ችላ ተባልን ያሉ የታጋች ቤተሰቦች ጥሪ
ዓርብ፣ የካቲት 27 2012በኦሮሚያ ክልል፣ ቄሌም ወለጋ ዞን በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ የታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ ዝም መባሉ አሳስቦናል ሲሉ ቤተ ዘመዶችና ጉዳዩ ያገባናል ያሉ ዜጎች ገለፁ። ተማሪዎቹ መታገታቸው ከተነገረ 93 ቀን እንደሆነው ያመለከቱት ቤተ ዘመዶች መንግሥት ጉዳዩን እየተከታተልኩ ነው ሲል ይገልፅ ነበር አሁን ግን ዝምታን መርጦአል ብለዋል። ጉዳዩ ያገባናል ብለው እየተከታተሉ የሚገኙ ወደ አስር የሚሆኑ ወጣቶች በበኩላቸው መንግሥት ከሰጠው መግለጫ የተለየ የሰማነው ነገር የለም፤ እንደውም የታገቱትን ተማሪዎች ጉዳይ ማንሳት በፖለቲካ የሚስፈርጅ ሆንዋል ይላሉ። በሀገሪቱ የሚገኙ ብዙኃን መገናኛዎች ብሎም ፖለቲከኞች ጉዳዩን ከማንሳት ተቆጥበዋል ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ከታገቱት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሆነችዉ እህቴ ሙሉ ዘውዱ ነገር ምን ደረሰ እባካችሁ ጠይቁ ሲል ወደ ዶይቼ ቬለ የደወለው የታጋች ተማሪ ወንድም በምዕራብ ጎጃም ቡሬ ወረዳ የሚኖሩት ወላጅ እናቴና እና አያቴ ጠዋት ማት በለቅሶ እየደከሙ ነዉ ይላል። የታገቱትን ተማሪዎች ጉዳይ በቅርበት እየተከታተል ነው ግን አሁን መንግሥት ይፋ ካደረገዉ መግለጫ በላይ የምናውቀው ነገር የለም ያለችን በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በመስራትዋ የምትታወቀው መምህርት መዓዛ መሃመድ ጉዳዩን ማንሳት በፖለቲካ የሚያስፈርጅ መሆኑን ተናግራለች። ግን የታጋች ቤተሰቦች እስከመቼ ያልቅሱ ? ስትልም ትጠይቃለች።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ