1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማርኛን ከእንግሊዘኛ የመቀየጥ አባዜ ለምን?

ሐሙስ፣ መስከረም 14 2013

በዓለማችን የሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ ከሌላ ቋንቋ አዲስ ቃላትን ይዋሳሉ፤ በአንፃሩም ያዉሳሉ።  ይሁንና አንድ ቋንቋ ከሌላ ቋንቋ አንድ ቃልን ሲወርስ የቋንቋዉን ባህል ተከትሎ ሊሆን ይገባል ሲሉ የቋንቋ ጉዳይ ባለሞያዎች በአጽኖት ይመክራሉ።

https://p.dw.com/p/3ixo2
amharisch alphabet
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

ቃላትን ከሌላ ቋንቋ ስንዋስ በሃገርኛ ተመጣጣኝ ትርጉም የሚሰጥ ስያሜ ልናበጅ ይገባል

በዓለማችን የሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ ከሌላ ቋንቋ አዲስ ቃላትን ይዋሳሉ፤ በአንፃሩም ያዉሳሉ።  ይሁንና አንድ ቋንቋ ከሌላ ቋንቋ አንድ ቃልን ሲወርስ የቋንቋዉን ባህል ተከትሎ ሊሆን ይገባል ሲሉ የቋንቋ ጉዳይ ባለሞያዎች በአጽኖት ይመክራሉ። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ  ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች፤ በየስብሰባዉ ብሎም ታዋቂ የተባሉ ፖለቲከኞች፤ በሚናገሩበት የአፍ መፍቻ ቋንቋዋቸዉ ላይ ፤ እንጊሊዘኛ ቃልን ጣል ሲያደርጉ ፤ አብዛኞች የሊቅነት ማሳያ ማድረጋቸዉ ነዉ፤ ለመደመጥ ብለዉ ነዉ፤ የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል። አሁን አሁን ደሞ ባዕድ ቃላትን ስያሜ መስጠቱ እንጊሊዘኛ ቋንቋን ጠንቅቆ ለማያዉቀዉ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ገጠሪ ነዋሪ የታሰበበት አይመስልም ፤ አልያም የቋንቋ ጉዳይ ምሁራን ጉዳዩን ቢያስቡበት ይሻላል ሲሉ የቋንቋዉ መሸርሸር እያሳሰባቸዉ መሆኑን ይናገራሉ። አማርኛን ከእንጊሊዘኛ የመቀላቀል አባዜያችን ምናልባት ቅቤን ከሙዝ፤ በርበሪን ከሸክላ የምንቀላቅለዉ አባዜ ይሆን?  አሁን ደግሞ አማርኛን ከእንጊሊዘኛ መቀላቀላችን እየጨመረ የመጣዉ ሲሉ አንድ የባህል እና የኅብረተሰብ ጉዳይ ምሁር በድረገፃቸዉ ያሰፈሩት ጽሑፍን አስታወሰን። እንደዉም አሉ እናም ስለ ቡና ስለ ቢራ የእግር ኳስ ተጫዋች ቡድኖች ብቻ አዉርተን አድማጭ ከምናጣ ስለ አርሴናል ማንችስተር ማድሪድ ባርሴሎና ጣል አድርገን አድማጭ በቅጡ እንድናገኝ መጣራችን የተለመደ ፈሊጥ ሆንዋል፤ 30 ሺህ ወገኖችን የምናስብበት ከሰማዕታት መታሰብያ በዓል ይልቅ የቫልንቲንስ ዴይ ብለን የፍቅረኛሞች ቀንን ማሰባችን እየጎላ መጥቶአል ሲሉ በቁጭት ነግረዉናል። በባህርዳር ዩንቨርስቲ የግዕዝ ቋንቋ እና የሥነ-ጽሑፍ መምህር ዶ/ር ሙሉቀን አንዱዓልም ቋንቋን ከእንጊሊዘኛ መቀየጥ የተጀመረዉ ባለፈዉ ሥርዓት ነዉ።

ይህ ባለፈዉ ስርዓት ብቻ ሳይሆን አሁንም ይታያል። እኛ ጋዜጠኞች የብዙኃን መገናኛ ባለሞያዎች፤ ፖለቲከኞች ታዋቂ ሰዎች ፤ ይህንኑ አማርኛን ከኢንጊሊዘኛ ሲቀላቅሉ ይሰታዋል።

ከሰሞኑ እንኳን በሚዲያችን እና በፖለቲከኞች አንድ አዲስ ባዕድ ቃል ሲናገሩ ተሰምቶአል «ቴስት ኪት»  ኮሮና ለመያዝ አለመያዙ አልያም ፤ ለመከላከያ የሚሆን ቁስ የያዘ መመርመርያ ስብስብ ሳጥን ለማለት ነዉ።  ብዙዎች የተለያየ ተስማሚ የሆነ ገላጭ ቃል ሰጥተዉታል። የመመርመርያ ዘንግ ፤ "የመመርመሪያ ቁስ" ወይንም "የመመርመሪያ እቃዎች ሳጥን፤ የበሽታ መመርመሪያ እሽግ፤ መመርመሪያ ስንቅ ። የዳበረ አማርኛ አለን የሚሉን ፤ በአዲስ አበባ የሥነ ልሳን የትምህርት ክፍል ባልደረባ ረዳት ፕሮፊሰር  ሞገስ ይገዙ ፤ እንደሚሉት ባለፉት መንግሥታት ቋንቋዉ ሕግና ሥርዓት እንዳይኖረዉ ሆንዋል። ይሁንና አሁን ሁሉን ነገር ለማስተካከል በዚህ መንግሥት ፈቃደኝነት ታይቶአል።

ለሃገር የምንሰራዉ ስራ የአገር ባህል ታሪክ በአማርኛ ስንናገር እንጊሊዘኛ ቃላትን እየቀላቀልን ቋንቋዉን ማቀጨጫችን ለምን ይሆን? በቂ የአማርና ችሎታ ስለሌለን ? ወይስ ምሁር ለመባል? አሁንም አብዛኞች የሚያቀርቡት ጥያቄ ነዉ? አማርናዉ ላይ የቃላት እጥረትም ካለ መዋስም ካለብን መጀመርያ ከራስ፤  ከዝያ ከጎረቤት፤  ከሚቀርበን መዋስ ይኖርብናል እኮ ያሉን አንድ ምሁር ፤ ቃላት ካጣን ከከግዕዙ፤ ከትግሪኛዉ ከኦሮምኛዉ ፤ከጉራጌኛዉ  ወዘተርፈ ለምን አልወሰድንም? ብለዉ ጠይቀዋል። እንደ  ቋንቋ ምሁሩ አማርኛችን  እኮ  ጉዲፈቻ የሚለዉን ቃል ከኦሮምኛ ወስዶአል። እና  መጀመርያ ከሚቀርበን ብንዋስ ሲሉ የስነ ባህል ሃይማኖት እና ብሔረስብ ጉዳይ ምሁሩ መክረዋል። ስለሆነም አንድ ቃልን ስያሜን ከባዕድ ሃገር ስንወድ ኅብረተሰቡን ዉሰድ ብለን ከመለጠፋችን በፊት ቃሉን አልያም ስያሜዉን ኢትዮጵያዊ አድርገን ብናጠምቀዉ ሲሉ መጀመርያ በአማርኛ አቻ ቃል ቢፈለግለት ከባህሉ ከቋንቋዉ ተግባብቶ ይዘልቃል ብለዋል። ከባእድ ስያሜና ቃላት ሌላ ግን ከ ፊደል ያለቦታዉ እየገባ የአማርኛ ቋንቋን እየረበሸነዉ ያሉንም ምሁር አሉ። እንደምነክ ደህናነክ የሚሉ ብዙዎች ናቸዉ እና መጀመርያ የከን አጠቃቀም ጠንቅቀን እንወቅ ያሉኝን  ባለሞያ ይዤ በሌላ ዝግጅት እቀርባለሁ።  እስቲ እናንተም አስተያየቶቻችሁን ተሞክሮዎቻችሁን  ፃፉልን አካፍሉን!

ሙሉዉን ጥንቅር የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ