1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻድ እና ኢድሪስ ዲቤ ኢትኖ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 16 2013

ቻድ ለሦስት አስርት ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝደንቷ ኢድሪስ ዲቤን ትናንት ሸኘች። ዲቤ ለስድስተኛ ጊዜ በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ በተደረገ በሰዓታት ውስጥ ነው መገደላቸው የተሰማው። ልጃቸው በቦታቸው ተተክቷል፤ የቻድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይኽ ተቀባይነት የለውም እያሉ ነው።

https://p.dw.com/p/3sVId
Tschad l Beerdigung des tschadischen Präsidenten Idriss Déby Itno
ምስል Blaise Dariustone/DW

ትኩረት በአፍሪቃ

በጎርጎሪዮሳዊው 1952 ዓ,ም ሰኔ 18 ቀን ውሎ አድሮ ቻድን ከ30 ዓመታት በላይ ሊመራ እንደሚችል ባይገመትም በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል በርዶባ በተባለች መንደር አንድ ሕጻን ተወለደ። ኢድሪስ ዲቤ። ፤ አባት የከብቶች ጠባቂ እረኛ ነበሩ። ቢዳያት ከተባለው ጎሳ የተገኘው ሕጻን በትንሽነቱ የቁርዓን ትምህርት ቤት ገብቶ ቀራ እና ከፍ ሲል ፍራንኮ አረብ ትምህርት ቤት ዘለቀ። በትምህርቱ ገፍቶም የመጀመሪያ ዲግሪውን በሳይንስ አገኘ። ከቀለም ትምህርቱ ቀጥሎ ወደ ዋና ከተማ ንጃሚና በመዝለቅ ወታደራዊ መኮንኖች ትምህርት ቤት ገባ። ከዚህም ወደ ፈረንሳይ ለልምምድ ተልኮ በጎርጎሪዮሳዊው 1976 ዓ,ም የፕሮፌሽናል አውሮፕላን አብራሪነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱን ይዞ ተመለሰ። ለቻድ ጦር ሠራዊት እና ለወቅቱ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ማሉም ታማኝ ሆኖ ማገልገሉን ታሪኩ ያወሳል።

ማዕከላዊ አፍሪቃዊቱ ሀገር ቻድ የበርካታ ታጣቂዎች የፍልሚያ ምድር በሆነችበት ወቅት በጎርጎሪዮሳዊው 1979 ዓ,ም ማለት ነው ከፈረንሳይ የተመለሰው ወጣቱ መኮንን ኢድሪስ ዲቤ ወገንተኝነቱን ከቻድ የጦር አበጋዞች አንዱ ለነበሩት ሂሲኔ ሀብሬ ጋር አደረገ። ብዙም ሳይቆይ በ1982 ሀብሬ የቻድ ፕሬዝደንት ለመሆን በቁ። ኢድሪስ ዲቤንም የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ አድርገው ሾሙ። የጦር አዛዡ ኢድሪስ ዲቤም በያዙት ወታደራዊ ሥልጣን በጎርጎሪዮሳዊው 1984 በምሥራቃዊ ቻድ የሚንቀሳቀሱ የሊቢያ ወገንተኛ የሆኑ ኃይሎችን ድምጥማጥ በማጥፋት ስማቸው ገነነ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም የቻድ ፕሬዝደንት ሂሲኔ ሀብሬ ወታደራዊ አማካሪ ኃላፊ ሆኑ። በፈረንሳይን እየተደገፉ ከሊቢያ ኃይሎች ጋር ውጊያ ገጠሙ። ቶዮታ ዕቃ ጫኝ ተሽከርካሪን አዘውትረው በመጠቀማቸውም ጦርነቱ «የቶዮታ ጦርነት» በመባል ይታወቃል። ዲቤ በተጠቀሙት የጦር ስልትም በጠላት ኃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አደረሱ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በጎርጎሪዮሳዊው 1989 ዓ,ም ሚያዚያ ወር መባቻ በሀብሬ እና በዲቤ መካከል ልዩነት መፈጠር ጀመረ። ቆየት ብሎም ፕሬዝደንት ሀብሬ የቀኝ እጃቸው የነበሩትን ኢድሪስ ዲቤን፣ የወቅቱ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር የነበሩትን ማህማት ኢትኖን እና የቻድ ጦር ኃይል የበላይ የነበሩትን ሀሰን ጃሙስን መፈንቅለ መንግሥት በማደራጀት ወነጀሉ። ወዲያው ዲቤ መጀመሪያ ወደ ዳርፉር ከዚያም ወደ ሊቢያ ሸሹ። ኢትኖና ጃሙስ ታስረው ተገደሉ። አብዛኞቹ የመፈንቅለ መንግሥቱ ተጠርጣሪዎች ከዛግሀዋ ጎሳ አባላት ስለነበሩ ሀብሬ ብዙዎቹን ማሳደድና በዘፈቀደ መግደል ጀመሩ። ይኽም የጦር ወንጀል ክስ አስከተለባቸው። ወደ ሊቢያ የሸሹት ኢድሪስ ዲቤ በያኔው የሀገሪቱ መሪ ሞአመር ጋዳፊ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸው ባገኙት ወታደራዊ ድጋፍ የቻድን መንግሥት ለመገልበጥ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ወደ ሱዳን በመሻገርም በኻርቱም እና ትሪፖሊ መንግሥታት እየታገዙ የአርበኞች ንቅናቄ የተሰኘ የአማጽያን ቡድን አቋቋሙ። በሦስት ዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊው 1990 ታኅሣስ ወር አማጽያኑ ያለምንም ተገዳዳሪ ወደ ዋና ከተማ ንጃሚና ገብተው በተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ሀብሬን ከሥልጣን አባረሩ። በቀጣዩ ጎርጎርዮሳዊ ዓመት በይፋ የቻድ ፕሬዝደንት የሆኑት ኢድሪስ ዲቤ በተከታታይ ለስድስት ጊዜ በተካሄዱ ምርጫዎች እሳቸው ዳግም እየተመረጡ በሥልጣን ከርመው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ  ከመንበሩ በሞት ተሰናበቱ።

ኢማኑዌል ማክሮ በቀብር ሥርዓቱ ላይ
ምስል Christophe P. Tesson/Epa/AP/picture alliance

የኢድሪስ ዲቤ ኢትኖ ሞታቸው የተሰማው በቅርቡ ቻድ ባካሄደችው ምርጫ የማሸነፋቸው ዜና በተነገረ በሰዓታት ውስጥ ነው። በእርግጥ የአካባቢውን ፖለቲካ የሚከታተሉ እንደሚሉት የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዳግም ቻድን በማዕከላዊ አፍሪቃ እና በሳህል አካባቢ የስበት ማዕከል ማድረግ የተሳካላቸውን የዲቤን መመረጥ ይፋ ማድረጉ የሚጠበቅ ነበር።

ስለዲቤ አሟሟት የሚነገሩት የተለያዩ ናቸው። ፕሬዝደንቱ የሞቱት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ከአማጽያን ጋር በሚካሄደው ውጊያ ቆስለው መሆኑን የሚገልጹ እንዳሉ ሁሉ በቅርብ ሰዎቻቸው ተገደሉ የሚሉም አሉ። የቀድሞ የቻድ ሚኒስትር የነበሩና አሁን በስደት ላይ የሚገኙት ፋውስቲን ፋቾ ባላማ ለዶቼቬለ እንደሚሉት ፕሬዝደንቱ እንደተባለው ጦር ግንባር ሄደው ሳይሆን በሥልጣናቸው አካባቢ ባሉ የቅርብ ሰዎቻቸው ሳይገደሉ አልቀረም። እስካሁን ግን ሞተ ምክንያታቸውን አስመልክቶ ግልጽ የወጣ ነገር የለም። የሚታወቀው ግን በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የወጡት ኢድሪስ ዲቤ ላይመለሱ መሄዳቸው ነው።

በሥልጣን ቆይታቸው በአስተዳደሩ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ቃል የገቡትን ያልፈጸሙት ዲቤ ከቀድሞ የቻድ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ በሚያገኙት ያላሰለሰ ድጋፍ ኃይላቸውን አጠናክረው መንበራቸውን አደላድለው ቆይተዋል። በኤኮኖሚው ረገድ የነዳጅ መገኘት ለሀገሪቱ አዎንታዊ ቢሆንም ገንዘቡ የሰፊውን ሕዝብ ኑሮ ለመለወጥ ብዙም አልዋለም። ይልቁንም የፀጥታና የስለላ ተቋማትን ለማጠናከር አውለውታል በሚል በሰፊው ይተቹበታል። ከዚህም ሌላ ዲቤ የአስተዳደሩን ቦታ ከጎሳቸው በመጡ ሰዎች በመሙላትም ይወቀሳሉ። በጎርጎሪዮሳዊው 2004 ያደረጉት የሕገ መንግሥት ማሻሻያም እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2033 ዓ,ም ደጋግመው መመረጥ እንዲችሉ መንገዱን ጠርጎላቸው ኖሯል።

ኢድሪስ ዲቤ
ምስል Ludovic Marin/AP/picture alliance

ወደ ሥልጣን ከወጡ ጀምሮ ዴሞክራሲያ ሥርዓትን ከማምጣት ይልቅ ወታደራዊ ኃይል ግንባታ ላይ ያተኮሩት ዲቤ ወደ ሥልጣነ መንበሩ በዋዛ እንዳልመጡ ሲናገሩ መኖራቸው ይጠቀስላቸል። እሳቸው በተገደሉበት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አማጺ ቡድኖች ጥምረት ቃል አቀባይ ማህማት አሊ ምርጫ በተካሄደበት ዕለት እሳቸው ወደ ሥልጣን በኃይል እንደመጡ በኃይል እናስወግዳቸዋለን ነበር ያሉት።

«እሱ እራሱ በአውሮፕላን ትኬት ወደሥልጣን አልመጣሁም ይል ነበር። ስዚህም ነው እሱን በኃይል አስወግደን ዴሞክራሲን እንመሠርታለን።»

የኢድሪስ ዲቤ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማ በኋላ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የቀድሞው የማሊ የፍትህ ሚኒስትር ማማዱ ኢስማኢላ ኮናቴ ጦር የሚያነሱ በጦር ይወድቃሉ የሚለው በእሳቸው ላይ መፈጸሙን ያመላክታሉ።

«በጦር የመራ ማንም ቢሆን ራሱ በጦር ያልቃል የሚለው መመሪያ በኢድሪስ ዲቤ ላይ ተግባራዊ መሆኑ ግልጽ ነው። እሳቸውም ቢሆኑ አስከሬናቸውን ተራምዶ ካልሆነ በቀር ከሥልጣን መንበራቸው ሊኖር እንደሚችል አልገመቱም።»

ያም ሆነ ይኽ ኢድሪስ ዲቤ ኢትኖ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሥልጣናቸውንም ሆነ ምድሪቱን ተሰናበቱ። በእግራቸውም ልጃቸው ተተካ። 

በቦታቸው የተተካው የኢድሪስ ዲቤ ልጅ
ምስል Presidency of the Republic of Chad

ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዲቤ ሞታቸው ይፋ ከሆነ በኋላ የ37 ዓመቱ ልጃቸው ማህማት ኢድሪስ ዲቤ ለ18 ወራት በቻድ የሽግግር መንግሥቱን እንዲመሩ በጦር ኃይሉ መሰየማቸው ይፋ ሆኗል። የቻድ ሕገ መንግሥት ፕሬዝደንት በሚሞትበት ወቅት የሀገሪቱ ብሔራዊ ጉባኤ ፕሬዝደንት የፕሬዝደንትነት ሥልጣኑን እንዲይዝ እንደሚደነግግ በማሳሰብ የሀገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልጃቸው በቦታቸው መተካታቸውን ተቃውመዋል። ፕሬዝደንቱን በመግደል የሚጠረጠሩት አማጽያኑም እንዲሁ አልተቀበሉትም። የጽንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት የፈጠረባት ፈረንሳይ በበኩሏ የጦር ኃይሉን ውሳኔ ደግፋለች። ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ሀገራቸው ለዴቢ ያላትን አቋም ለማሳየት ይመስላል በቀብራቸው ላይ ሳይቀር ተገኝተዋል።  

ኢድሪስ ዲቤ በሳህልና በቻድ ሐይቅ አካባቢ ለሚካሄደው የፀረ ሽብር ዘመቻ ግንባር ቀደም ሚና ነበራቸው። ሀገራቸውንም በከፍተኛ ጭቆና ለሦስት አስርት ዓመታት በመግዛትም ይታወቃሉ። በአንጻሩ ይኽ የአገዛዝ ዘመናቸው በማዕከላዊ አፍሪቃዊቱ ሀገር በቻድና በአጎራባቾቿ ዘንድም መረጋጋትን አምጥቷል በሚል እውቅና የሚሰጡት አሉ።  በማዕከላዊ አፍሪቃ የቦኮ ሃራምም ሆነ የሌሎች ጽንፈኛ ሙስሊም ቡድኖች እንቅስቃሴ ላይ በተደጋጋሚም ጫና ለማድረግ ዲቤ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። ቻድ በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓ, ምሕረትም በሳህል የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖችን ለመዋጋት የተደራጀው ቡድን አምስት በመባል የሚታወቁት የሳህል አካባቢ ሃገራት ትብብር አባል ሆነች። በዚህ ጊዜ ዲቤ ፈረንሳይ በፀረ ሽብር ውጊያው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራት የጦር ሰፈር አመቻችተው ሰጡ።

ኢድሪስ ዲቤ ምንም እንኳን በዚህ ረገድ የውጭ ድጋፍ ቢኖራቸውም ሀገር ውስጥ ባስተዳደራቸው ቅር የተሰኙ በርካቶች ነበሩ። ለሊቢያ በምትቀርበው የቻድ ግዛት ቲቢስቲ ውስጥ ከጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም አንስቶ ዴሞራሲያዊ ለውጥና አንድነት ለቻድ የተሰኘ ግንባር ተመሠረተ። በቅርቡ ጥቃት የከፈተው ይኽ አማጺ ቡድን ከኢድሪስ ዲቤ ድንገተኛ ሞት በኋላ ወደ ዋና ከተማ ንጃሚና ጉዞ መጀመሩን አስታውቋል። የማጺያኑ እንቅስቃሴም በዚኽች ሀገር ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሃገራትን ጭምር እጅግ ሃሳብ ላይ ጥሏል። ናይጀሪያ በደህንነት ስጋት ድንገት በብዛት የሚሰደዱ የቻድ ዜጎች እንዳይገቡባት ከቻድ ጋር በሚያገናኛት የድንበር አካባቢ የጦር ኃይሏን ወዲያው ነው ያጠናከረችው።

የዶቼቬለ የምዕራብ አፍሪቃ ዘጋቢ ፍሬድ ሙቩኒ እንደሚያምነው የዲቤ ሞት ቻድን መስቀለኛ መንገድ ላይ አድርሷታል።  እሱ እንደሚለውም ሀገሪቱ ቀድሞውንም ቀውስ ውስጥ ነበረች። በአንድ ወገን ተቃዋሚዎች በምርጫው አንሳተፍም አሉ፤ በሌላ በኩል አማጽያን ከሊቢያ በኩል በቻድ ላይ ጥቃት ከፈቱ፤ ላለፉት 30 ዓመታት ያለምንም የተጨበጠ ቃል የጸጥታ ስጋት፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና ስቃይ በምድሪቱ ተንሰራፋ። እንደጋዜጠኛው ከዚህ የባሰ አስጊው ሁኔታ ወጥቶ ወደፊት እንዴት መሄድ ይቻላል የሚለው ነው።

ውጥረት በንጃሚና
ምስል Str/AFP

በዚኽ ሁሉ መሀል የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ሀገራዊ ውይይት እንዲካሄድ እየጠየቁ ነው። በቻድ የብዙሃን ፓርቲዎች አስተባባሪ እና የፍራንኮፎን እንዲሁም የተመድ የሰላም አምባሳደር የሆኑት አብደርማኔ ዳጃሳንቤይ የሀገሪቱ ጦር ኃይል ታንኮችን ዋና ከተማ ውስጥ ካስገባ በኋላ ጦርነት ቀርቶ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ተማጽኖ አቅርበዋል።

«ሁኔታው አሳሳቢ ነው። እንዲያበቃ እመኛለሁ። እርስ በእርሳችን ተነጋግረውን መፍትሄ መፈለግ አለብን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህ ውይይት እንዲካሄድ እንዲረዳ ጥሪ አቀርባለሁ። ሁሉም ነገር ከመበላሸቱ በፊት ይኽ ሁሉ ማብቃት አለበት። አሁን በጦር መሣሪያ ኃይል ሥልጣን የሚያዝበት ጊዜ ላይ አይደለንም። በዋና ከተማዋ ጦርነት እንዳይካሄድ ማድረግ አለብን። ማንም አሸናፊ ቢሆን ሁላችንም ተሸናፊዎች ነው የምንሆነው።»

የ68 ዓመቱ የቀድሞ የቻድ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዲቤ ትናንት ዓርብ ዕለት በዋና ከተማዋ መንግሥታዊ ክብር ያጀበው ሽኝት ተደርጎላቸው በትውልድ መንደራቸው ግብዓተ መሬታቸው ተፈጽሟል። በጠንካራ ወታደራዊ መዳፋቸው ሥር ሦስት አስርት ዓመታትን የገዟት በአማጽያን እና በጽንፈኛ ታጣቂዎች የታጀበች ሀገራቸው የቻድ ዕጣ ፈንታ ግን አሁንም በስጋት የታጀበ ነው። በእግራቸው የተተኩት የ37 ዓመቱ ልጃቸው የወረሱትን ሥልጣን በዋዛ ላይለቁ እንደሚችሉ የሚገምቱ አሉ። የአፍሪቃ ህብረትን ግን የሽግግር ሂደቱን በቅርብ አግዛለሁ እያለ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ