1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል የዓረብ ሃገራት ተመላሾች አቤቱታ

ዓርብ፣ መስከረም 13 2015

አማራ ክልል የሚገኙ ከዓረብ ሃገራት ተመላሾች መንግስት የገባውን ቃል አልተወጣም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጡ። ተመላሾቹ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ችግራቸውን በጋራ ለመቅረፍ በሚል «ኑሮ በሀገር» የተሰኘ ማኅበር አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ነው።

https://p.dw.com/p/4HG0c
Äthiopien | Huluager Beweket | Nuro Behager | Merawit Misganaw
ምስል Alemnew Mekonne/DW

«በመንግሥት የተገባልን ቃል አልተጠበቀም»

አማራ ክልል የሚገኙ ከዓረብ ሃገራት ተመላሾች መንግስት የገባውን ቃል አልተወጣም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጡ። ተመላሾቹ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ችግራቸውን በጋራ ለመቅረፍ በሚል «ኑሮ በሀገር» የተሰኘ ማኅበር አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ነው። ማኅበሩ ለጊዜው ከሁለት ሺህ በላይ የዓረብ ሃገራት ተመላሾችን በስሩ እንደሚገኙ ገልጧል። ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ብቻ እንኳን እስር ቤት ቆይተው የወጡ ከዐሥር ሺህ በላይ ተመላሾቹ እንዳሉ እና ለእነሱም ወደፊት እንደሚታገል ማኅበሩ ዐስታውቋል።  መንግስት በበኩሉ ከስደት ተመላሾች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሠራ ነው ይላል። ዓለምነው መኮንን ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል። 

በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአረብ አገራት በሕጋዊም ይሁን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው ይሠራሉ። አንዳንዶቹ የተሸለ ሥራ በመሥራት ራሳቸውን የለወጡ ቢሆንም፣ ብዙዎች ደግሞ እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀርቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱና በአገራቸው እንዲሰሩ ባደረገው ጥሪ መሰረት በርካቶች ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል።

Äthiopien | Huluager Bewuket
ምስል Alemnew Mekonne/DW

ከተመላሾች መካከል በባህር ዳር የሚገኙ አንዳንድ ተመላሾች በጥሪው መሰረት ወደ አገራችን ብንመጣም የተገባልን ቃል አልተጠበቀም ይላሉ፣ በተናጠል ከመንቀሳቀስም ማኅበር አስፈላጊ በመሆኑ «ኑሮ በሀገር» የሚል ማኅበር መመስረታቸውን የማኅበሩ ሊቀመንበር ወ/ሮ ፋሲካ ባዩ ትናገራለች።
የማህበሩን ዓላማ በተመለከተ ያብራራችልን የማህበሩ ምክትል ሊቀመንበር ሁሉአገር በዕውቀት ባህር ዳር ብቻ 10 ሺህ የሚደርሱ ተመላሾች አሉ ብላለች።

«ማኅበራችን ኑሮ በሀገር በቅርብ ነው እውቅና ያገኘው። ዓላማችን የብዙሐንን ድምፅ ለማሰማት፣ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለመቀየር፣ የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ ለመቀየር፣ የእህቶቻችን ድምፅ ቤት ውስጥ ላሉ ቤት ውስት ሆነው ድምፃቸው ለማይሰሙ ለማሰማት ሠርተን በሰው አገር እንደመጣነው ሠርተን ለማሳየት ነው። ዕውቅና ያገኘነው 29 ነው። ለ8 ዓመት ስንለፋ ኖረን ዘንድሮ ነው ያገኘነው፤ 2014 ዓ.ም ሐምሌ 27 ነው ያገኘነው። በስራችን ደግሞ ከ2000 በላይ አለ አሁን አጀንዳችን ላይ አለ ወደፊት ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ አሉ እስር ቤት የቆዩ ሳዑድ አረቢያ እስር ቤት የቆዩ ልዩ ሁኔታ የሚባሉ መንግስት ውጡ ሲላቸው የወጡ።»

Äthiopien | Merawit Misganaw
ምስል Alemnew Mekonne/DW

ሸጋ ጓዴ አረብ አገር ብዙ ዓመታትን እንደቆየችና ቤተሰቦቿን ሰርታ በምታገኘው ገንዘብ ትደግፍ እንደነበር አስታውሳ ወደ አገር በት ብትመለስም የጠበቀችውን እንዳላገኘች ለዶይቼ ቬሌ ተናግራለች። አብዛኛዎቹ ተመላሾች የመሥሪያ ቦታ እንዳልተሰጣቸው አመልክታ የተሰጣቸው ጥቂቶችም፣ ሰዋራና መሰረተ ልማት የሌለው ለሥራ የማመች እንደሆነ አስረድታለች።

ከቤሩት የተመለሰች ሌላ ወጣት በ2 ዓመታት የቤሩት ቆይታዋ ፆታዊ ትንኮሳን ጨምሮ ብዙ በደሎች ይደርስባት እንደነበር ገልፃለች፣ ወደ አገር ብትመለስም የተመቻቸ የስራ ሁኔታ እንዳልጠበቃት ነው የተናገረችው። ለመሥራት ምንም ችግር እንደሌለባቸው የሚናገሩት ተመላሾቹ፣ ከሁሉም ወገን እገዛ ያስፈልገናል ሲሉ ጠይቀዋል።
ብዙኃን መገናኛ ተቋማት፣ መንግስት ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ የሥነ ልቦና ምሁራንና ሌሎችም ከጎናቸው እንዲቆሙላቸው ነው ያመለከቱት።

አረብ አገር ሄዶ መሥራት ገንዘብ የሚያስገኝ ቢሆንም በተለይ ኢትዮጵያውያን መረጃና ስልጠና ሳይወስዱ መሄድ እንደሌለባቸው ነው የኑሮ በሀገር ምክትል ሊቀመንበር ሁሉአገር የምትመክረው። ብዙዎች ቋንቋ፣ ሥራ፣ አጠቃላይ የሚሄዱበትን አገር ባህልና ወግ ሳያውቁ ከዚያም በላይ በሕገወጥ መንገድ ስለሚሄዱ ነው ጉዳትና እንግልት የሚደርስባቸው ብላለች ምክትል ሊቀመንበሯ።

Äthiopien | Shega Guade
ምስል Alemnew Mekonne/DW

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስሜ ብርሌው ከአረብ አገር ተመላሾችና ሌሎችም ቅድሚያ የሚያገኙ ሰዎች ሥራ ፈላጊ እስከሆኑ ድረስ ቅደሚያ ተሰጥቶ እንደሚስተናገዱና እንደሚታገዙ ገልጠዋል። በባህር ዳር ከተማ እስከ 10ሺህ ተመላሾች አሉ የሚለውን የማይቀበሉት አቶ አስሜ የሥራ እድል ይገኛል ከሚል እሳቤ ከሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የሚመጡ ብዙዎች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ