1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ነብሰጡር ሴቶች የኮቪድ-19 ክትባት መከተብ አለባቸውን? 

ረቡዕ፣ ግንቦት 18 2013

የኮቪድ -19 ክትባት ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው ለሚመደቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል።ነፍሰ ጡር ሴቶችም ከዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።ይሁንና ክትባቱ በፅንሱ ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል የሚል ስጋት ይስተዋላል ። ለመሆኑ ክትባትና እርግዝናን በተመለከተ እስካሁን የተደረሰባቸው ሳይናሳዊ እውነታዎች ምን ይላሉ? 

https://p.dw.com/p/3tzDG
Peru Symbolbild Schwangerschaft Coronavirus Südamerika
ምስል El Comercio/Zumapress/picture alliance

ነብሰጡር ሴቶች የኮቪድ-19 ክትባት መከተብ አለባቸውን? 

የኮቪድ -19 ክትባት በእድሜ ለገፉና ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው ለሚመደቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች  ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል።ነፍሰ ጡር ሴቶችም ከዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።ይሁንና ክትባቱ በእናትየውና በጽንሱ ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል  የሚል ስጋት ይስተዋላሉ።ለመሆኑ ክትባትና እርግዝናን በተመለከተ እስካሁን የተደረሰባቸው ሳይናሳዊ እውነታዎች ምን ይላሉ? ነብሰጡር ሴቶችሰ የኮቪድ-19 ክትባት መከተብ አለባቸውን? 
ነብሰ ጡር ሴቶች  ለኮቪድ-19 በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው ከሚመደቡት የኅብረተሰብ ክፍሎች  ውስጥ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ።
«ጃማ ፔዲያትሪክስ» በተባለ የአሜሪካ  የሳይንስ መጽሔት ላይ በሚያዝያ ወር  የታተመ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ በእርግዝና ወቅት በሽታን የመከላከል ስርዓት ጫና ውስጥ ስለሚሆን፣ነፍሰ ጡር  ሴቶች ካልሆኑ ሴቶች ጋር ሲነፃፀሩ  በበሽታው የበለጠ  ሊጠቁ እንደሚችሉ አመልክቷል። ተመራማሪዎቹ በዚሁ መፅሄት በሽታው በሚወለዱት ህፃናት ላይም ከፍተኛ የሞት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
የጀርመን የህክምና ባለሙያዎች በቅርቡ ባወጡት መረጃም በኮቪድ-19 በሽታ የተያዙ ነፍሰ ጡር ሴቶች ከሌሎች  ሴቶች ጋር ሲነፃፀሩ ለፅኑ ህክምና የመጋለጣቸው አደጋ በስድስት እጥፍ  ሊጨምር ይችላል። 
በዚህ የተነሳ በከፍተኛ ደረጃ ክትትል በሚደረግባቸው ክፍሎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት በኮቪድ-19  በጠና የታመሙ  ነፍሰ ጡር ሴቶች መኖራቸውን ባለሙያዎቹ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ  ፅንስና የማህፀን ህክምና ባለሙያዎች ማኅበር አባል እንዲሁም በየካቲት 12 ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ ሀላፊና የማህፀንና ፅንስ ሀኪም የሆኑት ዶክተር አየለ ተሾመም የኮቪድ-19 በሽታ ለነብሰ ጡር ሴቶችም ይሁን ለሚወለደው ህጻን  አደገኛ መሆኑን ይገልፃሉ።
በዚህ የተነሳ እንደ አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ፣ እስራኤል እና ቤልጂየም ባሉ ሀገራት ነፍሰ ጡር  ሴቶች  ክትባት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ናቸው ። 
በሌላ በኩል ጀርመንን በመሳሰሉ ሀገራት  የነብሰ ጡር ሴቶች ቅድሚያ ይከተቡ  ምክር ብዙም ግልጽ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። የክትባቱን አደጋዎች እና ጥቅሞች የመመዘን ተግባር ለሐኪሞች እና ለራሳቸው ለነፍሰ ጡር ሴቶች  የተተወ ነው።
የሀገሪቱ ገለልተኛ የክትባት ቋሚ ኮሚቴ  እንደሚለው እስካሁን ድረስ በእርግዝና ወቅት የኮቪድ-19 ክትባት ሲሰጥ የቆየው ለአንዳንድ ግለሰቦች  በተለዬ ምክንያት ብቻ ሲሆን፤ለዚህም  ኮሚቴው በምክንያትነት የሚያቀርበው እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ለመደገፍና ደህንነትን ለመጠበቅ በቂ መረጃ  አለመኖሩን ነው። 
ይሁን እንጅ እዚያው ጀርመን ውስጥ  የአንዳንድ ግዛቶች  የጤና ባለሥልጣናት  የኮሚቴውን  ምክር ሳይጠብቁ  ክትባቱ እንዲሰጥ የወሰኑም አሉ። 
የጀርመን የማህፀንና ፅንስ ህክምና ማህበራትና እና የህክምና ባለሙያዎች ቡድን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫም በሽታው ለእናት እና ለልጅ አደገኛ መሆኑን የሚያሳዩ በቂ መረጃዎች ስላሉን  ነፍሰ ጡር ሴቶች ቅድሚያ መከተብ አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። 
ዶክተር አየለ እንደሚሉት በኢትዮጵያም ለነፍሰ ጡር ሴቶች ክትባቱን ቅድሚያ የመስጠት ሁኔታ የለም።ይሁን እንጅ እንደ አካባቢው ነቫራዊ ሁኔታና የመረጃ ትንተና በክትባቱ ላይ  የተለያዬ አረዳድ ቢኖርም ከችግሩ አንፃር ለነብሰ ጡር ሴቶች ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ይስማማሉ። 
ባለሙያው እንደሚሉት በሽታው በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ ከሚያደርሰው ከጉዳት አንፃር በኢትዮጵያም የሚመለከታቸው አካላት ሊያስቡበት ይገባል።
በሌላ በኩል ስለክትባቱ አስፈላጊነት ሲነሳ ክትባቱ በእናት እና በሚወለደው ልጅ ላይ  ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል የሚለው ሀሳብም አብሮ ይነሳል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት  የኮቪድ-19 ክትባቶች በእርግዝና ወቅት ጎጂ መሆኑን የሚያሳይ  መረጃ የለም። በአሜሪካ  ክትባት በሚሰጡበት ወቅት ነፍሰ ጡር መሆናቸውን  የገለጹ ከ 106,000 በላይ ሴቶች «ቪ-ሴፍ ኮቪድ-19 እርግዝና የክትባት ምዝገባ» ተብሎ ለሚጠራው  ለአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና  እና መከላከያ ማዕከል በእንግሊዝኛው ምህፃሩ (ሲ.ዲ.ሲ)  የመረጃ ቋት በሰጡት መረጃ መሰረት እስከ ተያዘው ግንቦት ወር መጀመሪያ  ድረስ ምንም ዓይነት የደኅንነት ሥጋት አልመተዘገበም። 
በሲዲሲ መረጃ መሰረት በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ፅንስ የመቋረጥ አደጋ ከፍተኛ ቢሆንም፤ክትባት በተሰጡ ነፍሰ ጡር ሴቶችም ይሁን  በሕፃናቱ ላይ ምንም የደኅንነት ሥጋት አላጋጠመም።በኢትዮጵያም ሁኔታው ተመሳሳይ መሆኑን ባለሙያው ይገልፃሉ።
ያም ቢሆን በመጀመሪያ እና በሁለተኛ የእርግዝና ወራት ክትባት ለወሰዱ ሴቶች ተጨማሪ ምርመራና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና  እና መከላከያ ማዕከል  መረጃ ጠቁሟል። 
በመሆኑም  የፈረንሣይ ባለሙያዎች  ለጥንቃቄ ሲባል ከሶስት ወር በላይ ለሆናቸው  ነፍሰ ጡር ሴቶች ነው  ክትባቱን የሚሰጡት።ለጀርመናዊው የተዋህሲያን ተመራማሪ ሆዘማን ድሮስተን የፈረንሣይ አካሄድ መልካምና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። 
የጀርመን  የዛክሰን ግዛት የክትባት ኮሚሽን በበኩሉ ከአሜሪካ እና ከሌሎች ሀገሮች በተገኘ መረጃ መሰረት ከ13 ኛው ሳምንት እርግዝና ጀምሮ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ክትባት እንዲሰጥ ስምምነት ላይ ደርሷል።
በአጠቃላይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደካማ የጤና አጠባበቅ ስርዓቶች  ባሉባቸው ሀገራት ከኮቪድ-19 በሽታ በተጨማሪ እርግዝናን አደገኛ የሚያደርጉ ምክንያቶች በርካታ  በመሆናቸው ክትባቱን ለነብሰ ጡር ሴቶች  ቅድሚያ መስጠት ተገቢ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ። ለዚህም ክትባቱን የሚያመርቱ ሀገሮች ለድሃ ሀገራት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ ርምጃ ነው።በሌላ በኩል እንደ ባለሙያው ዶክተር አየለ የተማረውን የህብረተሰብ ክፍል ጨምሮ በክትባቱ ላይ ያለው ብዥታ ቀላል አይደለም። ስለሆነም የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠትም ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

Symbolbilder COVID-19-Vektor-Impfstoff
ምስል K. Schmitt/Fotostand/picture alliance
Iran Coronavirus Impfung
ምስል Morteza Nikoubazl/NurPhoto/picture alliance

 

ፀሀይ ጫኔ
ሸዋዬ ለገሠ


ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።