1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኑክሌር የታጠቀዉ ጦር ፍጥጫ

ሰኞ፣ ጥር 9 2014

የዋሽግተን-ብራስልስ ፖለቲከኞች ደጋፊዎቻቸዉን ለኪየቭ ቤተ-መንግስት ባበቁ በወራት እድሜ ግን ሩሲያ ስልታዊቱን፣ ታሪካዊቱን፣ የዩክሬን ግዛት ክሪሚያን ከኪየቭ እጅ በኃይ መንጭቃ ስትወሰድ የዋሽግተን-ብራስልስ ተሻራኪዎች ከቃላት ዉግዘት፣ ፉከራ፣ ምናልባት ከምጣኔ ሐብት ማዕቀብ በላይ ለዩክሬን የተከሩት ነገር የለም።

https://p.dw.com/p/45emc
Bildkombo Biden und Putin
ምስል Jim WATSON/Grigory DUKOR/AFP

የቀዝቃዛዉ ጦርነት ቅሪት ዉዝግብ


170122
የተመሳሳይ ዘር የአንድ ኃይማኖት ተከታዮች መኖሪያ፣የአንድ ፖለቲካዊ ሥርዓት ተጋሪ፣ አንድም-ሁለትም፣ የዘመናት ወዳጆች-ጠበኞችም ከሁሉም በላይ ድንበር ተጋሪ ጎረቤቶች ናቸዉ።ሩሲያና ዩክሬን።በ1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንደ ሁለት ጎረቤት ሐገር ለየብቻቸዉ ቆሙ፣በ2014 ተጣሉ።ጠቡ አቀጣጣይ እንጂ አብራጅ አጥቶ የወዳጅ፣ወንድማማች፣ተጎራባቾች ከመሆን ይልቅ የቀዘዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን መልክና ባሕሪ ይዞ ሞስኮን ከዋሽግተን-ብራስልሶች ጋር እያወዛገበ፣ ጦር ያማዝዝ፣ዲፕሎማት-ፖለቲከኞችን ያራዉጥ ገባ።ምላጭ ያስብ ይሆን? ጠብ፣ዉጥረቱ መነሻ፣ የደረሰበት ደረጃ ማጣቀሻ ጥያቄዉ መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
                                 
የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈዉ ወር እንዳሉት ነገር የተበላሸዉ በ1991 ነዉ።«በ1991 እራሳችንን 12 ሥፍራ ከፋፈልን።ይሕ ክፍፍል፣ እንደሚመስለኝ፣ ለወዳጆቻችን በቂ አይደለም።የአዉሮጳ ሐገራት ራሳቸዉ ትናንሽ መንግስታት በመሆናቸዉ ሩሲያ አሁንም ለነሱ በጣም ትልቅ ሆነችባቸዉ።»
በርግጥም ትልቅ ሐገር ናት።በቆዳ ስፋት ከዓለም አንደኛ ናት።ሰዉ ከሚኖርበት ምድር አንድ ሰባተኛዉን ግዛት ትጠቀልላለች።የሕዝቧ ቁጥር ግን ከስፋቷ ጋር ሲነፃፀር ትንሽ ነዉ።144 ሚሊዮን።ይሕ ከነቻይና፣ሕንድና ዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሲወዳደር ቁጥሩ እጅግ ያነሰ ሕዝብ ግን ከዓለም አምስተኛዉን የጦር ሐይል አሰልፏል።ከአንድ ሚሊዮን በላይ መደበኛ፣ ከ2 እስከ 20 ሚሊዮን የሚገመት ተጠባባቂ ወታደሮች አሉት።
ዓለም ካከማቸችዉ የኑክሌር ቦምቦች ከግማሽ የሚበልጠዉ በክሬምሊን ትዕዛዝ የሚፈነዳ ነዉ።አያድርስ።ከዓለም አንደኛዉ ጠንካራ እግረኛ ጦር የሩሲያ ነዉ።በዓየርና በባሕር ኃይል ሁለተኛዉ ጠንካራ ጦር የሩሲያ ነዉ።ይሕ ጦር ከአንድ መቶ ሺሕ የሚበልጡ ወታደሮቹን በቅርቡ ወደ ዩክሬን ድንበር አስጠግቷል።
ጦሩ ከሞስኮ «ቀጥል» ከተባለ፣ ከፊል የሶቭየት ሕብረት፣ በከፊል የምዕራባዉያን ጦር መሳሪያ እንደነገሩ የታጠቀዉን 255 ሺሕ የዩክሬን ጦር ባጭር ጊዜ ረምርሞ ኪየቭ ለመግባት የጦር አዋቂዎች እንደሚሉት ከሰዓታት በላይ አይፈጅበትም።
እስካሁን ግን ያ ግዙፍ ጦር ማድረግ የሚችለዉን እንዲያደርግ ጠቅላይ አዛዡ አላዘዙም። የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስቴር (ፔንታጎን) ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢም ይሕን ያምናሉ።«ሚስተር ፑቲን የመጨረሻዉን ወስነዋል ብለን አናምንም።ጉዳዩ እዚሕ ደረጃ ላይ ስለሚገኝም፣አሁንም ለዲፕሎማሲ በቂ ጊዜና ሥፍራ አለ ብለን እናምናለን።እና በግልፅ እንደሚታወቀዉ እኛም የምንፈልገዉ ይሕ እንዲሆን ነዉ።ዲፕሎማሲዉ ለዉጤት እንዲበቃ ነዉ።»
ፑቲን ጦራቸዉን በርግጥ እስካሁን ለጥቃት አላዘዙም።የሳይበር አዋቂዎቻቸዉ ግን የኪየቭ መንግስትን የኮምፒዉተር መረብ መነቃቅረዉ ጣሉት።አንድም ጥይት ሳይጮሕ የዩክሬን መንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ምናልባትም የጦሩ የመረጃና የመገናኛ አዉታር ተሽመደመደ።ሐሙስ-ለአርብ አጥቢያ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል አይደለችም።የአዉሮጳ ሕብረት አባልም አይደለችም።የሩሲያ ጦር ዘመቻ፣የስለላ ዝግጅቷ፣ የሳይበር ጥቃቱም ከኪየቮች እኩል በጣም ያሳሰበ፣ ያስጨነቀዉ ግን እንደ ኔቶ አዛዥ ዩናይትድ ስቴትስን፣እንደ አዉሮጳ አሰባሳቢ ደግሞ የአዉሮጳ ሕብረትን ነዉ። የሕብረቱ የዉጪ ግንኙነት የበላይ ጆሴፍ ቦርየል ባለፈዉ አርብ ይሕንኑ አረጋግጠዋል።
«እንዲሕ አይነቱን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል ሐብታችንን ማንቀሳቀስ እንችል እንደሁ፣ አባል ሐገራትን እጠይቃለሁ።ምክንያቱም ዩክሬን የአዉሮጳ ሕብረት አባል አይደለችም።በዚሕ ፕሮጄክት አትሳተፍም።ዩክሬን ይሕን የሳይበር ጥቃት እንድትከላከል ሁሉንም ሐብታችንን ማንቀሳቀስ አለብን።በሚያሳዝን ሁኔታ ይሕ እንደሚሆን እናዉቅ ነበር።»
ሕዳር 2013 ወደ ሞስኮ ያዳላሉ የሚባሉት የያኔዉ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቪክቶር ያኑኮቪችን በመቃወም የርዕሠ-ከተማ ኪየቭ ሕዝብ አደባባይ ሲወጣ ለተቃዋሚዎቹ ከዲፕሎማሲ እስከ ጉብኝት የሚደርስ ድጋፍ የሰጡት የዋሽግተን-ብራስልስ ወዳጆች የመጨረሻ ዉጤቱን ሳያዉቁ፣ሞስኮን ለከፋ አፀፋ እንደሚያነሳሳ ሳይጠረጥሩ ቀርተዉ አልነበረም።

Victory Day Military Parade
ምስል Sergei Karpukhin/TASS/dpa/picture alliance
Russland Moskau Tag des Sieges Parade
ምስል Alexander Zemlianichenko/AP Photo/picture alliance

ደገፉ።የዋሽግተን-ብራስልስ ፖለቲከኞች ደጋፊዎቻቸዉን ለኪየቭ ቤተ-መንግስት ባበቁ በወራት እድሜ ግን ሩሲያ ስልታዊቱን፣ ታሪካዊቱን፣ የዩክሬን ግዛት ክሪሚያን ከኪየቭ እጅ በኃይ መንጭቃ ስትወሰድ የዋሽግተን-ብራስልስ ተሻራኪዎች ከቃላት ዉግዘት፣ ፉከራ፣ ምናልባት ከምጣኔ ሐብት ማዕቀብ በላይ ለዩክሬን የተከሩት ነገር የለም።
ቦርየል ባለፈዉ አርብ እንዳሉት የሳይበር ጥቃቱን ሕብረታቸዉ፣ኔቶ፣የሁለቱም መሪና አስተባባሪ ዩናይትድ ስቴትስም ጠንቅቀዉ ያዉቃታል።ያወቁቱን ካለከሸፉ፣ ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ዉግዘት፣የአፀፋ እርምጃ ዛቻ፣ፉከራዉን ቢያንቆረቁሩ ለዩክሬን ሕዝብ የሚጠቅመዉ መኖሩ በርግጥ አጠራጣሪ ነዉ።
ባለፈዉ አርብ  የሳይበር ጥቃቱን ለመበቀል ፉከረ-ቀረርቶዉ በተንቆረቆረበት በአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ግን ከፉከራ-ማስፈራራቱ ጋር የዲፕሎማሲዉ ጥረትም መቀጠል አለበት ባይ ናቸዉ።
                                         
«ቀዉሱ ከዚሕ በላይ እንዳይባባስ የምንችለዉን ሁሉ እናደርጋለን።የተለያዩ መስመሮችን መጠቀም የሚያስፈልገዉም ለዚሕ ነዉ።በተለይም የአዉሮጳ የፀጥታ ድርጅት OSCE እና የኖርማንዲ ቀርፅን መጠቀም አስፈላጊ ነዉ።በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ ወገኖች ጋር ለመነጋገር ወደ ሞስኮ የምሔደዉም ለዚሕ ነዉ።»
«የኖርማዲ ቅርፅ» የሚባለዉ የጀርመን፣የፈረንሳይ፣ የሩሲያና የዩክሬን መሪዎች ከዚሕ ቀደም ኖርማዲ-ፈረንሳይ ዉስጥ ጀምረዉ በተለያየ ጊዜ ያደርጉት የነበረዉ ዉይይት ነዉ።አዲሲቱ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወደ ሞስኮ ከመዉጣታቸዉ በፊት ዛሬ ጧት ኪየቭ ነበሩ።ከዩክሬኔ አቻቸዉ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የሰጡት መግለጫ ግን የክሬምሊን ሹማምንትን ፊት እዳያጠቁርባቸዉ ማስጋቱ አልቀረም።
                                    
«እያንዳዱ ተደጋጋሚ ወረራ፣ ከዚሕ በፊት በተደጋጋሚ ብለነዋል፣ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል።ከሩሲያ ጋር የምር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ነን።ምክንያቱም አሁን ያለዉን በጣም አደገኛ ሁኔታ ለማርገብ ብቸኛዉ መንገድ ዲፕሎማሲ ነዉና።አንድ ሐገር በየትኛዉ መንገድ መጓዝ እንዳለበት፣ምን ዓይነት ግንኙነት እንደሚኖረዉ፣የትኛዉን ማሕበር መቀላቀል እንዳለበት ማንም ሌላ ሐገር የመወሰን መብት የለዉም።»
አዎ! ማንም ሐገር ስለሌላዉ ሐገር የመወሰ የለበትም-ድፍን ዓለምን የሚያግባባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርሕ።ይሁንና አዲሲቱ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኪየቭ ሆነዉ፣ኪየቭን ወክለዉ፣ዩክሬን ብትጠቃ አጥቂዉ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍል እያስጠነቀቁ፣ ማንም ሐገር የሌላዉን መብት መንካት የለበትም ማለታቸዉ ማጠያየቁ በጣሙን ሞስኮዎችን ማስከፋቱ አይቀርም።
በ13ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ሞንጎሎች ሩስ ወይም ኪይቫን ሩስ የሚባለዉን ጥንታዊ ሥርዓት አፍርሰዉ በአብዛኛዉ የዛሬዉን የዩክሬን አካባቢ እስከተቆጣጠሩበት ድረስ ሁለቱ ሐገራት የአንድ ሥርዓት ግማደ ግዛቶች ነበሩ።ሞንጎሎች ተዳክመዉ የሩሲያ ንጉሳዊ ሥርወ-መንግስት ሲጠናከር የዛሬዎቹ ዩክሬንና ቤሎ ሩስ ትንንሾቹ ሩሲያ ከሚል ቅፅል ጋር የሩሲያ አካል ሆኑ።
የሩሲያ አብዮተኞች ክሬምሊንን በተቆጣጠሩ ባመቱ ግድም በ1918 ዩክሬን ነፃነትዋን አወጀች።የሶቭየት ሕብረት ጦር ዩክሬንን ወርረ።የሁለቱን ተመሳሳይ ጎሳ መኖሪያ፣ የአንድ ኃይማኖት፣ የአንድ ሥርዓት ተጋሪ ተጎራባች ሐገራት መንግስታት ጠብ ያረገቡት በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የጋራ ግንባር የፈጠሩት «የማዕከላዊ ኃይላት» ይባሉ የነበሩት መንግስታት ነበሩ።
ጀርመንን፣ የኦስትሪያ-ሐንጋሪን፣የኦስማን ቱርክንና ቡልጋሪያን በሚያስተናብረዉ ሕብረት ሸምጋይነት የሞስኮና የኪየቭ ገዢዎች ያደረጉት ስምምነት ከሶስት ዓመት በላይ አልቆየም።ሩሲያና ዩክሬን በ1922 የሶቭየት ሕብረት ሶሻሊስታዊ ሪፐብሊክን ሲመሰርቱ ስምምነቱም ተልዕኮዉን ጨረሰ።
የሞስኮና የኪየቭ ፖለቲከኞች ቀድመዉ የመሰረቷት ሶቭየት ሕብረት በ1991 ስትፈራርስ ሁለቱም የየራሳቸዉን ነፃነት አወጁ።የሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ 70 ዓመት ግድም ያስቆጠረዉ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜም፣ የዎርሶ ስምምነት የሚባለዉ የሶሻሊስት ሐገራት የጦር ተሻራኪ ድርጅት መጨረሻም ነበር።
ሶቭየት ሕብረት ስትፈራርስ አብዛኛዉን የጦር ኃይል፣የፖለቲካ ጡንቻና ምጣኔ ሐብት የተረከበችዉ ሩሲያ ናት።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከ1991 ወዲሕ ባለፍ አገደም፣ በ2014 ጀምሮ ደግሞ በተከታታይ የቀጠለዉ የኪየቭና የሞስኮ ጠብ ዋና መነሻዉ የሁለቱ መንግስታት ልዩነት ሳይሆን የምዕራባዉያንና የሩሲያ ስር የሰደደ የጥቅም ሽሚያ ነዉ።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የቀድሞ የሶቭየት ሕብረትን ሪፐብሊኮች ተራ በተራ አባሉ እያደረገ ወደ ምስራቅ መስፋፋቱን ሩሲያ ለሕልዉናዋ አደገኛ እንደሆነ ትቆጥረዋለች።ትቃወመዋለችም። ሩሲያ በ2014 ክሪሚያን ለመጠቅለልዋም ሆነ አሁን ጦርዋን ወደ ዩክሬን ድንበር ለማስጠጋትዋ ምክንያት ያደረገችዉም ኔቶ ዩክሬንን ከጠንካራ ዕቅፉ ለማስገባት ዳርዳር ማለቱን በመቃወም ነዉ።
ፕሬዝደንት ፑቲን ባለፈዉ ታሕሳስ እንዳሉት ኔቶ ወደ ምስራቅ እንደማይስፋፋ ምዕራባዉያን በ1991 ለሞስኮዎች የገቡትን ቃል አጥፈዋል።«ኔቶ አንድም ኢንቺ ወደ ምስራቅ አይስፋፋም።ይሕ ነበር በ1990ዎቹ የተነገረን።ምንድነዉ የሆነዉ።ንዝንዝ ነዉ።ማብቂያ የሌለዉ ንዝንዝ።አምስት የኔቶ የመስፋፋት ማዕበል ነበር።የሚሳዬል መሳሪያዎች ፖላንድና ሩሜኒያ ዉስጥ ተተክለዋል።ይሕን ነዉ የምንለዉ።ሊገባችሁ ይገባል።ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ወይም ወደ ብሪታንያ ድንበር የተጠጋነዉ እኛ አይደለንም።እኛጋ የመጣችሁት ናንተ ናችሁ።»
ጠቡን ለማድረገብ የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ መሪዎች ሁለቴ፣ የሁለቱ ሐገራት ዲፕሎማቶች አንዴ ያደረጉት ዉይይት እስካሁን ያመጣዉ ዉጤት የለም።ሩሲያ የፀጥታ ውዋስትና በሚል ማዕቀፍ ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን ያቀረበችዉን ጥያቄ ምዕራባዉያኑ አልተቀበሉትም።
ሩሲያም ጦሯን ከዩክሬን ድበር እድታነሳ ምዕራባዉያን ያቀረቡትን ጥያቄ ዉድቅ አድርጋዋለች።ምዕራባዉያን ለዩክሬን ዙሪያ መለስ ድጋፍ ከመስጠት፣ እስከ ዉጊያ ዝግጅት፣ከዲፕሎማሲ ጫና እስከ ማዕቀብ ሩሲያን ሊቀጡ ይዝታሉ።
ሩሲያ ባንፃሩ ከጠመንጃዉ አፈሙዝ በተጨማሪ ከሳይበር ጥቃት ለአዉሮጳ የምታንቆረቁረዉን ጋስ እስከማቋረጥ በሚደርስ እርምጃ ምዕራባዉያኑን ለመቅጣት ትፎክራለች።ያ ኑክሌር  የታጠቀ ጦር እስካሁን ምላጭ አልሳበም።ዩክሬን ድንበር ላይ እንደተሰላለፈ ነዉ።ከዚያስ?

Ungarn | Clinton and Jelzin | Unterzeichnung Atomwaffensperrvertrag
ምስል David Brauchli/AP Photo/picture alliance
Ukraine Kiew | Pressekonferenz Annalena Baerbock und Dmytro Kuleba
ምስል Janine Schmitz/photothek.de/picture alliance
Bundeswehrsoldaten in Litauen
ምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ