1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጅጅጋ እስከ ቦን ጀርመን

ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2012

የእንሰሳት ሳይንስ ምሑር ናቸው።በዚሁ የትምሕርት ዘርፍ ከዓለማያ ግብርና ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ከጀርመኑ የቦን ዩኒቨርስቲ የማስተርስ እና የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው።የድሕረ ዶክትሬት ዲግሪ መርኃ ግብር የተከታተሉትም በዚሁ በቦን ዩኒቨርስቲ ነው።በተማሩበት ዩኒቨርስቲ ለ15 ዓመታት  በጥናት እና ምርምር እንዲሁም በማስተማር አገልግለዋል።

https://p.dw.com/p/3Que1
Universität Bonn | Professor Dawit Tesfaye & Team
ምስል Dawit Tesfaye

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳዊት ተስፋዬ

በቦን ዩኒቨርስቲ የግብርና ትምሕርት ክፍል ስር በሚገኘው በእንሰሳት ሳይንስ ተቋም ባልደረባነት ለ15 ዓመታት ያገለገሉት የተባባሪ ፕሮፌሰር ዳዊት ተስፋዬ ጥናት እና ምርምር በወተት ከብት ልማት ላይ ያተኮረ ነው። ጥናታቸው ከብቶችን ማዳቀልንም ይጨምራል። የዶክትሬት ዲግሪያቸው ጥናት በተለይ ብዙ ወተት የሚሰጡ ላሞች ፣ጽንስ መጨናገፍ መንስኤ እና መፍትሄ ላይ ያተኩራል።ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳዊት እንዳሉት ይህ ምርምር ለከብቶች ብቻ ታስቦ የሚካሄድ አይደለም።ዶክተር ዳዊት የተወለዱት ያደጉት እና የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት ጅጅጋ ነው። ከፍተኛ ትምሕርታቸውን ደግሞ በያኔው አጠራር በዓለማያ የግብርና ዩኒቨርስቲ ነው የተማሩት። ለቤተሰባቸው ሰባተኛ ልጅ የሆኑት ዳዊት ከቤተሰብ በኩል ሌላ የትምሕርት መስክ እንዲመርጡ ግፊት ነበረባቸው። ሆኖም የርሳቸው ምርጫ በሆነው  በእንሰሳት ሳይንስ ጸንተው መቀጠላቸውን ትክክለኛ ውሳኔ ይሉታል። ከዓላማያ ትምሕርታቸውን እንደጨረሱ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰርተዋል። ለድህረ ምረቃ ትምህርት ወደ ቦን ዩኒቨርስቲ ከመምጣታቸው በፊት«ሰዎች ለሰዎች» በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ አገልግለዋል። የዛሬ 22 ዓመት በመጡባት በቦን ከድህረ ምረቃ ትምሕርታቸው ቀጥሎ የዶክትሬት ትምሕርት እድል አግኝተው ምርምራቸውን በመቀጠል ካጠናቀቁ በኋላ የድህረ ዶክትሬት ድግሪ መርሃ ግብርም ተከታትለው እዚያው የተማሩበት ተቋም በጎርጎሮሳዊው 2004 ነበር በረዳት ፕሮፌሰርነት ማገልገል የጀመሩት።ዶክተር ዳዊት እና ባልደረቦቻቸው እዚህ ቦን ከወተት ምርት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ የረቀቁ ምርምሮች አካሂደዋል።እነዚህ ሥራዎች ግን ወደ ኢትዮጵያ አልተሻገሩም።ይሁን እና በርሳቸው እምነት ቢያንስ  ከብቶችን በማዳቀል በኢትዮጵያ የተሻለ የወተት ምርት ማግኘት ስለሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።ዶክተር ዳዊት እንደሚያስረዱት በአሁኑ ጊዜ በቦን ዩኒቨርስቲ ስር ያለው የግብርና ትምሕርት ክፍል የእንሰሳት ሳይንስ ተቋም ኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሠራ ነው።
በቦን ዩኒቨርስቲ በተመራማሪነት በመምህርነት እንዲሁም በተማሪዎች አማካሪነት የሠሩት ዶክተር ዳዊት በ15 ዓመታት አገልግሎታቸው ከሚያስደስታቸው ውስጥ ርሳቸው የተሰማሩበት የተቋሙ የምርምር ዘርፍ መስፋፋቱና እውቅናውም መጨመሩ አንዱ ነው። ተማሪዎቻቸው በሥራው መስክ ተፈላጊ ሲሆኑ ማየትም ሌላው እርካታቸው ነው።
ባለትዳርና የሦስት ሴቶች ልጆቻቸው አባት  ዶክተር ዳዊት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳዊት በአሜሪካኑ የኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ሥራ ግን ከፍ ባለ ደረጃ የስራ እድል አግኝተው ወደዚያው ከሄዱ አንድ ሳምንት አልፏቸዋል። 

Universität Bonn | Professor Dawit Tesfaye & Team
ምስል Dawit Tesfaye
Universität Bonn | Professor Dawit Tesfaye & Team
ምስል Dawit Tesfaye

ኂሩት መለሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ