1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

ታዋቂ የመሆን ህልም ያላቸው የናይሮቢ ወጣቶች

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 2 2013

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅታችን በናይሮቢ የደሀ ሰፈር የሚኖሩ እና ድምፃዊ መሆን የሚፈልጉ ወጣቶች እና በኢንስታግራም በመጠኑም ቢሆን ህልማቸውን ያሳኩ አዳዊ ወጣቶች ናቸው። « the H Town Kids » ይባላሉ።

https://p.dw.com/p/3mXaB
Kenia Boris Bachorz Mitgleider der somalischen Rap Gruppe Waayaha Cusub (New Era in Somali)
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

ታዋቂ የመሆን ህልም ያላቸው የናይሮቢ ወጣቶች

እንደ ዩ ቲውብ ፣ ኢንስታግራም እና ቲክ ቶክ ባሉ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች በርካታ ወጣቶች ታዋቂ ወይም ሀብታም ለመሆን ሲጥሩ እና ሲሰሩ ይስተዋላል። ለዚህም ወጣቶቹ አቅማቸው እንደፈቀደው ከያሉበት ቦታ ሆነው በብዛት ቪዲዮ እየሰሩ ያሰራጫሉ። 
በኬንያ ናይሮቢ አንድ የድሆች ሰፈር የሚገኝ የሙዚቃ ስቱዲዮ ውስጥ ነው። ስቱዲዮው ይህን ያህል የተጋነነ የሚባል አይደለም። ግድግዳዎቹ  ድምጽ እንዳያስገቡ በስፖንጅ ተሸፍነዋል። መሣሪያዎቹም ጥቂት ናቸው። አንድ ኮምፒውተር፣ አንድ ድምጽ ማጉያ፤  አንድ የሙዚቃ ማቀናበሪያ እና አንድ ማይክራፎን ናቸው። የ 18 ዓመቱ ሊኪ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ሆኖ ዛሬ የመጀመሪያውን ሙዚቃ ለመቅረጽ እየተዘጋጀ ነው። «ሙዚቃ ህይወቴን ይለውጠዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሰዎችን ማስደሰት እፈልጋለሁ። ምናልባት የሙዚቃው መልዕክት እንዲያስቡበት ያደርጋቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ ዝም ብሎ ብቻ ዘና ያደርጋቸው ይሆናል»
የሊኪ ምኞት የበርካታ በኬንያ የድሆች ሰፈር የሚኖሩ ወጣቶችም ምኞት ነው። አንዱ ሙዚቃቸው ወዲያው ከህዝብ ጋር እንዲያስተዋውቃቸው ወይም ደግሞ ትንሽ ገንዘብ ማግኛ እንዲሆናቸው ይመኛሉ። ለዛም ነው ለስቱዲዮ የሚከፍሉትን ገንዘብ የሚያጠራቅሙት። ለስቱዲዮ ለቀረፃው ሲመነዘር 2500 ብር ገደማ መክፈል ይኖርባቸዋል።  ሊኪ የሚዘፍነው ለት ከለት ስለሚገጥመው ነገር ነው። «በዚህ የደሀ ሰፈር ውስጥ ስለሚገጥሙን ችግሮች፤ በጠቅላላ ስለ ህይወት፣ ስለ ድህነት፤ ስለ ጨካኝ የፖሊስ ርምጃዎች እንዲሁም አደንዛዥ እፅ ስለሚወስዱ ወጣቶች እጽፋለሁ።»

ዘፈኖቹ በአካባቢው የተለመዱ ናቸው። በተለይ ኬንያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የራፕ፣ የሬጌ እና ዳንስ ሆል የሙዚቃ ስልቶች ቅንብር ዝነኛ እየሆኑ መጥቷል። ግጥሙ የተፃፈው ደግሞ የኬንያ ወጣቶች በሚግባቡበት   በብዛት የእንግሊዘኛ እና ሱዋሂሊኛ በሚቀላቅለው «የሼንግ» ቋንቋ ነው። ኬንያ ውስጥ በየዓመቱ በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶች በእንደዚህ ቀላል በሚባል ስቱዲዮ በተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ታዋቂ ለመሆን እድላቸውን ይሞክራሉ። አልፎ አልፎም አንዳንዶች ልክ እንደ ቢግፍሬድ ቼቼ ተሳክቶላቸዋል። ቢግፍሬድ ቼቼ ገበያውን ከተቀላቀለ ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ።  እሱም ዛሬ ሊኪ ተስፋ በጣለበት በዚሁ ስቱዲዮ ውስጥ ነው የመጀመሪያውን ሙዚቃ የቀረፀው። « ሙዚቃ ሁሌም ደስ የሚለኝ ነገር ነበር። ምናልባትም ይህንን መውደድ የጀመርኩት ከመወለዴ በፊት የእናቴ ሆድ ውስጥ ሳለሁ ነው። የመጀመሪያ ሙዚቃዬ ራፕ ነበር። ይህ እስቱዲዮ ብዙ ፈጠራዎች አሉት ወጣቶችንም ያግዛል።»  ቢግፍሬድ በብዛት የሚታወቀው ናይሮቢ ውስጥ ነው። እንደዛም ሆኖ አንዳንድ ትላልቅ የሙዚቃ ስቱዲዮዎች አብረውት ለመስራት ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። ይሁንና ዝና ላጎናፀፈው ትንሽ ስቱዲዮ ታማኝ ሆኖ መቆየትን ይመርጣል።« ቤትሽ ሁል ጊዜ ቤትሽ ነው። ወደየትም ሄድሽ ወዴት ተመልሰሽ ትመጪበታለች። አዲስ  ሀሳብም የማገኘው እዚህ ነው»

ሌሎች አዳጊ ኬንያውያንም ቢሆኑ ተመሳሳይ ህልም አላቸው። ከሚኖሩበት የደሀ ሰፈር ወጥተው ዝነኛ መሆንን ይፈልጋሉ። ይህም በከፊል የተሳካላቸው ይመስላል። « the H Town Kids » ኬንያ ውስጥ ኢንስታግራም ላይ ዝና ተጎናፅፈዋል።  የሙዚቀኛ እና የታዋቂ ሰዎችን ንግግር በአፍ እንቅስቃሴ በማስመሰል በሰፈራቸው የሚችላቸው ጠፍቷል። ህልማቸውም የዛኑ ያህል ትልቅ ነው።« ሳድግ ኮሜዲያን መሆን እፈልጋለሁ፤ እኔ ከአለም ታዋቂ ደናሽ መሆን ነው የምፈልገው፤ እኔ ካሜራ ማን መሆን ነው የምፈልገው። ይላሉ በናይሮቢ የድሆች ሰፈር በሆነችው ሁሩማ የሚኖሩት « the H Town Kids » ኢንስታግራም ላይ ታዋቂዎቹ ልጆቹ ቢሆኑም ከበስተጀርባቸው ሮዝ ምዋሬ የተባለች ሴት አለች ። አይስክሬም ሻጯ ሮዝ ቪዲዮ እንዴት እንደሚቀረፅ እና እንደሚቀናበር ራሷን በራሷ ነው ያስተማረችው።  ከሰፈሯ ህፃናት ልጆች ጋር ቪዲዮ መስራት ከጀመረች አሁን አንድ ዓመት አለፋት « ትልቅ ስሆን እውን ማድረግ የምፈልጋቸው አንዳንድ ነገሮች ነበሩ። ነገር ግን አልተሳኩልኝም። ስለዚህ እነዚህ ልጆች በእኔ ቦታ ሆነው ይህንን እውን እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ።»  አስቂኝም ይሁን የሙዚቃ ቪዲዮዎች እነዚህን ልጆች ምንም የሚከብዳቸው ነበር የለም። ዛሬ ለምሳሌ ‘Black is King’ የሚለውን የዩናይትድ ስቴትሷን ዝነኛ የሙዚቃ አቀንቃኝ የቢዮንሴን ሙዚቃ ይቀርፃሉ። ቀረፃው ሙሉ ቀን ይፈጃል። እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው።« የቀረፃው ቦታ ምን እንደሚመስል አልፎ አልፎ ስልኬ ላይ አያለሁ። ማናጀራችንም ምን ማድረግ እንዳለብን ትነግራናለች። አሁን ለምሳሌ ብስክሌቱን እንዳመጣ ነግራኛለች። ይህንን ብስክሌት እንሸፍንና ልክ እንደ ፈረስ እንጠቀምበታለን። »ይላል ከልጆቹ በእድሜ ከፍ የሚለው ጆሴፍ። 

« እያንዳንዷ ዝርዝር ነገር ከዋናው ቪዲዮ ጋር እንዲመሳሰል እንጥራለን። ለዛ ነው አንድ አንዴ ልጆች ላይ እንደዚህ ጠንከር የምለው።» ለአዳጊ ልጆቹ ቪዲዮው አስመስሎ ከመስራት በላይ ነው። በሰፈራቸው ሌላ ወጣቶች ጊዜያቸውን ማሳለፍ የሚችሉበት ምንም አይነት ተቋም የለም። « ቡድናችን ያስደስተኛል ምክንያቱም ብቻዬን አይደለሁም። እንደኔ ያሉ ሌሎች ልጆች አሉ እና እንተጋገዛለን። አንዳችን ሲሳካልን ሌሎቻችንም ስራውን ቁምነገር አድርገን እንወስደዋለን»ይላል ጆሴፍ።  

Ghetto Classics Nairobi
የኬንያ የድሆች ሰፈርምስል Antje Passenheim/WDR
Kenia Boris Bachorz Mitgleider der somalischen Rap Gruppe Waayaha Cusub (New Era in Somali)
አንዳንድ ኬንያ የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞችም ናይሮቢ ውስጥ ሙዚቃ ይቀርፃሉምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

ሮዝ ልጆቹን መቅረፅ የጀመረችው ለራሷ ያልተሳካላትን ምኞት በልጆቹ ለማሳካት ብላ ብቻ አይደለም። ለልጆቹ ደህንነት ስትል እንደሆነም ትናገራለች። እሷ እንደምትለው ልጆቹ ጎዳና ላይ አልባሌ ነገር ከሚሰሩ እና አደጋ ከሚገጥማቸው ይህ ጥሩ አማራጭ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ልጆቹ ከትወና ሌላ እውቀት መገብየት ይችላሉ። እንደ Black Lives Matter እና የኮሮና ወረርሽኝን በመሳሰሉ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችንም ሮዝ ከልጆቹ ጋር ቪዲዮዎች ትቀርፃለች።« የወደፊት እጣ ፈንታቸው ብርሃን የፈነጠቀበት እንዲሆን እንፈልጋለን። እና አንድ ሰው ችሎታቸውን ለማሳደግ ከዚህ ከሁሩማ የደሀ ሰፈር ያላቅቃቸዋል። »ታዋቂ የመሆን ህልም ካላቸው የናይሮቢ ወጣቶች ጋር ያስተዋወቀን የዛሬው ዝግጅት በዚሁ ይጠናቀቃል። በሚቀጥለው ሳምንት አዲስ ዝግጅት ይዘን እንጠብቃችኋለን።

አንትየ ዲክሀንስ/ ልደት አበበ 

አዜብ ታደሰ