1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል ዉስጥ ትምሕርት አልተጀመረም

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2015

በትግራይ ክልል አሁንም አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች በተለመደ ስራቸው ላይ ሳይሆኑ የተፈናቃዮች መጠልያ ጣብያዎች ሆነው እያገለገሉ ነው። በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር በተደጋጋሚ ተደረጉ የተባሉ ጥረቶች እስካሁን አልሰመሩም

https://p.dw.com/p/4PR9T
Äthiopien Bildungsbüro der Region Tigray
ምስል DW/Million Haileselassie

ትምሕርት ከተቋረጠ ከ3 ዓመት በልጦታል

ትግራይ ክልል ይደረግ በነበረዉ ጦርነት ምክንያት ከ3 ዓመታት በላይ የተቋረጠዉ መደበኛ የትምሕርት አገልግሎት በመጪዉ ግንቦት ለማስቀጠል ማቀዱን የክልሉ ትምሕርት ቢሮ አስታወቀ።ቢሮዉ እንደሚለዉ የፌደራሉ መንግስት የመምሕራን ደሞዝን ጨምሮ ለመማር-ማስተማሩ ሒደት የሚያስፈልገዉን የበጀት ድጋፍ እንዲያደርግ ቢሮዉ ጠይቋል።ትግራይ ክልል 2.3 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምሕርት ካቋረጡ 3 ዓመት በልጧቸዋል።

በትግራይ ያሉ መምህራን ደሞዝ የሚያገኙበት ሁኔታ ከተመቻቸ እስከ መጪው ግንቦት ወር ድረስ በትግራይ መደበኛ ትምህርት የማስጀመር እቅድ መያዙም ተጠቁሟል። በትግራይ 2 ነጥብ 3 ሚልዮን ተማሪዎች ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ውጭ ከሆኑ ከሶስት ዓመት በላይ አልፏል።

በኮረና እና ጦርነቱ ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት በትግራይ ተቋርጦ ያለው መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት፣ ግጭቱ ከቆመ ወራት በኃላም ቢሆን እስካሁን አልተጀመረም። በትግራይ አሁንም አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች በተለመደ ስራቸው ላይ ሳይሆኑ የተፈናቃዮች መጠልያ ጣብያዎች ሆነው እያገለገሉ ነው። በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር በተደጋጋሚ ተደረጉ የተባሉ ጥረቶች እስካሁን አልሰመሩም። የ18 ዓመት ታዳጊው ፋኑኤል ሃይለስላሴ በትግራይ መደበኛ ትምህርት ከመቋረጡ በፊት አስረኛ ክፍል ተማሪ እንደነበር ገልፆልናል። ታዳጊው ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ከትምህርት ውጭ ሆኖ ህልምና ምኞቱ መደናቀፉ ይናገራል። "መጀመርያ ላይ በኮረና ምክንያት ነበር ትምህርት ያቋረጥነው። ቀጥሎ ጦርነቱ ተከተለ። ይሀው እስካሁን ትምህርት አልጀመርንም" ይላል ያነጋገርነው ተማሪ ፋኑኤል። 

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚንስቴር
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚንስቴር ምስል Solomon Muchie/DW

ይህን ታዳጊ የመሰሉ በተለያየ የትምህርት ደረጃ የነበሩ 2.3 ሚልዮን የትግራይ ተማሪዎች ለተከታታይ ዓመታት ከመደበኛ የትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው እንዳለ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ይገልፃል። በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹ ላይ ተስፋ ማጣት፣ መደበኛ የትምህርት ዕድሜ ማለፍ ጨምሮ በርካታ ችግሮች እየተስተዋሉ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው የተማሪ ልጆች ወላጆች እና መምህራን ይገልፃሉ። 

ከሰላም ስምምነቱ በኃላ በትግራይ ቅድሚያ ሊጀመሩ ከሚጠበቁ መካከል ትምህርት አንዱ ነው። የትግራይ ትምህርት ቢሮ እንደሚለው በትግራይ ትምህርት ለማስቀጠል ጥረት ላይ ቢሆንም በበጀት እጦት ምክንያት፣ የመምህራን ያለፉት 21 ወራት ደሞዝ ባለመክፈሉ እስካሁን ትምህርት ሊጀመር አለመቻሉ ይገልፃል። ይህ ችግር ለመፍታት ከፌዴራሉ መንግስት ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ንግግር መጀመሩ የነገሩን የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳኘው አይጠገብ፥ ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑም ጠቁመዋል። አቶ ዳኘው "ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች እና አመራሮች ጋር ንግግር ተጀምሯል። ይህ በጎ ጅምር ነው። ወደ ፊት ሊያስኬደን የሚችል የጋራ እቅድ አዘጋጅተናል። ስለዚህ በጋራ እቅዱ መሰረት ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችለንን የበጀት ጥያቄ አቅርበናል። የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጉዳዩ አይተው ውሳኔ ይሰጡበታል" ብለዋል።

እንደ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ገለፃ የመማር ማስተማር ሂደቱ ማስቀጠል የሚቻልበት በጀት በቅርቡ ከተገኘ፣ እስከ ግንቦት ወር ድረስ በትግራይ ለዓመታት የተቋረጠ ትምህርት ለማስጀመር እቅድ አለ ።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር