1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ታይም» መጽሔት ጠ/ሚ ዐቢይን ተፅእኖ ፈጣሪ ያለበት መንገድና ውዝግቡ

ረቡዕ፣ ግንቦት 17 2014

«ታይም» መጽሔት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ተፅእኖ ፈጣሪ ያለበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ተቸ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም ቀዳሚ 100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ የገቡበት አግባብም ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ የተቃርኖ አስተሳሰቦች አሰልፏል፡፡

https://p.dw.com/p/4Brmo
Äthiopien Abiy Ahmed
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተጽኖ ፈጣሪነትና የተከተለው ውዝግብ

«ታይም» መጽሔት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ተፅእኖ ፈጣሪ ያለበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ተቸ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም ቀዳሚ 100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ የገቡበት አግባብም ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ የተቃርኖ አስተሳሰቦች አሰልፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በጦርነት የሚተቹ እንዳሉ በሰላም ወዳድነታቸው እና ጦርነቱን ተገዶ እንደገቡበት የሚያነሱም አሉ፡፡ 

ታይም የተሰኘው የዩናይትድ ስቴትስ መጽሔት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በዓለማችን ተፅዕኖ ያሳደሩ 100 ሰዎች ስም ዝርዝር ዉስጥ ማካተቱ ኢትዮጵያውያንን በተቃርኖ አሰልፏል፡፡ ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከቀዳሚ የዓለማችን 100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መባልን ከተቃወሙ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ በጂማ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጤኝነትና ኮሚዩኒኬሽን የሚያስተምሩ ዶ/ር ደመላሽ መንግስቱ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር አዎንታዊነቱ የሚበዛ በመሆኑ ተጽእኖ ፈጠሩ መባል ያለበት የአገር አንድነትን በማስጠበቅ እና በሰላም ወዳድነታቸው ነው ይላሉ፡፡

ታይም መጽሔት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መካከል መሆናቸውን ሲገልጽ ከዚህ ቀድም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረውን ጠብ በሰላም በመፍታታቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት መውሰዳቸውን አስታውሷል፡፡ አክሎም በትግራይ ተቀስቅሶ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ላስከተለው ጦርነትም ተጠያቂ ናቸው ብሏል፡፡ በመጽሔቱ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘገበችው ጋዜጠኛ አሪያን ቤከር “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይሎች ላይ የዘር ተኮር ግድያ እና የጾታ ጥቃት ክስ መቅረቡን” አንስታለች፡፡ ከወራት በፊት “ለሰብዓዊ ድጋፍ መቀላጠፍ ሲባል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው መንግስት ጦርነት ማቆሙንም” አስታውሳበታለች፡፡  ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ  በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።ዶ/ር ደመላሽ መንግስቱ በፊናቸው በአስተያየታቸው በተቃራኒው ሞግተዋል፡፡ የታይምስ መጽሔት ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ ቢለኔ ሥዩም ለታይምስ በጻፉት ደብዳቤ መጽሔቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያቀረበበት መንገድ ላይ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ለፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊዋ የእጅ ስልክ ላይ ደውለን ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ቢልለኔ ለታይምስ መጽሔት በጻፉት ደብዳቤ ግን መጽሔቱ እውነታን ትቶ በአንድ ወገን የሚቀርበው ትርክት ላይ አተኩሯል ነው ያሉት፡፡ መጽሔቱ እውነትን አዛብቶ ለዓለም ለማቅረብ ለምን እንደፈለገ ማብራሪያም እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

Äthiopien | PK Billene Seyoum | Sprecherin des Premierministers
ምስል Yohannes Geberegziabher/DW

በዘንድሮው የታይምስ መጽሔት 100 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኮምፒዩተር ባለሙያ ትምኒት ገብሩ፣ የአሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ቻይና እና ታንዛኒያ ፕሬዝዳንቶችንም አካቷል፡፡

ሥዩም ጌቱ 
ሂሩት መለሰ
ሽዋዬ ለገሰ