኃይል ወርረዉ፣ በኃይል ተገድደዉ ወጥተዉባታል። አፍቃኒስታል። ከ11ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 13ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ከመሐሙድ ጋዛኒ እስከ ጌንጊስ ኻሕን ተፈራርቀዉባታል።ብሪታኒያዎች ከ1838-(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እስከ 1842፣ ከ1878-እስከ 1880፣ ከ1919 እስከ 1921 እየወረሩ፣ ገድለዉ፣ አጋድለዉ፣ በተራቸዉ እየተገደሉ ተባርረዉባታል።በ1979 ተራዉ የሶቭየት ሕብረቶች ነበር።10 ዓመት ተዋጉ፣ ብዙ ሰዉ ጨረሹ፣ግን ተሸነፉ። እና ጓዛቸዉን ጠቅልለዉ ዉልቅ አሉ።1989። ግዙፏ፣ የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ድል አድርጊያዋ፣ ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር በነበረችበት ብዙም አልቆየች።ተፈረካከሰች።የታሪክ አጥኚዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞች የሚሉ፣የሚከራከሩበት ብዙ ጉዳይ አለ።የአሜሪካና የአፍቃኒስታን አጭር ታሪክ ግን አሜሪካ ዓለምን አስከትላ እንደ ብዙ ቀዳሚዎችዋ ሁሉ አፍቃኒስታንን ወረረች፣ 20 ዓመት ተዋጋች፣ አዋጋች፣ዘንድሮ ጓዟን ጠቅልላ ወጣች።

 የቢቢሲዋ ዋና አለም አቀፍ ዘጋቢ ሊዝ ዱሴት ያኔ ወጣት ነበረች።1989።ክረምቱን ካቡል ነበረች።የካቡል መዳረሻን ካየር ከምድር በሚደልቀዉ ቦምብ፣ መድፍ፣መትረየስ እየተገነደሰ በሚወድቀዉ በረዶ መሐል የሶቭየት ሕብረት ጦር ጓዙን ለመጠቅለል፣ የምዕራባዉያን ሐገራት ኤምባሲዎች በራቸዉን ለመዝጋት ሲጣደፉ ታዝባለች።ዱሴት ባለፈዉ ሳምንት ከያኔ ትዝታዋ ቀንጨብ አርጋ ፃፈች።በፅሁፍዋ መሐል በካቡል የብሪታንያ አምባሳደር አፍቃኒስታን ለሚገኙ የሐገራቸዉ ዜጎች ያሰራጩትን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለጥፋለች። «መደበኛ በረራ ሳይቆም አፍቃኒስታንን ለቅቃቸሁ እንድትወጡ ልመክራችሁ አገደዳለሁ» ትላለች የዘመን ሒደት ያወየባት የታይፕ ፅሁፍ።ለንደንም ዋሽግተንም ኤምባሲዎቻቸዉን ሲዘጉ «ባጭር ጊዜ እንደሚመለሱ (እንደሚከፍቱ) ቃል ገብተዉ ነበር» ትላለች ጋዜጠኛዋ።ይሁንና ቀጠለች  አፍቃኒስታንን የወረረዉ ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር በ2001 ታሊባንን ከስልጣን እስኪያስወግድ ድረስ ቆስላዎቻቸዉ እንደተዘጉ ነበር።»

Weltspiegel | Washington, USA | President Biden bekräftigt US Truppenabzug aus Afghanistan
ምስል Tom Brenner/imago images

ጥቅም እንጂ ቃል የእምነት ዕዳ ነዉ-ብሎ ፖለቲካ-ዲፕሎማሲ በተለይ ለምዕራቦች የለም።ወይም ምናልባት «አጭር ጊዜ» ማለት የሶቭየት ሕብረት ጦር ተሰናብቶ፤ ጦሩ የሚደግፋቸዉ የአፍቃን ኃይሎች ተሸንፈዉ፣ እነ ናጂ ቡላሕ ተገድለዉ፣ በአሜሪካ-ፓኪስታን-ሳዑዲ አረቢያ-ግብፅ/እስራኤሎች ይረዱ የነበሩት እነ ሙላሕ ዑመር ነግሰዉ፣ እነ መስዑድ  ተገድለዉ፣ ሶቭየት ሕብረት ተፈረካክሳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ተሸብራ--አፍቃኒስታንን ወርራ--- ማለት ቢሆንስ።ሆነም አልሆነ የወረራዉ ምክንያት የያኔዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እንዳሉት መስከረም 11፣ 2001 ኒዮርክና ዋሽግተንን ያሸበሩና 3ሺሕ ግድም ሰዉ ያስገደሉ የአልቃዳ መሪዎችን ለማጥፋት፣ የታሊባን ተባባሪዎቻቸዉን የመዋጋት አቅም ሰብሮ ለመጣል ነዉ።ጆርጅ ቡሽ ጥቅምት 7፣ 2001።

«በእኔ ትዕዛዝ፣ የአሜሪካ ጦር አፍቃኒስታን ዉስጥ የሚገኙ የአልቃኢዳ ማሰልጠኛ ጣቢያዎችንና የታሊባን ሥርዓትን ወታደራዊ ተቋማት መደብደብ ጀምሯል።ይሕ በጥንቃቄ የተመረጡ ኢላማዎችን የመምታቱ ዘመቻ፣ አፍቃኒስታን የአሸባሪዎች ዕዝ ማዕከል መሆንዋን ለማጨናገፍና የታሊባን ሥርዓትን ወታደራዊ አቅም ለመስበር ነዉ።»

የቡሽን መግለጫ እንዳለ ያልተቀበለ አሜሪካዊ ፖለቲከኛ፣ ምሁር፣ጋዜጠኛ፣ወታደር ከነበረ እሱ አልተሰማም።«የተመረጡ» ያዉም «በጥንቃቄ» ኢላማዎችን ይመታል የተባለዉ የአሜሪካ ጦር ወደ ሙሉ ወረራ፣ ዉስን ጥቃቱ ወደ ለየለየለት ጦርነት ለመሸጋገር ጊዜ አልፈጀበትም።ዩናይትድ ስቴትስን ከልቡ ደግፎ፣ ኔቶን በመሳሰሉ ማሕበራት በመደራጀቱ ፈቅዶ፣ ዋሽግተኖችን ፈርቶ፣በጥቅም ተደልሎ ወይም በሌላ ምክንያት ወረራዉን ያልደገፈ፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በወረራዉ ያልተሳተፈ የዓለም መንግስትም አልነበረም።

Russland Afghanistan l PK der Anführer der Taliban-Bewegung in Moskau
ምስል Tatyana Makeyeva/REUTERS

የዩናይትድ ስቴትስ የረጅም ጊዜ ጠላቶች የሚባሉት ከቴሕራን እስከ ትሪፖሊ፣ ከሞስኮ እስከ ቤጂንግ የነበሩና ያሉ ገዢዎች ሳይቀሩ ባንቆረቆሩት መረጃ፣በሰጡት የዓየር ክልልና ወታደራዊ ማዕከል የታገዘዉ የአሜሪካና የተባባሪዎችዋ ሐገራት ምርጥ ጦር  እኒያን በየጉጥ ስርጓጉጡ የተወሸቁ ከነብስ ወከፍ ጠመንጃ ሌላ፣ ሌላ ያልታጠቁ፣ ከዘመናዊ  ወታደራዊ ስልትና ሙያ የማይተዋወቁ ሸማቂዎችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ጊዜ ይወስድበታል ብሎ ያሰበ የዚያችን ጉደኛ ሐገር ሕዝብ የጉድ ታሪክን ጠንቅቆ የሚያዉቅ ብቻ ነበር።ኢምንት።

ልክ እንደ ሶቭየቶች ሁሉ ዋና ማዘዢያ ጣቢያዉን ከካቡል 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ ባግራም አዉሮፕላን ማረፊያ  ያደረገዉ አሜሪካ መራሹ ጦር ከራስዋ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ሉትዌንያ፣ ከብሪታንያ እስከ አልባኒያ ያሉ 30 ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ያዘመተዉን በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ወታደሮችን አዋግቷል።ከ400 ሺሕ የሚልጥ የአፍቃኒስታን መንግስት ወታደሮች፣ሚሊሺያዎችንና ወታደራዊ አማካሪዎችን መርቷል።ከኑክሌር ቦምብ በስተቀር የሰዉ ልጅ በእስካሁን ዕዉቀቱ ባመረተዉ ጦር መሳሪያ የቶራ ቦራ ተራራ-ጉድባዎችን፣ የማዛር ኢ ሸሪፍ፣ የኮንዱዝ፣ የታሪን ኮዉት፣የካንዳሐር ሜዳ፣ ሸለቆ፣ፈፋ-ጉብታ፣ ከተሞችን አጋይቷል።ከ50 ሺሕ በላይ የታሊባን፣ 2 ሺሕ ያሕል የአልቃኢዳ 3 ሺሕ የISIL ታጣቂዎችን ገድሏል።እነ ኹዋንታናሞን ወደ ዘመኑ ዓለም ዕዉቅ የሰዎች ማሰቃየነት ለዉጧል።

የዚያኑ ያክል ከ3ሺሕ የሚበልጡ የኔቶ አባል ሐገራት ወታደሮችን፣ 4ሺሕ የጦር ኮንትራት ሠራተኞችን፣ 66 ሺሕ የአፍቃኒስታን መንግስትና ተባባሪ ሚሊሺያዎችን ሕይወት ገብሯል።ለ20 ዓመት ሶስት ወር በቀረዉ ጦርነት ካንዱ ወይም ከሌላዉ ወግነዉ የማይዋጉ፣ በትንሽ ግምት 50 ሺሕ ሰላማዊ ሰዎች የተፋላሚ ኃይላት ቦምብ-ሚሳዬል-ጥይት ሲሳይ ሆነዋል።አብዛኞቹ ሮጠዉ ማምለጥ፣ ተሸሽገዉ መደበቅ የማይችሉ ልጆች፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ነበሩ።አፍቃኒስታን ለዝንተ-ዓለም እንደለመደችዉ ባለፉት 19 ዓመት ከዘጠኝ ወር ብቻ የ213ሺሕ ሰዉ አስከሬን ተለቅሞባታል።ከ3 እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሞባታል።ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ግን በቀደም ዓላማችን ግቡን መትቷል አሉ። «ሚያዚያ ላይ እንዳልኩት ዩናይትድ ስቴትስ አፍቃኒስታን ዉስጥ ለማድረግ ያቀድነዉን አድርጋለች።መስከረም 11 ያጠቁንን አሸባሪዎች ለማግኘትና ኦስማ ቢን ላደንን ለፍርድ ለማቅረብ ነዉ።እና ዩናይትድ ስቴትስን ማጥቃታቸዉን ለመቀጠል የሚያስቡ አሸባሪዎች አፍቃኒስታን ዉስጥ መደራጃ ሠፈር እንዳያገኙ ማድረግ ነዉ።እነዚሕ አላማዎቻችን ከግብ አድርሰናል።የዘመትነዉ ለዚሕ ነዉ።»

ኦሳማ ቢን ላደን ለፍርድ የቀረቡበትን ሥፍራና ጊዜ አናዉቅም።ግን ተገድለዋል።የተገደሉት ደግሞ አፍቃኒስታን ዉስጥ በተደረገ ዉጊያ ሳይሆን ፓኪስታን በዘመተ የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ ጦር የደፈጣ ጥቃት ነዉ።የታሊባኑ መሪ ሙላሕ ዑመር መሐመድም በተፈጥሮ በሽታ መሞታቸዉ ተሰምቷል።የ2001ዱ ወረራ የባላይ መሪና አስተባባሪ መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስፌልድም በቀደም ሞቱ።ያኔ እንደ ሴናተር ከራምስ ፌልድ፣ ከፍ ካለም ከቡሽ የሚሰጣቸዉን ገለፃና ማብራሪያ ይከታተሉ የነበሩት ጆ ባይደን ዛሬ «ተሳክቷል» የሚሉት ዓላማ ቢን ላደንን መግደል ከነበረ 213 ሺሕ ሰዉ ማለቅ ነበረበት? ለዘመን ሒደት የሚተዉ ጥያቄ።እሳቸዉ ግን እኛ ሐገር ለመገንባት አፍቃኒስታን አልዘመትንም አሉ።

Afghanistan Angriff auf amerikanische Universität in Kabul
ምስል Reuters/M. Ismail

«አፍቃኒስታን የዘመትነዉ ሐገር ለመገንባት አይደለም።ሐገራቸዉን እንዴት መምራት እንዳለባቸዉ መወሰን የአፍቃኒስታን ሕዝብ መብትና ኃላፊነት ነዉ።ከኔቶ ሸሪኮቻችንና ከተባባሪዎቻችን ጋር በመሆን ወደ 3መቶ ሺሕ የሚጠጋ የአፍቃኒስታን የፀጥታ ኃይላትን አሰልጥነናል።ከዚሕ በተጨማሪ ባለፉት 20 ዓመታት ከ100 ሺሕ የሚበልጡ የአፍቃኒስታን የመከላከያ አባላት ሰልጥነዋል።የትኛዉም ዘመናይ ወታደር የሚያስፈልገዉን ሁሉንም ጦር መሳሪያ (አስታጥቀናል)።የረቀቀ መሳሪያም አቅርበናል።»

ዩናይትድ ስቴትስን ተከትለዉ አፍቃኒስታን ዉስጥ ጦራቸዉን ካሰፈሩ ሐገራት ብዙዎቹ አሜሪካኖችን ቀድመዉ ጦራቸዉን ማስወጣቱን አጠናቅዋል።ባንድ ወቅት ከዩናይትድ ስቴትስና ከብሪታንያ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ወታደር አፍቃኒስታን አስፍራ የነበረችዉ ጀርመንም የመጨረሻ ወታደሮቿን ከአፍቃኒስታን ካስወጣች ሁለተኛ ሳምንቷን ይዛለች።የጀርመን ጦር አፍቃኒስታን በነበረበት ወቅት ለጦሩና ጦሩ ለሚመራዉ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ባስተርጓሚነት፣ በዘጋቢነት፣ በመረጃ አቀባይነት ያገለግሉ የነበሩትን የአፍቃኒስታን ተወላጆችን ግን እነሱ እንደሚሉት ጦሩ «ለታሊባን ጥይት» አጋልጧቸዋል።በመቶ የሚቆጠሩት የቀድሞ ሠራተኞች ለጀርመን ባለስልጣናት በተደጋጋሚ አቤት ቢሉም እስካሁን ያገኙት መልስ የለም።

ዴር ሽፒግል የተባለዉ የጀርመን መፅሔት የኦን ላይን እትም ካነጋገራቸዉ አስተርጓሚዎች አንዱ ጃዉድ ሱልጣን የጀርመን ጦር ማዛኢ-ሸሪፍ ከሚገኘዉ ሠፈሩ ነቅሎ ሲወጣ ይታዘብ ነበር።«እናንት ጀርመኖች» አለ ጃዉድ ሽፒግል እንደጠቀሰዉ «27 ቶን የሚመዝን የማስታወሺያ ድንጋይ እና 22 ሺሕ ሊትር ቢራ ወደ ጀርመን ይዛችሁ ትሔዳላችሁ።» ቀጠለ ክፍት ብሎት።«በየመስኩ አብረዋችሁ የሰሩ ሰዎችን ግን ትጥሏቸዋላችሁ።»

ለአፍቃኖች፣ በጣሙን ታሊባንን ለሚቃወሙት የሐገሪቱ ዜጎች አሜሪካና ተባባሪዎችዋም ድፍን አፍቃኒስታንን ከ20 ዓመት በፊት ይገዛት ለነበረዉ ለታሊባን አስረክበዉ ወጡ ከማለት ሌላ፣ ሌላ ትርጉም ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።የአሜሪካና የተባባሪዎችዋ ሐገራት ጦር እግሩን የነቀለባቸዉን ስልታዊ አካባቢዎች ታሊባኖች ተራ በተራ እየተቆጣጠሩ ነዉ።በአፍቃኒስታን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ዴቦራሕ ላዮን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት የታሊባን ታጣቂዎች ካለፈዉ ግንቦት ወዲሕ ብቻ 50 አዉራጃዎችን ተቆጣጥረዋል።

«ካለፈዉ ግንቦት ጀምሮ ከ370 የአፍቃኒስታን አዉራጃዎች 50ዎቹን ታሊባን ተቆጣጥሯቸዋል።ታሊባን የተቆጣጠራቸዉ ብዙዎቹ አካባቢዎች የክፍለ ሐገር ርዕሠ-ከተሞች አጠገብ የሚገኙ ናቸዉ።ይህ የሚጠቁመዉ የዉጪ ኃይላት ሙሉ በሙሉ ሲወጡ ታሊባን ጠቃሚ አካባቢዎችን ጠቅልሎ ለመያዝ በሚያመቸዉ ሥፍራ መመሸጉን ነዉ።»

የታሊባን መሪዎች አላስተባበሉም።ማስተባበል አላስፈለጋቸዉምም።ሐኃምሌ 28 1915 የሔቲዉ ፕሬዝደንት ዤን ቫይብሩ ጉላዩሜ ሳም በወርሮ በሎች ተቀጥቅጠዉ ተገደሉ።የሔይቲ ዜጎችን በባርነት ለመፈንገል፣ የተፈጥሮ ሐብቷንም ለመመዝበር ለዓመታት ስትቋምጥ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ በማረጋጋት ስም ጦሯን አዘመተች።ትንሽ፣ደካማ፣ በሁከት ብጥብጥ የምትተራመሰዉን ሐገር ተቆጣጠረች።የአሜሪካ ጦር የሔይትን ባንኮች፣የማዕድን ጉርጓዶችና ሌሎች ተቋማትን እየመዘበረ፣ሐገሪቱን ለአሜሪካ ባሪያ ፈንጋዮች ከፈተ።የሔይቲ ፀጥታ አስከባሪ ያለዉን ጦር አሰለጠነ፤አስታጠቀም።የአሜሪካ ጦር በ1934 ለቅቆ ወጣ።«ሚሽን አኮፕሊሽድ።» እነሱ እንደሚሉት።አሜሪካ ፋሺስትና ኮሚንስትን ለመዋጋት አዉሮጳ፣ ኮሪያ፣ ቬትናም፣ አፍሪቃ፣ መካከለኛዉ ምሥራቅ፣ አፍቃኒስታንም ስትዘምት ሔይቲ በጥቂት መቶ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሆና ቁልቁል እየሰጠመች ነበር።ዘንድሮም ዘራፊ ወርሮ በሎች የሚፈነጩባት፣ ፕሬዝደንቷ ሳይቀር በመኖሪያ ቤታቸዉ የሚገድልባት ሐገር ናት።ዓለም ከቀዳሚዉ ከመማር ይልቅ ኃይለኞች እያወደሰ፣ እያሞገሰ፣ ዋሽግተኖች የሔይቲን ታሪክ አፍቃኒስታን ላይ ሲደግሙ እየደገፈ ባጓጉል ዉጤቱ ሊደነቅ አይገባም።

Deutschland NATO Stützpunkt Geilenkirchen
ምስል Getty Images/C. Koepsel

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ