1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አልነጃሺ በአፍሪቃ የመጀመርያዉ መስጊድ 

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 29 2013

ነብዩ መሐመድ እጃቸዉን ከፍ አድርገዉ ጣታቸዉን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በመጠቆም « ሂዱ ወደ ምእራብ በእዚያም አንድ ሃበሻ ንጉስ ታገኛላችሁ ንጉሱ ፍርዱ ፍትሃዊ ግዛቱ ሰላማዊ ህዝቡም እጅግ ጨዋና እንግዳ ተቀባይ ነዉ በእሱ ግዛት ስር ካላችሁ የሚነካችሁ አንዳች ነገር የለም» ሲሉ በፍርሃት ለተሞሉት ተከታዮቻቸዉ ነገሩዋቸዉ። ከዛም ወደ ሃበሻ ምድር መጡ

https://p.dw.com/p/3neTB
Äthiopien Al-Nejashi Moschee in Tigray
ምስል Mohamed Ali/DW

ወደ ንጉስ ነጋሽ የመጡት የነብዩ መሐመድ ተከታዮች 10 ወንዶችና 5 ሴቶች ነበሩ

ከአዲስ አበባ 800 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ስለሚገኘዉ አልነጃሺ መስጊድ ታሪክ ምን ያህል ያዉቃሉ? በእስለምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተና ግምት የሚሰጠዉ ታሪካዊዉ አልነጃሺ መስጊድ በትግራይ በተካሄደዉ ሕግን የማስከበር በተባለዉ ጦርነት ጉዳት እንደነበረበት መሰማቱ ብዙዎችን አሳዝኖአል፤ አነጋጋሪም ሆኖአል።  በጥንት ዘመን የአይሁድ እምነት ተከታዮች ብሎም ጠባቂዎች እንደነበሩ የሚነገርላቸዉ ኢትዮጵያዉያን የክርስታና እና የእስልምና እምነትን በመቀበል በመጠበቅ ከዓለም የመጀመርያዉያን ስፍራ መያዛቸዉ በታሪክ ተመዝግቦአል። አልነጃሺ መስጊድም  ከ1400 ዓመት በፊት በስደት ከመካ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የነብዩ መሐመድ የመጀመርያዎቹን ተከታዮች ተቀብለዉ ባስተናገዱት ንጉሥ ነጋሽ ምክንያት ነዉ ስያሜዉን ያገኘዉ።  
35 ተኛ መጽሐፋቸዉን በቅርቡ እንደጨረሱ የነገሩን ቡርሃን አዲስ በመባል የሚታወቁት ደራሲ መሐመድ አሊ አልነጃሺ የኢትዮጵያዉያን ታሪክ ሃብት ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ብሎም የዓለም መሆኑን ገልፀዋል። አልነጃሺ መስጊድ ታሪካዊነቱ በሰፊዉ ሲነገር አይሰማም ለምንድን ነዉ ? ለሚለዉ በተለይ የምሁራን ዜጎች ቸልተኝነት መሆኑን ይናገራሉ። 
«ነብዩ መሐመድ 613 ዓ.ም የእስልምና እምነትን ባወጁበት ወቅት ተከታዮቻቸዉ ስጋት እና ጭንቀት ዉስጥ ገቡ። ይህን የተረዱት ነብዩ መሐመድ እጃቸዉን ከፍ አድርገዉ ጣታቸዉን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በመጠቆም « ሂዱ ወደ ምእራብ በእዚያም አንድ ሃበሻ ንጉስ ታገኛላችሁ ንጉሱ ፍርዱ ፍትሃዊ ግዛቱ ሰላማዊ ህዝቡም እጅግ ጨዋና እንግዳ ተቀባይ ነዉ በእሱ ግዛት ስር ካላችሁ የሚነካችሁ አንዳች ነገር የለም» ሲሉ በፍርሃት ለተሞሉት ተከታዮቻቸዉ ነገሩዋቸዉ ከዝያም ነዉ አስር ወንዶች እና አምስት ሴት የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ንጉስ ነጋሽ የመጡት። ግን በአልነጃሺ መስጊድ ዉስጥ ምን ታሪካዊ ነገር ይኖር ይሆን? የንጉስ ነጋሽ ፤ አልያም የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ቁሳቁስ ይኖር ይሆን? ደራሲ መሐመድ አሊ ወይም ቡርሃን አዲስ ፤ ቦታዉን ብዙም አያዉቁትም። ቢሆንም ታሪካዊ መሆኑን እና የነብዩ መሐመድ አህዛቦች የቀብር ቦታ እንደሆንም ተናግረዋል።   

Äthiopien Al-Nejashi Moschee in Tigray
ምስል Mohamed Ali/DW

በትግራይ ክልል ከዉቅሮ 11 ኪሎሜትር ላይ የሚገኘዉ በአፍሪቃ የመጀመርያዉ መስጊድ መሆኑ የሚነገርለት ታሪካዊዉ አልነጃሺ መስጊድ ዉስጥ ፤ የንጉስ ነጋሽ እና የዛሬ 1400 ገደማ እስልምናን ወደ ኢትዮጵያ ያመጡት የነብዩ መሐመድ ተከታይ ሱሀባዎች አጽም ተቀብሮ እንደሚገኝ የታሪካዊ ጽሑፎች ያሳያሉ። ትግራይ ላይ ሕግን የማስከበር ዘመቻ በተባለዉ ጦርነት መስጊዱ ተጎድቶአል። ይሁንና ይህን አስከፊ ድርጊት ተጠቅሞ አልነጃሺን ይበልጥ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ደራሲ ቡርሃን አዲስ ተናግረዋል። 
የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የሆነዉ አልነጃሺ መስጊድ በ 1950 ዎቹ እድሳት እንደተደደረገለት በቅርቡም በቱርክ መንግሥት ጥሩ እድሳት ከተደረገለት በኋላ መስጊዱን እና በዉስጡ የሚገኙትን መካነ መቃብሮች ዓለም አቀፋዊ የእስልምና መካነ ቅርስ ለማድረግ ብሎም ቦታዉን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ጥረት መደረጉ ተመልክቶአል። ይሁንና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን የአልነጃሺ መስጊድን ለመጠበቅ ቦታዉን የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ በቀጣይ ያቀደዉን ስራ በተመለከተ ለመጠየቅ ያደረግነዉ ጥረት ለዛሬ አልተሳካም። ሙሉ ጥንቅሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

Äthiopien Al-Nejashi Moschee in Tigray
ምስል Mohamed Ali/DW

አዜብ ታደሰ  

ነጋሽ መሐመድ