1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የአፍሪቃ የማስጠንቀቂያ ሥልት፤ አዲሱ የቻድ ፕሬዝደንት

ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 2016

የሚታወቀዉ ኢትዮጵያ ዛሬም አስቀድመዉ ሊከላከሉት በሚችሉት ድርቅ፣ ረሐብና ጎርፍ ሺዎች መሞት፣ሚሊዮኖች መራብና መፈናቀላቸዉ ነዉ።ባጋመስነዉ የግሪጎሪያኑ 2024 ኔቸር በተባለ የሳይንስ መፅሔት ላይ የታተመ አንድ መጣጥፍ እንደሚያመለክተዉ አፍሪቃ ዉስጥ በጎርፍ አደጋ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር አዉሮጳና ሰሜን አሜሪካ ከሚሞተዉ በአራት እጥፍ ይበልጣል።

https://p.dw.com/p/4gGNf
መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትዮ የቀድሞዉ የቻድ መሪ የኢድሪስ ዴቢይ ልጅ ናቸዉ
የቻድ የቀድሞ ወታደራዊ መሪ መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሆነዉ ቃለ መሐላ ፈፀሙምስል Israel Matene/REUTERS

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የአፍሪቃ የማስጠንቀቂያ ሥልት፤ አዲሱ የቻድ ፕሬዝደንት

 

የአፍሪቃ ሐገራት በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጮች ናቸዉ።ድርቅ፣የዉሐ ሙላት፣ የአሸዋ አዉሎ ንፋስ የመሳሰሉ የዓየር ንብረት ቀዉሶች በሌሎቹ ክፍለ ዓለማት በተደጋጋሚ ቢደርሱም ከፍተኛ ጥፋት የሚያደርሱት ግን  አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ።ባለሙያዎች እንደሚሉት የተፈጥሮ አደጋዎቹ አፍሪቃ ዉስጥ ከፍተኛ ሕይወት የሚያጠፉ፣ ብዙ ሕዝብ የሚያፈናቅሉትም ሆነ የምጣኔ ሐብት ቀዉስ የሚያደርሱት አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት አስተማማኝ የቅድመ ትንበያ ሥርዓትና በቂ ዝግጅት ሥለሌላቸዉ ነዉ።

የዶቸ ቬለዋ ኬይት ዎከር እንደፃፈችዉ የአፍሪቃ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት በዘመኑ ቴክኖሎጂ ካልተደገፈ፣ ካልተሻሻለና ካልተጠናከረ አፍሪቃ ለተፈጥሮ መቅሰፍት «እጇን ለመስጠት» ትገደዳለች።

የተፈጥሮ መቅሰፍትና የቅድመ ማስጠንቀቂያ 

 

ኢትዮጵያ በ1976/77ቱ በረሐብበመቶ ሺ በአንዳዶች ግምት ሚሊዮን የሚጠር ዜጎቿ ካለቁባት በኋላ ቢያንስ ለድርቅ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ዘርግታ ነበር።የያኔ ባለሥልጣናት ከአፍሪቃ ዘመናይ ያሉት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ዛሬ ይሥራ አይስራ በዉል አይታወቅም።

የሚታወቀዉ ኢትዮጵያ ዛሬም አስቀድመዉ ሊከላከሉት በሚችሉት ድርቅ፣ ረሐብና ጎርፍ ሺዎች መሞት፣ሚሊዮኖች መራብና መፈናቀላቸዉ ነዉ።ባጋመስነዉ የግሪጎሪያኑ 2024 ኔቸር በተባለ የሳይንስ መፅሔት ላይ የታተመ አንድ መጣጥፍ እንደሚያመለክተዉ አፍሪቃ ዉስጥ በጎርፍ አደጋ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር አዉሮጳና ሰሜን አሜሪካ ከሚሞተዉ በአራት እጥፍ ይበልጣል።

ባለፉት 10 ዓመታት በመላዉ ዓለም ከደረሰዉ ድርቅ አፍሪቃ ዉስጥ የደረሰዉ ከግማሽ ያነሰ ነዉ።ይሁንና በድርቅና ድርቅ ባስከተለዉ ረሐብ ከሞተዉ ሰዉ 99ኝ በመቶዉ አፍሪቃዊ ነዉ።ለምን? አፍሪቃ በቂና አስተማማኝ የቅድመ መስጠንቀቂያ ሥርዓትና የዓየር ትንበያ ሥለሌላት ይላሉ ቪክቶር ኦንጎማ።የሞሮኮዉ  የመሐመድ 6ኛ ፖሌቴክኒክ ዩኒቨርስቲ የአየር ንብረት ጉዳይ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸዉ።

«የዓየር ንብረት ተንባዮች አስተማማኝ፣ ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ የዓየር ፀባይ ትንበያ እንዲያቀርቡ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸዋል።ሥለዚሕ ጥራትና ጊዜዉን  የጠበቀ የዓየር ፀበያ ትንበያ አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነዉ።አሁን ገና እዚያ ደረጃ አልደረስንም፣ ገና ከአማካዩ በጣም ያነሰ ነዉ።»

የአስቅሞ ትንበያና ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ ደካማ ሥለሆነ ጉዳቱ ከፍተኛ ነዉ
ባለፈዉ ሚያዚያ ኬንያን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋልምስል IMAGO/Xinhua

ለወትሮዉ ሩቅ ወይም በብዙ ዓመታት ይደርስ የነበረዉ የተፈጥሮ መቅሰፍት በዓየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት እየተደጋጋመ፣ ብዙ አካባቢዎችንም እያዳረሰ ነዉ።አደጋዉን አስቀድሞ አዉቆ በመከላከሉ ረገድ ግን አፍሪቃ አሁንም ከብዙዉ ዓለም ብዙ የራቀች ናት።የዓየር ፀባይ ቅድመ ትንበያ፣ አዋቂዎች እንደሚሉት ዉስብስብ፣ የብዙ ጊዜ መረጃ ክምችትን የሚሻ፣ ረቂቅ መሳሪያ ሳይንሳዊ ትንታኔን ይጠይቃል።

መረጃ አሰባሰብ፣ መሳሪያዎችና የአፍሪቃ ፈተና

 

መረጃዎቹ ከመሬት፣ ከሐይቆች፣ከዉቅያኖስ፣ ከከባቢ ዓየር ወዘተ በዘመናዊ ሳተላይት መሰብሰብና በኮምፒዉተር መቀመር አለባቸዉ።አፍሪቃ ግን በአብዛኛዉ ያላት በመሬት የተመሠረተ እሱም ቢሆን፣ የዓለም የሜትሪዮሎጂ አገልግሎት እንደሚለዉ ኃላቀርና አነስኛ ነዉ።አንጎላ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1975 ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ሥትወጣ 150 የሚትሪዮሎጂ ጣቢያዎች ከቅኝ ገዢዎቿ ተረክባ ነበር።ከ47 ዓመት በኋላ በ2022 የተረፋት 20 ጣቢያ ነዉ።

አዉሮጳ የዓየር ፀባይን የሚከታተሉ 345 የሬዳር ጣቢያዎች አሏት።ከአዉሮጳ በቆዳ ስፋት ብዙ የምትበልጠዉ አፍሪቃ ግን 37።በዚያ ላይ ብዙዎቹ የዓየር ፀባይ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪዎች የአፍሪቃን የዓየር ሁኔታ ለማጥናት ብዙ አይጠቅሙም።

የሊድ-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ ተጋባዥ ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ላምፕቴይ እንደሚሉት አብዛኞቹ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎቹ ለሰሜኑ ንፍቀ-ክበብ ታስበዉ የተሰሩ በመሆናቸዉ በነዚሕ መሳሪያዎች የአፍሪቃን የዓየር ፀባይ በትክክል ማጥናት አይቻልም።

«ዋናዉ ችግር የእነዚሕ አይነት መሳሪያዎች የአፍሪቃ የዓየር ፀባይ ያካተተ ሥርዓት የላቸዉም።የተሰሩት መካከለኛ ከፍታ ላላቸዉ ለሰሜኑ ንፍቀ-ክበብ ታስበዉ ነዉ።የትሮፒካል (ሞቃት)፣ የትሮፒካል ብቻ ሳይሆን የመላዉ አፍሪቃ የዓየር ሁኔታ በነዚሕ መሳሪያዎች ዉስጥ አልተካተተም።»

የአፍሪቃ የአየር ሁኔታን ለማጥናት የሚረዱ መሳሪያዎች ቢኖሩ እንኳ በአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት በሚ,ጊዜዉ የሚከሰተዉ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የኢንተርኔት መዘጋት፣ መቋረጥ ወይም ጨርሶ አለመኖር ተገቢዉ መረጃ በተገቢዉ ጊዜ እንዳይሰበሰብ ማደናቀፉ አይቅርም።የምሥራቅ አፍሪቃ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከምዕራቡ፣ የሰሜኑ ከደበቡ የተለያየ መሆኑና የዓየር ንብረቱም ልዩነት ሥላለዉ ለሁሉም የአፍሪቃ አካባቢዎች አንድ አይነት መሳሪያና ሥርዓት መዘርጋትም አስቸጋሪ ነዉ።

የመሳሪያዎቹ ማነስ፣ የአፍሪቃ የዓየር ሁኔታ አለመጣጣም፣ ከኃይልና የኢንተርኔት ችግር ጋር ተዳምረዉ አንዳዴ የሚትሪዮሎጂ ድርጅቶች ወይም ባለሙያዎች የሚሰጡት የዓየር ትንበያ በተጨባጭ ከሚሆነዉ ጋር ይቃረናል።ይሕ ተቃርኖ በፋንታዉ ሕዝቡ በአየር ፀባይ ተንበያና ተንባዮች ላይ እምነት እንዲያጣ አድርጎታል።

የጋናዉ የክዋሚ ንክሩማ ዩኒቨርስቲ የዓየር ንብረት ባለሙያ ጄፍሬይ N.A አዬ ግን በተለይ ጋናን በመሳሰሉ ሐገራት ጥሩ ለዉጥ አለ ባይ ናቸዉ።

«ያኔ አስታዉሳለሁ ብዙ ሰዎች፣ የዓየር ፀባይ ትንበያዎች እዉነተኛ ዓይደሉም ይሉ ነበር።ባለሙያዎች የሚሰጡት ትንበያ ከእዉነታዉ በጣም የተራራቀ ነዉ የሚል ወቀሳ ነበር።ብዙ የተዓማኒነት ጥያቄ ነበር።አሁን ግን የሰዉ አስተሳሰብ እየተሻሻለ፣ ትንበያዉም ወደ እዉነቱ እየቀረበ ነዉ።ከፍተኛ መሻሻል አለ።»

ሐቻምና ደቡባዊና ምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ግዛቶችን የመታዉ ድርቅ በርካታ ከብቶች ፈጅቷል።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተርበዋል።
አፍሪቃ የአስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሥርአቷ ደካማ በመሆኑ በየጊዜዉ ለተፈጥሮ አደጋ ትጠቃለች።ድርቅ-ኢትዮጵያምስል Thomas Mukoya/REUTERS

ይሁንና አዬ እንደሚሉት መሻሻሉ በቂ አይደለም።ተጨማሪ ዘመናይ መሳሪያዎችና ሥርዓቶች ያስፈልጋሉ።በዚያ ላይ «አንድ አሳ አጥማጅ ዝናብ ይዘንባል ወይም አይዘንብም ብትለዉ ብዙ የሚያስጨንቀዉ ጉዳይ ላይሆን ይችላል።» ቀጠሉ ፕሮፌሰር አዬ «ባሕሩ ማዕበል ይገጥመዉ ይሆን ወይ-ለሚለዉ ጥያቄዉ መልስ ይሻልና።»

 

ቻድ ከወታደራዊ መሪነት ወደ ተመራጭ ፕሬዝደንትነት

 

ባለፈዉ ሚያዚያ ማብቂያ ቻድ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ማሸነፋቸዉ የተነገረዉ የሐገሪቱ ወታደራዊ መሪ ጄኔራል መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ ባለፈዉ ሐሙስ ቃለ መሐለ ፈፅመዉ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ይዘዋል።

መሐመድ ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ የቻድ የረጅም ጊዜ ገዢ የነበሩት ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ ልጅ ናቸዉ።አባታቸዉ በ2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከአማፂያን ጋር ሲዋጉ ከተገደሉ ወዲሕ የ40 ዓመቱ ጄኔራል ቻድን ለ3 ዓመት ገዝተዋል።በጦር ኃይሉ ትብብር በዉርስ የያዙትን ሥልጣን በምርጫ አፀድቀዉ፣ ወታደራዊ ማዕረጋቸዉን አዉልቀዉ ያቺን በረሐማ፣ ደሐ ሐገር ከእንግዲሕ ለ5 ዓመት ይመራሉ።

«መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ፣ የሪፐብልኪቱ ፕሬዝደንት፣ በሐገሪቱ ሕግ መሰረት የተመረጥኩ፣ ከቻድ ሕዝብ ፊት ቆሞ የቻድን ክብር ለመጠበቅ፣ ሕገ መንግስቷን ለማስከበር፣ ገቢራዊነቱን ለማረጋገጥ፣ እንዳይጣስ ለመከላከል ቃል አገባለሁ።»

በሐሙሱ በዓለ ሲመት ድግስ ላይ  ስምት የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎችን ጨምሮ የበርካታ ሐገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሳሕል በረሐ፣ሰፊ፣ ወደብ አልባይቱ ሐገር እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1960 ነፃ ከወጣች ወዲሕ መፈንቅለ መንግስት፣ አመፅ፣ የርስበርስ ጦርነትና የፖለቲካ ዉዝግብ ተለይቷት አያዉቅም።የቀድሞዉ የጦር መኮንን ኢድሪስ ዴቢ እንደ አማፂ መሪ ሥልጣን ከያዙ ከ1990 በኋላ ቻድ ከረጅም ጊዜ የርስ በርስ ጦርነት ብትላቀቅም ፖለቲካዊ እመቃ፣ጭቆናና አፈናዉ ግን አላባራም።

የኬንያ ርዕሰ ከተማ የናይሮቢ መንደሮችና መንገዶች ወደ ኩሬነት ተቀይረዉ ነበር
አስቀድሞ ዝግጅት ሳይደረግ ድንገት የደረሰዉ ጎርፍ የኬንያ አንዳድ መንደሮችን ጠራርጎ ወስዷል።ምስል Luis Tato/AFP/Getty Images

ዴቢይ ከሰላሳ ዓመት በላይ የያዙትን ሥልጣን ለተጨማሪ 5 ዓመታት በምርጫ ባራዛሙ በዕለታት ዉስጥ ከአማፂያን ጋር ሲዋጉ ተገደሉ።ሐሙስ ቃለ መሐላ የፈፀሙት የዴቢይ ልጅ መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ የአባታቸዉን አልጋ ወርሰዉ እንደ ወታደራዊ ሁንታ በሥልጣን ላይ የቆዩበት ሶስት ዓመታትም ለቻድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ለመብት ተሟጋቾችና ለጋዜጠኞች አንዳዶች እንደሚሉት ከዴቢይ ዘመን የከፋ ነበር።

 

«የሁሉም ፕሬዝደንት ነኝ» መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ

 

ባለፈዉ ሚያዚያ ማብቂያ በተደረገዉ ምርጫ የተወዳደሩ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸዉ ወከባ፣ እንግልትና ማሳደደር ደርሶባቸዋል።መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖን በግንባር ቀደምትነት የተፎካከሩት የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትራቸዉ ሰክሴስ ማርሳ ከተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራ ማምለጣቸዉን አስታዉቀዋል።

በ2022 ከስደት ወደ ቻድ ተመልሰዉ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት ማርሳ የምርጫዉን ሒደትና ዉጤት የተጭበረበረ በማለት ዉድቅ አድርገዉታል።የምጣኔ ሐብት ባለሙያዉ ማርሳ ከተሰጠዉ ድምፅ 18.5 ከመቶዉን ማግኘታቸዉን የቻድ አስመራጭ ኮሚሽን አስታዉቋል።መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ ካጠቃላዩ ድምፅ 61 ከመቶ ማግኘታቸዉ ነዉ የተነገረዉ።ቃላ መሐላ በፈፀሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ግን የአዲስ መሪ ወግ ነዉና ለሁሉም የቻድ ሕዝብ ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

አዲሱ የቻድ ፕሬዝደንት መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ በዓለ ሲመታቸዉን ሲያከብሩ
አዲሱ የቻድ ፕሬዝደንት መሐመድ ኢድሪስ ዴቢይ ኢትኖ በዓለ ሲመታቸዉን ሲያከብሩምስል Israel Matene/REUTERS

«ባንድ ወይም በሌላ ምክንያት እኔን ላልመረጣችሁ ወድምና እሕቶቼ የመምረጥ ነፃነታችሁን አከብራለሁ።የመምረጥ መብታችሁ የመሰረታዊ ዴሞክራሲያችን የማይነጠል አካል ነዉና።ከዚሕ በኋላ ግን እኔ የቻድ ፕሬዝደንት ነኝ።ከዚሕ በኋላ የሁሉም የአብዛሐና የአሐዳዊ ቻዳዉያን ፕሬዝደንት ነኝ።»

የሚያዚያዉ ምርጫ ብዙ መዛባቶች እንደነበሩበት የተለያዩ ወገኖች ዘግበዋል። ወደ 3ሺሕ የሚጠጉ የአዉሮጳ ሕብረት ታዛቢዎችም  የምርጫዉን ሒደት እንዳይከታተሉ ታግደዋል።ይሁንና የቀድሞዋ የቻድ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይን ጨምሮ ብዙዎቹ የምዕራብ አዉሮጳ መንግስታት ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ ለአዲሱ ፕሬዝደንት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ