1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮችን የመደገፍ ዘመቻ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 1 2014

በድሬደዋ ቀደም ብሎ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን የገለፁ ወጣቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀጣይ ሦስት ወራት በሚካሄደው ዘመቻ ይሄንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። በአጠቃላይ በዚህ ዘመቻ የማይሳተፍ አካል እንደማይኖርም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/446eh
Äthiopien Dire Dawa | Fundraising IDP
ምስል Mesay Teklu/DW

ወጣትነቴ ለሀገሬ

ከዛሬ አንስቶ አስከ መጪው የካቲት 30 ድረስ በሚኖሩ ቀጣይ ሦስት ወራት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለሀገር ደጀንነታችውን ያረጋግጡባቸዋል የተባሉ የተለያዩ የዘመቻ ተግባራት እንደሚከናወኑ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ። በዘመቻው ከሚከናወኑ ተግባራት ቀዳሚው በጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚረዳ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ መሆኑ ተገልጿል። ወጣቶች በበኩላቸው ይህንኑ ኃላፊነት በመወጣት ታሪካዊ ሥራ እንሠራለን ብለዋል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ከዛሬ አንስቶ ባሉት ሦስት ወራት «ወጣትነቴ ለሀገሬ» በሚል መሪ ሀሳብ የሀገሪቱ ወጣቶች የሀገር ደጀንነታቸውን የሚያረጋግጡባቸው በርካታ የዘመቻ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጠዋል። ወጣቶች በዘመቻው ይሳተፉባቸዋል ከተባሉ አራት ዋና ዋና መስኮች አንዱ አሸባሪው ቡድን ከወረራቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉና ሀብት ንብረታቸው በዚሁ የሽብር ቡድን የወደመባቸውን ዜጎች መልሶ ማቋቋም መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ኤርጎጌ በዚህም በርካታ ሥራ ይከናወናል ብለዋል። በሦስቱ ወራት ወጣቶች የዘማች ቤተሰቦችን እና የመከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ ፣ በማኅበራዊ መገናኛ ዘመቻው የሀገራቸውን ሀቅ ይዘው በመሟገት ፣ የአካባቢያቸውን ፀጥታ በመጠበቅ ለሀገር ህልውና መጠበቅ የበኩላቸውን የሚወጡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ሚንስትሯ ጠቁመዋል። የብልፅግና ወጣቶች ፕሬዝዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ በበኩሉ በቀጣይ ሶስት ወራት ዜጎቻችንን ወደ ቀደመ የሞቀ ጎጇቸው የምንመልስበትን ታሪካዊ ሥራ እንደሚሠሩ ገልጿል።

በድሬደዋ ቀደም ብሎ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን የገለፁ ወጣቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀጣይ ሦስት ወራት በሚካሄደው ዘመቻ ይሄንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። በአጠቃላይ በዚህ ዘመቻ የማይሳተፍ አካል እንደማይኖርም ተገልጿል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በወጣቶች ይከናወናል በተባለው የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ ከሦስት መቶ ሚልየን ብር በላይ የሆነ የዓይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ይሰባሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

መሳይ ተክሉ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ