1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ፣አፍሪቃ በዳቮስ፣የኮንጎ ጦርነት

ቅዳሜ፣ ጥር 13 2015

በየአመቱ ዳቮስ ስዊዘርላንድ ዉስጥ በሚደረገዉ የዓለም የንግድ ጉባኤ ላይ አፍሪቃና አፍሪቃን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሰፊ ዉይይትና ክርክር ይደርግባቸዋል።የአፍሪቃ መንግስታትና ኩባንዮች ግን ባለሐብትና ሸማች ለማግኘት ምርቶቻቸዉን ሲያስተዋዉቁ ብዙም አይታዩም።

https://p.dw.com/p/4MWGs
ዳቮስ 2023
ዳቮስ 2023ምስል Dursun Aydemir/AA/picture alliance

አፍሪቃ፣በዳቮሱ የምጣኔ ሐብት ስብሰባ፤ የኮንጎ ጦርነት

 

አፍሪቃ በዳቮስ የምጣኔ ሐብት መድረክ
ከዳቮሱ ረጅም፣ሰፊ፣ደማቅ የእግረኛ መንገድ ዳርቻ ከተገጠገጡት መለስተኛ የትርኢት ቤቶች መሐል «የአፍሪቃ ቤት» የሚባለዉን እልፍኝ ማግኘት ከባድ ነዉ።ስም አልተለጠፈበትም።ባንዲራ ወይም አርማ የለዉም።እንደ ሁሉም እልፍኞች የዕለቱን አጀንዳዎች የሚዘረዝር ስክሪን ብቻ ተለጥፏል።በቃ ምናልባት አፍሪቃ በዓለም ምጣኔ ሐብት ጉባኤ ያላት ዉክልና ትንሽነቱን ጠቋሚ ይሆን?

ወደ እልፍኙ ሲገቡ ግን አፍሪቃ ደምቃ ትታያለች።ቅይጥ፣ አንፀባራቂ ቀለሞችዋ፣ ባሕልና ወጓ ዓይነት ባይነት ተንቆጥቁጣል።
ባአንድ የቡድን ዉይይት ላይ የተወከለ አንድ አፍሪቃዊ «አፍሪቃ ዉስጥ የተመረተ ቸኮላትን ማን ይበላዋል ይላሉ» አለ-አሉ የሰሙ «እነግራቸዋለሁ» ቀጠለ አፍሪቃዊዉ ተናጋሪ «አፍሪቃዉያን ይበሉታል» ብዬ።
የቡድን ዉይይቱ የአፍሪቃን የዕድገት ታሪክ ለዓለም ባለሐብቶች ለማተዋወቅ «የአፍሪቃ ቤት» ከሚያዘጋጃቸዉ በርካታ ትዕይንቶች አንዱ ነዉ።
«የተካፋዩ ብዛት እጅግ ከፍተኛ ነዉ» ትላለች የአፍሪቃ ቤት የንግድ ጉዳይ ኃላፊ ሐያት አንቶኚኒ። ቀጠለች-----«ብዙ ሰዎች ጠንካራ ተሻሪኮዎች ማግኘታቸዉን እየሰማን ነዉ።ነገሮች በትክክለኛዉ አቅጣጫ እየተጓዙ ይመስላሉ።»
በየአመቱ ዳቮስ ስዊዘርላንድ ዉስጥ በሚደረገዉ የዓለም የንግድ ጉባኤ ላይ አፍሪቃና አፍሪቃን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሰፊ ዉይይትና ክርክር ይደርግባቸዋል።የአፍሪቃ መንግስታትና ኩባንዮች ግን ባለሐብትና ሸማች ለማግኘት ምርቶቻቸዉን ሲያስተዋዉቁ ብዙም አይታዩም።
የዓለም የምጣኔ ሐብት 50ኛ ጉባኤ በ2020 (ዘመኑ በሙሉ እግአ) ሲደረግ የተመሠረተዉ «የአፍሪቃ ቤት» ነባሩን አስተሳሰብና አሰራር ለመቀየር እየጣረ ነዉ።ቤቱ የአፍሪቃ የንግድ ድርጅቶችና ጀማሪ ኩባንዮችን ለማበረታት፣ምርቶቻቸዉን ለማስተዋወቅና ከሌላዉ  ዓለም ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያደርጋል።
«ሌሎችን አንጠብቅም» አለ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙና የቴክኖሎጂ ድርጅት ባለቤቱ ዊል አይ አም።የአፍሪቃ ቤት ተባባሪ ሊቀመንበርም ነዉ።ዊል።
«አንጠብቅም።ሌላ ሰዉ እንዲያደርግልን ለምን እንጠብቃለን።እየታዩ ነዉ።ናጄሪያ እየታየች ነዉ።ጋና እየታየች ነዉ።ሌሎችም።አፍሪቃ ማራኪ ናት።ዉብ ናት።እርግጥ ነዉ የትም ስፍራ ብዙ ፈተናዎች አሉ።አፍሪቃም ብዙ ፈተናዎች አሉባት።የዚያኑ ያክል በርካታ ሳቢ፣ ማራኪ ነገሮችም አሏት።»
በቴክኖሎጂዉ መስክ አፍሪቃ ያባከነችዉን ጊዜ ለማካካስ ወጣቶችዋ የሚጣደፉ ይመስላሉ። በተለይ የመረጃ ቴክኖሎጂ (IT) እየተስፋፋ ነዉ።በቅርቡ የተጠናቀረ ዘገባ እንዳመለከተዉ ናጄሪያ፣ደቡብ አፍሪቃ፣ኬንያና ግብፅ ዉስጥ በ2021 የተመሰረቱ ጀማሪ ኩባንዮች 2 ቢሊዮን ዶላር ተገምተዋል።
የዋሽግተኑ የታንበርድ ትምሕርት ቤት የአስተዳደር ፕሮፌሰር ላንድሬይ ሲግኔ «በክፍለ ዓለሚቱ ዉስጥ የምናየዉ ከሌሎቹ በተጨማሪ ብዙ መዋለ ነዋይ ጀማሪ ኩባንዮች ላይ እየወጣ ነዉ።ምክንያቱም ባለሐብቶች እጥረት ባለበት መስክ መሳተፍ ይፈልጋሉ።ዕድሎች እንዳሉ ይታያቸዋል።» ይላሉ።
ኬንያ ዉስጥ በ2007 የተጀመረዉ በተንቀሳቃሽ ስልክ ገንዘብ የማዘዋወር ስልት (ቴክኖሎጂ) M-Pesa ከፍተኛ ዉጤት ማሳየቱ ብዙ የIT ባለሙያዎችን ለአዳዲስ ፈጠራ አነሳስቷል።«ቅርንጫፍ የለሽ ባንክ» የተሰኘዉ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ማዘዋዋሪያ ሥልት ከኬንያ ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢ (GDP) 40% ይዘዋወርበታል።
 የዳቮሱ የአፍሪቃ ቤት ሰሞኑን ካስተናገዳቸዉ ስብሰባዎች አንዱ የመንግስታት ፖሊሲ አዉጪዎችና የክሪፕቶ ኩባንዮች ያደረጉት መደበኛ ያልሆነ ስብሰባ ነዉ።ስብሰባዉ መደበኛ ባይሆንም ወረቀትና ሳንቲም አልባዉ ገንዘብ አፍሪቃ ዉስጥ ስራ ላይ እንዲዉል የሚደረገዉ ማግባባት፣ ግፍትና ጥረት አካል ነዉ።
ናጄሪያ ቤትኮይን በመባል የሚታወቀዉን የክሪፕቶ ገንዘብን በብዛት ከሚጠቀሙ ጥቂት የዓለም ሐገራት አንዷ ናት።ቢቲኮን ሕጋዊ የመለዋወጪያ ገንዘብ እንዲሆን ከኤልሳልቫዶር ቀጥሎ የደነገገች ብቸኛዋ ሐገር ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ናት።
በዲጂታል የሚደረገዉ የገንዘብ ልዉዉጥ ለፈጣን የንግድ ዝዉዉር፣ ለግልፅነትና ቅልጥፍና ይረዳል ነዉ-የሚባለዉ።የሚቃወሙና የሚጠራጠሩት ግን ብዙ ናቸዉ።ኡቡንቱ ትራይብ የተሰኘዉ ኩባንያ መስራችና ባለቤት ማማዶ ቱሬ እንደሚለዉ አፍሪቃ በተቀረዉ ዓለም ዘንድ የሚገባትን ያክል አልተዋወቀችም።
«እንደሚመስለኝ አፍሪቃ በምትችለዉ ወይም በሚገባት ልክ አልተወከለች ወይም ማግኘት የሚገባትን ያክል ጥቅም አልተሰጣትም»----ባይነዉ ቱሬ----«ስላለዉ ዕድል የተሰራጨዉ መረጃ በጣም ቁንፅል ነዉ።የአፍሪቃ ቤትን የመሰረትነዉም አሐጉሪቱ ማድረግ የምትችለዉንና የምታደርገዉን ለማስተዋወቅና ለማንፀባረቅ ነዉ።» 
«የአፍሪቃ ቤት» በተመሰረተ 2 ዓመቱ ብዙ ስብሰባዎችን፣ትርዒቶችን፣ ትዉዉቆችን አስተናግዷል።እራሱን ከዉጪ ያልስተዋወቅበት ምክንያት ግን አይታወቅም። 

የዳቮሱን ጉባኤ የሚቃወሙ ሰልፈኞች
የዳቮሱን ጉባኤ የሚቃወሙ ሰልፈኞችምስል Arnd Wiegmann/REUTERS
የዳቮሱ ጉባኤ ካስተናገዳቸዉ ዉይይቶች አንዱ
የዳቮሱ ጉባኤ ካስተናገዳቸዉ ዉይይቶች አንዱምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance
የአፍሪቃ ቤት-ዳቮስ
የአፍሪቃ ቤት-ዳቮስምስል DW

የኮንጎ ጦርነት
የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦርነት የርስበርስ፣ የአጎራባች፣የአፍሪቃ፤ የዓለምም ሆኖ ያቺን ሰፊ፣ለም፣ሐብታም ሐገር አፈር ደቼ እያስጋጠ ቀጥሏል።አንዴ ኮንጎ፣ሌላ ጊዜ የቤልጂግ ኮንጎ፣ኋላ ዛኢር፣በቅርቡ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ--ጊዜዉ ይነጉዳል።ስም፣ገዢ፣ ትዉልዷ ይለዋወጣል ለእልቂት ፈጅቱ  ግን ትናንት ዛሬ-ዛሬም ትናንት ነዉ።
ጦርነቱ በ1990ዎቹ አጋማሽ (ዘመኑ በሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ብዙ የአፍሪቃ ሐገራትን በማሳተፉ «የአፍሪቃ ትልቁ ጦርነት» ተብሎ ነበር።በ1997 አበቃ ተባለ።ግን ተዋጊዎች ለአንድ ዓመት አረፉና በ1998 እንደገና ዉጊያ ገጠሙ።
በዚሕም ጦርነት ከሩዋንዳ እስከ ናሚቢያ፣ ከአንጎላ እስከ ብሩንዲ የሚገኙ 10 የአፍሪቃ መንግስታት፣ 17 አማፂያን ከዲሱ ዉጊያ ተሞጀሩበት።ይሄኔ ስም አዉጪያዎች «ሁለተኛዉ የአፍሪቃ ትልቅ ጦርነት» አሉት።
ስም አዉጪዎች ስጥለዉ-ስም ሲያነሱ ጦርነቱ ሚሊዮኖችን ፈጅቶ በ2003 ጋብ አለ።በ2008 ይፋ የሆነ ጥናት አንዳረጋገጠዉ ሁለተኛ ዙር ጦርነትና በጦርነቱ መሐል የተሰራጨዉ በሽታ ከ5.4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።የቆሰለ፣የተፈናቀለና የተደፈረችዉ ቁጥር ከሟቾቹ እጥፍ ይሆናል።
ከ2005 በኋላ የዉጪዎቹ መንግስታት ጦር በከፊል ቢወጣም እንደበሽታዉ ሁሉ በየጦርነቱ መሐል የተፈለፈሉ ከ120 የሚበልጡ አማፂያን ከመንግስት፣ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦርና እርስበራሳቸዉ ሲተጋተጉ ቆይተዉ በቅርቡ «ሶስተኛዉን የአፍሪቃ ጦርነት» ገጠሙ።በዚሕ ጦርነት ሩዋንዳ ከቀድሞ ወዳጆችዋ ዩጋንዳና ብሩንዲ ተነጥላ ግን M23ን የመሳሰሉ የምስራቃዊ ኮንጎ አማፂያንን አስቀድማ የኮንጎ መንግስት ጦርና ደጋፊዎቹን ትወጋለች።
ኬንያ፣ብሩንዲ፣ዩጋንዳና ደቡብ ሱዳን የምስራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብ (EAC) በሚል ስም የኮንጎ መንግስትን ደግፎ በሩዋንዳ የሚረዱ አማፂያንን የሚወጋ በሺሕ የሚቆጠር ጦር አዝምተዋል ወይም ለማዝመት ቃል ገብተዋል።የዉጊያዉ ክብደት-ቅለት፣ የሚሞት፣የሚፈናቀለዉ ሕዝብ ስንትነት፣ መከራ ጥናቱ ሲዘረዘር በቀደም ኡቱሪ ግዛት ዉስጥ በጅምላ የተቀበሩ ሰዎች አስከሬን ይቆጠር ያዘ።
«ይሕ የጅምላ ቀብር ደግሞ ከየት የመጣ ነዉ?» አሉ የኢቱሪ ግዛት የሰላማዊ ሰዎች አስተባባሪ ዲዉዶኔ ሎሳዴካና ለሳቸዉም ግራ ነዉ።
««ይሕ የጅምላ ቀብር ደግሞ ከየት የመጣ ነዉ? ሰዎችን በጅምላ ከቀበርን ገና ሳምንትም አልሞላን።ከሌንዱም ሆነ ከሔማ መንደሮች የጠፋ ወይም የተገደለ ሰዉ አለ የሚል መልዕክት ወይም ጥቆማ አልደረሰንም። አሁን ስለተገኘዉ ጅምላ ቀብር ምን ማለት እንዳለብን አናዉቅም።የተፈፀመዉ ነገር በገለልተኛ ወገን መመርመር አለበት።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ቡኒያ ከተባለችዉ የኢቱሪ ትልቅ ከተማ በስተምስራቅ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ 2 መንደሮች ዉስጥ 2 ጅምላ ቀብር ተገኝቷል።አንደኛዉ ዉስጥ 42፣ ሌለኛዉ ዉስጥ ደግሞ 7 አስከሬን ተቆብሮባቸዋል።የገዳይ ቀባሪዉ ማንነት በዉል አልታወቀም።
ይሁንና በአካባቢዉ የኮንጎ ልማት ትብብር (CODECO) የተባለ ነዉጠኛ ታጣቂ ቡድን ሸምቋል።በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ ኃላፊ አብዱል አዚዝ ትዮዬ እንደሚሉት ሟቾቹን በጅምላ የገደለዉ ወገን ማንነት በዉል አይታወቅም።
ይሁንና ኃላፊዉ አክለዉ እንዳሉት እንዳሉት የተገኙት ፍንጮች፣ ገዳዮች፣ አንድም CODECO አለያም የዛኢር ቡድን የሚባሉት ታጣቂዎች መሆናቸዉን ያመለክታሉ።
 «የተገኘዉን እዉነታ ባለፈዉ ሰኞ መዝግብናል።ባለፈዉ ሳምንት ዕሁድ ወደአካባቢዉ  የተጓዘዉ ቡድን የጅምላ መቃብሩንና የተቀበሩትን ሰዎች ቁጥር አጣርቶ ተመልሷል።ሁኔታዉ በጣም አሳሳቢ ነዉ።ድጁጉ እና ማሐጊ ግዛቶች ዉስጥ ጥቃቶችና አፀፋ ጥቃቶች ከተፈፀሙ ወዲሕ የአካባቢዉ ሁኔታ አደገኛ ሆኗል።ግድያዉም የተፈፀመዉ በዛኢር ቡድን ወይም ከCODECO ባፈነገጠ አንጃ ሊሆን ይችላል።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  እንዳስታወቀዉ ጅምላ መቃብሮቹ በተገኙበት አካባቢ የCODECO ታጣቂዎች ባለፈዉ ሮብ አንድ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያን አጥቅተዉ ሰባት ተፈናቃዮች ገድለዋል።ሰባቱ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የዓለም አቀፉ ድርጅት ባካባቢዉ አንድ ተነጣይ ሠራዊት ማስፈሩን የድርጅቱ ምክትል ቃል ቀአባይ ፋርሐን ሐቅ አስታዉቀዋል።
ኢቱሪ ግዛት ዉስጥ ከ1.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ተፈናቃዮች ሰፍረዋል።የሮቡን ጥቃት ያደረሰዉ CODECO የተባለዉ አማፂ ቡድን ባለፈዉ ዓመት የካቲትም 50 ሰላማዊ ሰዎችን በመደዳ ገድሎ ነበር።
ቡድኑ ባለፈዉ ሰኔ ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉን ማቆሙን አዉጆ ነበር።ይሁንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ጨካኙ ቡድን ካለፈዉ ታሕሳስ ወዲሕ ብቻ 195 ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።
ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ ከ20 የሚበልጡ ሐገራት ያዘመቱት ከ18 ሺሕ በላይ ሰማያዊ መለዮ ለባሽ ሰራዊት ሰፍሯል።በቅርቡ ደግሞ ወደ 3 ሺሕ የሚጠጋ የምስራቅ አፍሪቃ ሐገራት ጦር ተጨምሮበታል።ሰላማዊ ሰዎችን በጀምላ ከመረሸን ያዳነ ግን የለም።በየጊዜዉ የሚፈራረቀዉ ጦር የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት አለማዳኑ ያበሳጨዉ የጎማ ከተማ  ሕዝብ  የዉጪዉ ጦር እንዲወጣለት ባለፈዉ ሮብ እንዳደረገዉ ባደባባይ ሰልፍ ቢጠይቅ ይፈረድበት ይሆን?

የዉጪ ጦር እንዲወጣ የሚጠይቀዉ ሰልፈኛ-ጎማ
የዉጪ ጦር እንዲወጣ የሚጠይቀዉ ሰልፈኛ-ጎማምስል Justin Makangara/REUTERS
የኮንጎ ዉድመት
የኮንጎ ዉድመትምስል Zanem Nety Zaidi/Xinhua/IMAGO
የምስራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብና የM23 ጦር አዛዦች ድርድር
የምስራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብና የM23 ጦር አዛዦች ድርድርምስል Guerchom Ndebo/AFP

ነጋሽ መሐመድ