1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትልን ለተፈጥሮ ማዳበሪያ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 16 2014

በሲዳማ ክልል ወንዶገነት ወረዳ የሚገኙ አርሶደሮች Varmy worm ወይንም የቫርሚ ትል የተባለውን የትል ዝርያ በመጠቀም ለእርሻው የሚያስፈልጋቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ እያመረቱ ነው።

https://p.dw.com/p/4Bn0c
Äthiopien Bio Landwirtschaft Natürlicher Dünger
ምስል Shewangizaw Wogayehu/DW

ትልን ለተፈጥሮ ማዳበሪያ

 

ወ/ሮ ኦሚቱ ቡሹራ በሲዳማ ክልል ወንዶገነት ወረዳ የአሩማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ናቸው። ወ/ሮ ኦሚቱ ከሰባት ዓመት በፊት ቫርሚ የሚባለውን የትል ዝርያ ወደ ቀበሌው ይዘው ሲመጡ የመንደሩ ሰው ሁኔታውን ከባዕድ አምልኮ ጋር በማያያዝ በአሉታ እንደተመለከታቸው ያስታውሳሉ። አሁን ግን ወ/ሮ ኦሚቱን ጨምሮ የቀበሌው አርሶአደሮች የቫርሚ ትልን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት ላይ ናቸው። የቡና ገለባ፣ ፍራፍሬ እና ቅጠላ ቅጠልን ጨምሮ የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን በማበስበስ ወደ ማዳበሪያነት ይቀይራል ስለተባለው የቫርሚ ትል የተጠየቁት በሀዋሣ ግብርና ምርምር ማዕከል የተፈጥሮ ሀብት የሥራ ሂደት አስተባባሪ ገነት ጌታቸው፤

« በዓለም ላይ ከ3000 በላይ የመሬት ትል ዝርያዎች ይገኛሉ። ከነኚህም መካከል ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት የሚውለው  ኢዚኒያ ፌቲዳ የተባለው  ነው። ይህ በተለምዶ ቀይ ትል ወይም ጥምልምል ትል በመባል የሚታወቀው ዝርያ ቅጠላቅጠሎችና ከቤት ውስጥ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን በማበስበስ የተፈጥሮ ማዳበሪያን  ይፈጥራል። ከትሉ የተገኘው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለሁሉም አይነት የእርሻ ምርቶች በማዳበሪያነት የሚያገለግል ነው » ይላሉ።

Äthiopien Bio Landwirtschaft Natürlicher Dünger
ለማዳበሪያ ማዘጋጃነት የሚውለው ቫርኒ ትልምስል Shewangizaw Wogayehu/DW

አርሶ አደሮች በአነስተኛ ቦታ ላይ የቫርሚ ትልን በመጠቀም የሚያስፈልጋቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት እንደሚችሉ የሚናገሩት የማዕከሉ የሥራ ሂደት አስተባባሪዋ ገነት ጌታቸው የአመራረት ሂደቱም ቀላል ነው ባይ ናቸው። የዛሬ ሰባት ዓመት የቫርሚ ትል ዝርያን ከኦሮሚያ ክልል አምቦ አካባቢ በማስመጣት በሲዳማ ክልል ወንዶገነት ወረዳ አሩማ ቀበሌ የተጀመረው «የቫርሚ ኮምፖስት» ሥራ አሁን ላይ ውጤት እያስገኘ እንደሚገኝ የማዕከሉ የሥራ ሂደት አስተባባሪዋ ይናገራሉ። የአሩማ ቀበሌ ነዋሪዎቹ አርሶ አደር ኦሚቱ ቡሹራ እና አሰፋ አምቦ ቫርሚ ትሉን መጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ  የምርት ጭማሪ ከማግኘታችውም በላይ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መግዛት ማቆማቸውን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

Äthiopien Bio Landwirtschaft Natürlicher Dünger
ምስል Shewangizaw Wogayehu/DW

የቫርሚ ኮምፖስት ሥራን ሲጀምሩ ለእርሻ ማሳቸው የሚያስፈልጋቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረት እንደነበር የሚናገሩት ኦሚቱ እና አሰፋ አሁን ላይ ግን ከማሳ የተረፋቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያውን በመሸጥ  ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆናቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

Äthiopien Bio Landwirtschaft Natürlicher Dünger
በተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀምምስል Shewangizaw Wogayehu/DW

የቫርሚ ትል ከሚያስገኘው የማዳበሪያ ምርት በተጨማሪ ንፁህ አካባቢ መፍጠርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተጓዳኝ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚናገሩት የሀዋሣ የግብርና ምርምር ማዕከል የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ሂደት አስተባባሪዋ ገነት ጌታቸው በተለይም አሁን ያለውን የእርሻ ማዳበሪያ ፍላጎት ለሟሟላት የቫርሚ ኮምፖስት ሥራን ማስፋፋት እንደሚገባ ይመልክራሉ።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ