1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተኩስ አቁሙ፤ እስር እና #NoMore ንቅናቄ

ዓርብ፣ ኅዳር 10 2014

በኢትዮጵያ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አስተላልፏል። በዓለምአቀፍ መገናኛ አውታሮችና ተቋማት ብሎም ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫናና ጣልቃ ገብነት ያብቃ በሚል የ#NoMore ንቅናቄ አጀምሯል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየቶች ተሰባስበዋል። 

https://p.dw.com/p/43Cvd
Symbolbild Äthiopien Tigray-Krise | Ausnahmezustand
ምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

በሰሜን ኢትዮጵያ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አስተላልፏል። በርካታ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች፦ በዓለምአቀፍ መገናኛ አውታሮች እና ተቋማት ብሎም ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና እና ጣልቃ ገብነት ያብቃ ሲሉ የ#NoMore ንቅናቄ አስጀምረዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል፤ አብዛኞቹ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ናቸው ተብሏል። 

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በሳምንቱ ዐበይት መነጋገሪያ የነበሩ ሦስት ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ውስጥ የተኩስ አቁም በፍጥነት እንዲደረግ እና ተፋላሚዎች ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አስተላልፈዋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ውይይት ይጀመር መባሉን ሲደግፉ ሌሎች ደግሞ ይኼን ሲቃወሙ ተስተውለዋል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ #NoMore ወይንም ከእንግዲህ በቃን የሚል መልእክት በማስተላለፍም የመልእክቱን መሪ ቃል በዓለም ዙሪያ እንዲዳረስ ወደ ንቅናቄ ቀይረውታል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ስላለው እስር በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶችም አሰባስበናል።

የተኩስ አቁም ጥሪ፦

በሰሜን ኢትዮጵያ የቀጠለው ጦርነት እንዲቆም እና የሰላም ድርድር እንዲጀመር በዋናነት ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮጳ ሃገራት እየወተወቱ ነው። ግድያ፤ ውድመት እና ስደቱን ያስቆማል ሲሉ የሰላም ጥሪውን ያወደሱ እንዳሉ ሁሉ፦ የለም ሕወሃት ጊዜ እንዲገዛ ምዕራባውያኑ ሊታደጉት ፈልገው እንጂ የኢትዮጵያ ሰላም ገዷቸው አይደለም የሚሉም አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

ጦርነቱ በትግራይ ክልል ጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ከመሻገሩም በፊት አንስቶ በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ጊዜያቶችን እና ኹኔታዎችን እየጠበቀች በከፍተኛ ባለሥልጣናቶቿ በኩል ማስጠንቀቂያዎችን ስትሰነዝር ቆይታለች የሚሉ ወገኖች ከማዕቀብ አንስቶ፤ እንደ አጎዋ ያሉ በዋናነት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች የሚጠቀሙበትን ዕድል እስከመዘረዝ መድረሱንም ተቃውመዋል።

Screenshot DW Interview mit Obasanjo

በዚሁ ሳምንት ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አንቶኒ ብሊንከን ሐሙስ ወደ ናይጄሪያ ከማቅናታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ ባለሥልጣናቱን አናግረዋል። ናይጀሪያ እና ሴኔጋል ከኬንያ ሌላ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ የሚጎበኟቸው ሃገራት ናቸው። ሦስቱም ሃገራት መሪዎች በጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝተዋል። የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ራይቼሌ ኦማሞ ተኩስ አቁም ተደርጎ ድርድር ይኖራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ  ተስፋቸውን ከአንቶኒ ብሊንከን ጋር ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ዐስታውቀዋል። ከንግግራቸው ቀጣዩ መልእክታቸው በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተንሸራሽሯል።

«በኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናት እና ጥበብ ልናምን ይገባል። ምክንያቱም በስተመጨረሻ መፍትኄው የሚመጣው ከእነሱ ነው። እንደ ጎረቤት ማድረግ ያለብን፤ ግጭቱ ሲያከትም፤ ያከትማል ብለንም እናምናለን፤ ያኔ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር እንደሆነች፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር እንደሆነች ብሎም ለቀጠናው ሰላም ዳግም ዋስትና የምትሰጥ ሀገር እንደሆነች ለማረጋገጥ ትክክለኛውን አቅጣጫ በማመላከት ድጋፍ መስጠት ነው፤ ማማከር ነው፤ እጃችንን መዘርጋት ነው። »

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ያሰሙትን ንግግር በርካቶች #NoMore ከሚል የሐሽታግ መልእክት ጋር አያይዘው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አሰራጭተውታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ድርድር እንዲደረግ የቀረበው ሐሳብ ላይ ግን ድጋፍ እና ተቃውሞው ቀጥሏል።

አማኑኤል ዮሐንስ ትዊተር ባሰፈሩት መልእክታቸው፦ «በሀገራችን ሉዓላዊነት ድርድር ዐናውቅም» ብለዋል በአጭሩ። ዮሐንስ ምንሊክ በአማርኛና እንግሊዝኛ በተቀላቀለ የትዊተር ጽሑፋቸው፦ «ድርድር፤ የተመረጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን አላካፍልም በማለቱ እንዴት መማረክ እንደሚቻል» ብለዋል በምጸት። ጎይቶም አረጋዊ ትዊተር ላይ «አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጦርነቱ እንዲያበቃ እየገፉ ነው» ሲሉ ጽፈዋል። ኸንግዱ ዘይቴ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ድርድር የሚባል አያስፈልግም» የሚል መልእክት በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስፍረዋል። «አንባገነን» ያሉትን መንግሥት ማስወገድ እንደሚፈልጉም አክለዋል። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጠቃሚዎች ድርድሩን በመቃወም #NoMore ከሚል የሐሽታግ መልእክት ጋር ሐሳባቸውን አንጸባርቀዋል። በዚሁ በከፍተኛ ፍጥነት ስለተስፋፋው #NoMore እንቅስቃሴ እንሻገር።

የ#NoMore ንቅናቄ፦

10 Jahre Hashtag
ምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

በትዊተር የሐሽታግ መልእክት #NoMore በሚል የተጀመረው ዘመቻ አሁን በሂደት ወደ ንቅናቄ ማደጉ እየተገለጠ ነው። መልእክቱን ያስጀመረችው ነዋሪነቷ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሆነችው ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ናት። ቤተሰቦቿ ከትግራይ እንደሆኑ የተናገረችው ሔርሜላ በአንድ ወቅት በጭፍን ለህወሃት ድጋፍ ታደርግ እንደነበር በመጥቀስ ነገሮች ሲገለጡልኝ ግን ስህተት መሆኑን ተረዳሁ ስትል ከዚህ ቀደም ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ተናግራለች። በተለይ በዓለም አቀፉ መገናኛ አውታሮች በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ የተጀመረው ዘመቻን ስለመታገልም ከጓደኞቼ ጋር መከርኩ ያኔም #NoMore የተሰኘው ሐሽታግ መልእክት ተጀመረ ብላለች። በዚህ ሐሽታግ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመላው ዓለም መልእክቶችን እያስተላለፉ ነው። ሐሽታጉ በከፍተኛ ደረጃ መታየት በጀመረበት ወቅትም ትዊተር ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶችን ለማስወገድ ሲል ይህ ሐሽታግ ከፍ ብሎ እንዳይታይ አድርጎታል። ይክን የትዊተር ርምጃ  በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ሰዎችን ድምጽ የማፈን ኢዴሞክራሲያዊ የትዊተር ድርጊት ሲሉ ኮንነውታል። በነገራችን ላይ ሐሽታግ በትዊተር የሚተላለፉ መልእክቶችን በአጭሩ በርካታ ሰዎች ጋር እንዲደርስ የማድረጊያ ስልት ነው።

እምሻው እስከዳር በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሰፈረ የትዊተር መልእክታቸው፦ «በውጭ ሃገራት ያሉ ሌሎች አፍሪቃውያን እና በመላ ዓለም የሚገኙ ጥቁሮችን በማወያየት ተደራጁ» ብለዋል።  ጦርነቱ «ምዕራባውያን አፍሪቃን ለመቦጥቦጥ እና ግጭቶችን ለመደገፍ የሚያደርጉት ዘመን የፈጀ ፍላጎታቸው ነው» ሲሉም አክለዋል።  

Karte Uganda Rwenzori Kasese Englisch

ዩጋንዳዊው ፖለቲከኛ ማቱዋ ጆብ ሪቻርድ #NoMore ከሐሽታግ መልእክት ወደ ንቅናቄ ከፍ ማለቱን ትዊተር ላይ ጽፈዋል፦ «የኢትዮጵያ ጸረ ኢምፔሪያሊዝም ተጋድሎ የዩጋንዳ ምዕራፍ የተሰኘ ቡድን ለመመስረት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሰናል» ብለዋል። ፉቱሪካል ከተባሉ እና በርካታ ተከታዮች ካላቸው ሌላኛው ዩጋንዳዊ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚ ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየታቸውንም ገልጠዋል።  «ራሳችንን በማደራጀት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚካኼደው በአፍሪቃ ላይ ስለተከፈተው ጦርነት የሚደረገውን ክርክር ቅርጽ ለማስያዝ ሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ አውታሮችን በትጋት እንዲሠሩ እናደርጋለን» ሲሉም አክለዋል። ሌሎች አፍሪቃውያን፦ ከናይጄሪያ፣ ከኬንያ እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገሮች በዚሁ የሐሽታግ #NoMore አስተያየታቸውን እያሰፈሩ ይገኛሉ። ከአፍሪቃውያኑ ባሻገርም በተለያዩ የአውሮጳ እና የአሜሪካ ሃገራት የሚገኙ ሰዎችም ሐሽታጉን በመጠቀም ላይ ናቸው።

የ#NoMore እንቅስቃሴ ስለዓለም ፖለቲከኞች፣ ምሑራን እና የመገናኛ አውታሮች  አድልዎ በስፋት እየተነገረ ነው። የአሜሪካ መንግሥት እና የምዕራቡ ዓለም ሃገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን መጠን ያለፈ ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች በተለያዩ ሃገራትም እየተደረጉ ነው።  

እስር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፦

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ መንግሥት ለሕወሓት ድጋፍ የሚያደርጉ በሚል ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን በርካታ ሰዎችን ማሰሩ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ኾኗል። የሰዎቹን መታሰር የሚቃወሙም የሚደግፉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

Bildcombo I Abiy Ahmed und  Uhuru Kenyatta

ምስግና ዓለም የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደረገው እስር እና እንግልት ይቁም» ሲሉ ጽፈዋል። ግርማ ጌታሁን ደግሞ «በሥራቸው እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ሕጉ በሚያዘው መሠረት ሊታሰሩ ይችላሉ» ብለዋል በፌስቡክ ጽሑፋቸው።  ኪዳኔ ትግራዋይ የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው፦ «ተጋሩ በመሆናቸው ብቻ የሚደረገው የቤት ለቤት እስር መቆም አለበት» ብለዋል። ማቴዎስ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛአውታር ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ተጠርጥሮ መታሰር ወንጀለኝነት አይደለም» ሲሉ ጽፈዋል።  «እከሌ ይሄ ስለሆነ የሚሉ ምክንያቶችን ይዘው የሚቀርቡ ሰዎች ይገርሙኛል ይልቁንስ ለምን ታሰረ ከሚሉ የተፋጠነ ፍትሕ ቢጠይቁ ያሳምነን ነበር» ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ረቡዕ፤ ኅዳር 8 ቀን፣ 2014 ዓ.ም.ባወጣው መግለጫው፦ «ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የተካሄዱ እስሮች እና የታሳሪዎች ሁኔታ አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ ነው»  ብሏል። ኮሚሽኑ ስለታሰሩ ሰዎች ሙሉ መረጃ ማግኘት አለመቻሉንም ጠቅሷል። በአንጻራዊነት የተሟላ መረጃ አገኘሁ ባላው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ «መረጃው በተሰጠበት ኅዳር 2 ቀን፣ 2014 . ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ 714 ሰዎች መታሰራቸውንና ከነዚህም ውስጥ 124 ሴቶች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል» ብሏል። «በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው ይገመታል» ሲልም አክሏል።

Äthiopien | Stadtansicht von Addis Abeba
ምስል Thomas Imo/photothek/imago images

«በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ እስከ 300 የሚሆኑ ሰዎች ታስረዋል» ብሏል ኮሚሽኑ። አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች፦ «የተያዙት በብሔራቸው ምክንያት እንደሆነ እንደሚያምኑና እና የተጠረጠሩበትን እና የተያዙበትን ምክንያትም እንዳልተነገራቸው» ቅሬታቸውን መግለጣቸውንም ኮሚሽኑ ገልጧል።

የፀጥታ አካላት ስለ እስሩ ተጠይቀው፦ «ሰዎች የሚያዙት በብሔራቸው ምክንያት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ተጠርጥረው እንደሆነና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሁለቱም ድርጅቶች ብሔር ተኮር ድርጅቶች ከመሆናቸው አኳያ የሚያዙ ሰዎች የአንድ ብሔር ሊመስሉ እንደሚችሉ» መናገሩን ኢሰመኮ ጠቅሷል። ፖሊስ ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ የፀጥታ ግብረ-ኃይሉ ቁጥጥር ሲያደርግ «ዘርን፣ ብሔርን፣ እምነትን» መሰረት እንደማያደርግ ዐሳውቋል።  ይልቁንም ፖሊስ «የሽብር ኃይል» ያለውን «በመደገፍ ሀገርን የማፍረስ ተግባር ላይ የሚሳተፍና የሚደግፍ አካል»ን  እየተቆጣጠረ መሆኑንም አክሏል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ