1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮች ወደ ቤንሻንጉል መመለስ መጀመራቸው

ሐሙስ፣ ሰኔ 17 2013

ከአራት ወራት በፊት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል የነበሩ 50ሺህ ሰዎች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መመለስ መጀመራቸው ተገለጠ።

https://p.dw.com/p/3vVJE
Äthiopien Rückkehrer aus Benshangul Gumuz
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከ50ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ተፈናቅለው ነበር

ዳንጉር፣ ድባጤ፣ ማንዱራ፣ ቡለን የተሰኙት የመተከል ዞን ወረዳዎች  ከአራት ወራት በፊት በአሰቃቂ የጅምላ ግድያዎች በበርካቶች አእምሮ ውስጥ ቀርተዋል። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ እና ጅምላ ግድያ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል የነበሩ 50ሺህ ነዋሪዎች ወደ ተጠቀሱት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወረዳዎች መመለስ መጀመራቸው ተገልጧል። የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጋራ ግብረኃይል ነዋሪዎቹ የተመለሱት ሁለቱ ክልሎች በደረሱት ስምምነት መሰረት ነው ብሏል። ኾኖም አንዳንድ ተፈናቃዮች ለዶይቸ ቬለ (DW) እንደተናገሩት «በቦታው ሰላም የለም፤ እየኼድንም አንሞትም» ብለዋል፤ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው አመልክተዋል። የቤኒሻንጉል ክልል በበኩሉ የመመለስ ፍላጎት ያላሳዩት እውነተኛ ተፈናቃዮች አይደሉም ብሏል፡፡ 

ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ 2013 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከ50ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው «ራንች» በተባለ ቦታ ቆይተዋል፡፡ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መንግስታት በደረሱበት የጋራ ስምምነት መሰረት ተፈናቃዮቹ ካለፈው አርብ ጀምሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተመለሱ እንደሆነ የሁለቱ ክልሎች የጋራ ግብረኃይል ቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ በትግሉ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Rückkehrer aus Benshangul Gumuz
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት መሥሪያቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍንም ተፈናቃዮች እየተመለሱ ስለመሆናቸው በስልክ አረጋግጠውልናል፡፡ ተፈናቃዮቹ በአንድ ማዕከል እንደሚሰባሰቡ የተናገሩት አቶ በትግሉ በቀጣይ ወደ የነበሩበት አካባቢዎች አንደሚሄዱ አብራርተዋል። ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተመለሱት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ካለፍላጎታቸው እንደተመለሱና የምግብ ድጋፍ እንዳልተሰጣቸው ቅሬታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ነገ ወደ ቤኒሻንጉል ክልል ለመመለስ እቅድ የተያዘለት ሌላው ተፈናቃይም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ የምግብ ድጋፍ የለም ስለሚባለው ቅሬታ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአንድ ወር ቀለብ ከነበሩበት እንዲሚያመጡና ከዚያ በኋላ መሥሪያ ቤታቸው እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡ አንዳንድ ተፈናቃዮች ወደ ነባር ቦታችን አልተመለስንም ለሚሉት ቅሬታም አቶ ታረቀኝ እንዳሉት ተፈናቃዮቹ ወደ አንድ ማዕከል እንደሚሰባሰቡ ጠቁመው በቀጣይ ወደ ነባር ቦታቸው ይሄዳሉ ብለዋል፡፡ እውነተኛ ተፈናቃዮች ወደ ክልላቸው መመለሳቸው አስደስቷቸዋል ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ የመመለስ ፍላጎት የሌላቸው ግን ከመጀመሪያውም ተፈናቃዮች አይደሉም ነው ያሉት፡፡ ከተፈናቃዮች ጋር ስለሚመለሱበት ሁኔታ ተከታታይ ውይይቶች ተደርጎ ስምምነት ላይ መደረሱን ደግሞ የጋራ ግብረኃይሉ ኮሚቴ አባል አቶ በትግሉ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ