1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታዋቂው እና አንጋፋው የጥበብ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ አረፉ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 7 2013

ላለፉት ዐሥር ቀናት ያህል በሕክምና ሲረዱ የቆዩት አንጋፋው የጥበብ ሰው ተስፋዬ ገሰሰ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በ84 ዓመታቸው ዛሬ ሌሊት ዐረፉ። የቀብር ሥነሥርዓታቸው የሚከናወነው ሐሙስ ታኅሣስ 8 ቀን፣ 2013 ዓም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሆነ ተገገልጧል።

https://p.dw.com/p/3mnnR
Äthiopien Addis Abeba Tesfaye Gessesse celebrates his 80th birthday
ምስል privat

ኢትዮጵያ ታላቅ የጥበብ ሰው አጣች

ላለፉት ዐሥር ቀናት ያህል በሕክምና ሲረዱ የቆዩት አንጋፋው የጥበብ ሰው ተስፋዬ ገሰሰ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በ84 ዓመታቸው ዛሬ ሌሊት ማረፋቸው ተገለጠ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ፦ የቀብር ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጠው የቀብር ሥነሥርዓት የሚከናወነውም ሐሙስ ታኅሣስ 8 ቀን፣ 2013 ዓም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሆነ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ነገ ማለዳ የጋሽ ተስፋዬ ገሠሰ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የቀድሞ ተማሪዎች፤ አፍቃሪዎች፣ አክባሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት የሽኝት ሥነ ሥርዓት እንደሚካኼድ ተናግረዋል። 

ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ የተወለዱት ሐረርጌ ጎረጎቱ በተባለ ሥፍራ ነው። ለወላጆቻቸው ብቸኛ ልጅ የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ እስከ ስምንት ዓመታቸው እዛው ሐረርጌ ውስጥ ኖረዋል። እዛም በቤተ ክኅነት ትምህርት እስከ መዝሙረ ዳዊት ድረስ ተምረዋል። ስምንት ዓመት ሲሞላቸውም ወደ አዲስ አበባ በመኼድ ተፈሪ መኮንን አዳሪ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። አዳሪ ትምህርት ቤት የገቡትም በጣሊያን ጊዜ ወላጅ እናት እና አባታቸው በመሞታቸው ነበር። 

በ1951 ዓም «ኢዮብ» የተባለውን ቴአትር ሲሠሩ የተመለከቷቸው ዐፄ ኃይለሥላሴ ጠርተዋቸው፦ «አንተ ቴአትር ነው ብትማር የሚሻለው የምን ሕግ ነው? ተፈልጎለት ይማር አሉ።» ብለዋቸው ዕድሉን እንዳገኙ በአንድ ወቅት ተናግረዋል።  «ቴአትር ኼጄ እንዳጠና ግርማዊነታቸው ናቸው ያደረጉት። ያ ነው አደራው የነበረብኝደግሞም የኢትዮጵያን ቴአትር ለማስፋፋት ዕድሉን የሰጡኝ እሳቸው ናቸው» ሲሉ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል። እና የዛሬ ስድሳ ዓመት ግድም በንጉሡ ወደ አሜሪካ ተልከውም በኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምሕርትን ተከታትለው በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቴአትር ታሪክ የመጀመሪያው ምሩቅም ናቸው። 

Äthiopien Addis Abeba Tesfaye Gessesse celebrates his 80th birthday
ምስል privat

ከአሜሪካ ከተመለሱም በኋላ የኢትዮጵያ ቴአትርን ለማዘመን ብዙ ሠርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ክፍል የረዥም ዘመን መምህር ኾነው አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅ በመሆን ቴአትሩን የማዘመን በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። በሐገር ፍቅር ቴአትርም። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ መሰናዶዎችን የጀመሩ የጥበብ ሰው ናቸው። 

ሌላው እጅግ የሚታወስላቸው፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘውን ቤተ ኪነ ጥበባት ወ ቴአትር የሚባለውን ማዕከል ከዶክተር ፊሊፕ ካፕላን ከሚባሉ የኤአትር ሰው እና ከግብጻዊ አሜሪካዊው የሙዚቃ ምሁር ሐሊብ ኤልድሃብ ጋር በመሆን መመሥረታቸው ነው። እሳቸው በወቅቱ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ ወካይ በመሆን የማዕከሉ ዳይሬክተር ኾነው ነበር።  ማዕከሉ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሕል ማዕከል ተብሎ ታላላቅ የሀገሪቱ ደራሲያን እና ከያኒያንን ማፍራት ችሏል። 

ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ፥ በድርሰት ሥራቸው፣ በትወናቸው ይታወሳሉ። በተለይ እንደ እነ ሐምሌት የተሰኙትን የሼክስፒር ታላላቅ ሥራዎች ላይ መሪ ተዋናይ በመሆን ተሳትፈዋል። እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ባሉት ዓመታት መጽሐፍትን እየጻፉም አሳትመዋል። 

ከድርሰት ሥራዎቻቸው መካከል፦ በአሜሪካን አገር እያሉ በ1953 ዓ.ም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ላቀችና ማሰሮዋ በሚል የጻፉት ይጠቀሳል።  በተጨማሪም በ1965 ዓ.ም. መተከዣ የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል። በ1954 የሺ፣ በ1958 አባትና ልጆች፣ በ1961 ዕቃዉ የተሰኙ ድራማዎችን ደርሰዋል። በ1966 ማነዉ ኢትዮጵያዊ፣ በ1970 ፍርዱን ለዕናንተዉ፣ በ1972 ተሀድሶ፣ በ1979 ሰኔና ሰኞ የተሰኙ ድራማዎችንም ለመድረክ አብቅተዋል። 

ጋሽ ተስፋዬ የኡመር ኻየምን መጽሐፍ «ሩብ አያት» በማለት ተርጉመው አሳትመዋል። የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ካሳተመው ጽሑፍ ውስጥ ሥራዎቻቸው እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።
፩. መተከዣ (ግጥምና ቅኔ)
፪. ጥላሁን ግዛው(ተውኔት)
፫. ዕቃው(ተውኔት)
፬. የሺ (ተውኔት)
፭. አባትና ልጆች (ተውኔት)
፮. ላቀችና ደስታ (ተውኔት)
፯. ተሐድሶ (ተውኔት)
፰. መተከዣ (ልብወለድ)
፱. ዑመር ኻያም ልቦለዳዊ የሕይወት ታሪኩና ሩብአያቶቹ ( ትርጉም)
፲ የመጨረሽታ መጀመርታ(ታሪክና ሕይወት ቀመስ ሽሙጥ ልቦለድ)
ታላቊ የጥበብ ሰው ነፍስ ይማር!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ