1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ የተስተጓጎለው ሰብዓዊ ድጋፍ

ቅዳሜ፣ ጥር 7 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ ያልተቋረጡ ግጭቶች በእጅጉ አስፈላጊ የተባለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ እንቅፋት መሆኑን የተመድ የአስቸኳይ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ አስታወቀ፡፡ድርጅቱ ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያገለግለው የአብዓላ-መቀሌ ኮሪደር በግጭት ቀጠናነት መያዙ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ከገባ ወር እንዲቆጠር አስገድዷል ብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/45Zod
Äthopien Militär in der Amhara Region
ምስል Seyoum Getu/DW

አሳሳቢው የኢትዮጵያ የሰብአዊ ሁኔታ ፤ የተመድ እና የመንግስት ምላሾች

በሰሜን ኢትዮጵያ ያልተቋረጡ ግጭቶች በእጅጉ አስፈላጊ የተባለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ እንቅፋት መሆኑን የተመድ የአስቸኳይ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያገለግለው የአብዓላ-መቀሌ ኮሪደር በግጭት ቀጠናነት መያዙ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ከገባ ወር እንዲቆጠር አስገድዷል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በፊናው መንግስት ያልተገደበ የእርዳታ ቁሳቁስ ወደ ትግራይ እንዲገባ ቢፈቅድም ህወሐት በአባዓላ በኩል የቀሰቀሰው ግጭት የእርዳታ ማጓጓዝ ስራውን እንዳስተጓጎለው ነው የሚገልጸው፡፡

በሌላ በኩል በትግራይ በተደጋጋሚ በሚፈጸመው የአየር ጥቃትም ሰላማዊ ዜጎች ይጠቃሉ መባሉንም መንግስት እያስተባበለ ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት የአስቸኳይ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ነገሮች የማይገመቱ እና ውጥረት እንደተሞላ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በትግራይ ደቡባዊ ዞን በዋጃ-ጥሙጋ፣ አዲአውሌ እና ሃዱሽ ቅኝ፤ ከሽራሮ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙት ሲገም ኮፎሎ፣ አዲ-ፀረር እና ገምሃሎ ግጭቶች መኖራቸውን ያመለክታል ሪፖርቱ፡፡ በአማራ ክልል ዋግሂምራ ዞን ሰቆጣ እና አበርጌሌ ወረዳዎችም፤ በሰሜን ጎንደር አዲ-አርቃይ ውጊያ መቀጠሉን አመልክቷልም፡፡ በአፋር በአባዓላ እና ትግራይን በሚያዋስኑ አከባቢዎች ቅጭቶች መዘገባቸውንና ባጠቃላይም ሰብዓዊ ድጋፍን ማስተጓጎሉንና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማስፈር እዳይቻል ማድረጉንም አትቷል፡፡

Äthopien Militär in der Amhara Region
ምስል Seyoum Getu/DW

በትግራይ የሚደረግ የአየር ጥቃት ከጥቅምት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መስተዋሉን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በምዕራባዊ የትግራይ ዞን ከሚገኘው የሲሁል ሆስፒታል አገኘሁ ባለው መረጃ ከ7 ቀናት በፊት በደደቢት ከተማ በደረሰ የአየር ጥቃት ህጻናትና ሴቶች የሚገኙበት በትንሽ ቁጥር 138 ሰዎች መጠቃታቸውን አመልክቷል፡፡ ሪፖርቱ ሁሉም ጉዳተኞች ከምዕርብ ትግራይ የተፈናቀሉ መሆኑንና መጠለያቸው ጭምር መውደሙን አውስቷል፡፡ በእርግጥ የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያው ሪፖርት በአከባቢው ባለው የፀጥታ ችግር የተነሳ በቦታው ተገኝቶ ድርጊቱን ለማረጋገጥ አለመቻሉን አክሎ ያትታል፡፡

በተመሳሳይ ከአራት ቀናት በፊት በማይፀብሪ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ከመጎዳታቸው ባለፈ ህይወታቸው ያለፈም መኖሩን ያወሳል፡፡ ይሁንና የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪዎች በኮሚዩኒኬሽን ግንኙነት ችግር ማረጋገጥ አለመቻሉን አክሏል ይህ ሪፖርት፡፡ ከ10 ቀናት በፊት ግን በማይአይኒ የስደተኞች ካምፕ ሶስት ሰዎች በጥቃቱ መጎዳታቸውን የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማረጋገጡን ገልጸል፡፡

በመሆኑንም የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ተቋማት በነዚህ አከባቢዎች ከመስተጓጎሉም በተጨማሪ ተፈናቃዮችን ወደየ ቀዬያቸው የመመለሱን ሂደት ፈታኝ ማድረጉ ነው የሚገለጸው፡፡

Äthopien Militär in der Amhara Region
ምስል Seyoum Getu/DW

ይሁንና አስተያየተቻውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ጄኔራል ባጫ ደበሌ እንደሚሉት በትግራይ የጥቃት ኢላማ የሚሆን ሰላማዊ ዜጋ የለም፡፡ 

የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ሳምንታዊ ሪፖርቱ አክሎ እንዳብራራው፤ ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ በብቸኝነት የሚያገለግለው የአፋር ሰመራ-አባዓላ-መቀሌ ኮሪደር የድጋፍ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ጉዞ በአከባቢው ባገረሸ ግጭት መስተጓጎሉን አመልክቷል፡፡ የድጋፍ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ ከገቡ አንድ ወር መድፈኑን የገለጸው ድርጅቱ፤ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ መቀሌ ለመጓዝ የሚጠባበቁ 68 ተሸከርካሪዎች መተላለፊያ በማጣታቸው በሰመራ ቆመዋል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ባጠቃላይም ከባለፈው ሰኔ ጀምሮ 1,338 ተሸከርካሪዎች ወደ ትጋረይ ገብተዋል፡፡ ይህም በክልሉ ድጋፍን ይሻሉ ከተባሉ 5.2 ሚሊየን ዜጎች 10 በመቶውን ብቻ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን በማከል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ስለእርዳታ መስተጓጎል እና ወደ ትግራይ የማጓጓዣ መንገድ መጥፋት በዶይቼ ቬለ ተጠይቀው፤ ለችግሩ መፈጠር በአባዓላ አካባቢ ግጭት በመጫር አከባቢውን የስጋት ቃጣና በማድረግ ሕወሓትን ከሰዋል፡፡ 

Äthopien Militär in der Amhara Region
ምስል Seyoum Getu/DW

የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያው ሪፖርቱ በትግራይ እየከፋ መጥቷል ላለው የሰብዓዊ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ሌላውና ዋነኛው ተግዳሮት የሆነው የነዳጅ እጥረት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም የሰብዓዊ ድጋፍ ባለሙያዎች በከተማ እና ከተሞች ዙሪያ ብቻ መወሰናቸውን አብራርቷል፡፡ ከወርሃ ነሃሴ ወዲህ ላለፉት 5 ወራት ነዳጅ ወደ ትግራይ አልገባም ያለው የሰብዓዊ ድርጅቱ ሪፖርት በዚሁ ሳቢያ የእርዳታ ድርጅቶች በእጃቸው ያለውን የምግብ ቁሳቁሶች ማከፋፈል እንኳ አለመቻላቸውን ነው የገለጸው፡፡

በአማራ ክልልም የሰብዓዊ ድጋፍ በተለይም በሰሜን ወሎ እና ዋግሂምራ ዞኖች አስከፊ መሆኑንና በዚህም አካባቢ የነዳጅ እጥረት አንዱ ተግዳሮች መሆኑን አመልክቷል፡፡ በነዚህ አካባቢዎች 35,000 ያህል ተፈናቃዮች እየተረዱ መሆኑንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ባለፉት 3 ወራት ያለ እርዳታ ወደ ቀየያቸው መመለሳቸውን ሪፖርቱ አክሎ ጠቅሷል፡፡

በአፋርም ኤሬብቲ፣ በርሃሌ እና ታላላክ 23,000 ተፈናቃዮች ወደ ቀዬቸው ቢመለሱም የጸጥታ ስጋቶች አሁንም በመጋረጣቸው ሰብዓዊ ድጋፎችን ማዳረስ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ድርጅቱ በሳምንታዊ ሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ