1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ሲታወሱ

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለረጅም ጊዜ የሥነ ጽሑፍ መምህር፣ ሐያሲና ተመራማሪ የነበሩት ተባባሪፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ከትናንት በስተያ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል። የስነጽሑፍ ምሁሩን ሥራዎች በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች «የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ዋርካ ነው የወደቀው» ይላሉ።

https://p.dw.com/p/4OSyD
Assistant Professor Zerihun Assfaw
ምስል Solmon Muche/DW

«የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ዋርካ ነው የወደቀው» የባህል መድረክ

«የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ዋርካ ነው የወደቀው» ይህ ምስክርነት ሰኞ ዕለት የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ሌሊት በድንገት ታመው ስላረፉት ፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና ተማሪዎቻቸው «የሥነ ጽሑፍ ዋርካው»  ስለሚሏቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የተሰጠ የመልካም ሥራ ውጤት የምስክርነት ቃል ነው። ላለፉት 40 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥነ ጽሑፍ መምህርነት በርካቶችን ያስተማሩና ያገለገሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ጥናት እና ምርምሮችን በመሥራት፣ በአርትዖት እንዲሁም በበሳል ሃያሲነታቸውም በወዳጆቻቸው ይጠቀሳሉ።
ወጣት ደራሲያን እና ተመራማሪዎች እንዲበረታቱ በነፃ  በማማከር እና ድጋፍ በመስጠት ወደር የለሽ በጎ የሙያቸውን ሥራ መፈፀማቸውም ይነገራል።

«የሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን» እና «ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ» የተባሉትን የሥነ ጽሑፍ ትምህርት አጋዥ መጻሕፍትን እንዲሁም ልዩ ልዩ የጥናት ጽሑፎችን ጨምሮ አራት መጻሕፍትን
ማሳተማቸውና ለተደራሲው ማበርከታቸውም ትናንት ረቡዕ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ውስጥ ባልደረቦቻቸው ምሁራን ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ፣ ደራሲዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ የመንግሥት ተሿሚዎች እና ወዳጆቻቻቸው በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው ሲፈፀም ተነግሯል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ካስተማሯቸው ብዙ ደራሲያን መካከል በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሚያገለግሉት እና በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያዋ ሴት የአጭር ልብ ወለድ አሳታሚ ወይም ጸሐፊት የዝና ወርቁ አንዷ ናቸው።
«ጋሽ ዘሪሁን ትዕግስተኛ ፣ መካሪ ነበር። ኢትዮጵያ እጅግ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ምኁር ነው ያጣችው።» ብለዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የሚለውን ሥም ከብዙ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሬድዮ ቅዳሜ የኪነ ጥበባት ምሽት በተባለው ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ስለ የመጀመርያው አጭር ልብ ወለድ «የጉለሌው ሰካራም» ጥናት ሲያቀርብ ነበር የሰማሁት ያለው ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበበ ከዚያ በኋላ ይበልጥ መተዋወቃቸውን በሀዘን ስሜት ሆኖ ነግሮናል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ከፍ ዝቅ ውስጥ ምን አበረከቱ ? የሚለውን በመመለስ ይጀምራል።

Assistant Professor Zerihun Assfaw
የስነጽሑፍ ምሁሩ ያዘጋጁት መማሪያ መጽሐፍምስል Solmon Muche/DW

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋል በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር በነበረው የአለማያ ግብርና ኮሌጅ በረዳት ምሩቅነት ደረጃ ተቀጥረው እስከ ሌክቸረርነት ደረጃ በመምህርነትና በተከታታይ ትምህርት አስተባባሪነት ማገልገላቸው የሕይወት ታሪካቸው ሲነበብ ተገልጿል።

ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋና ፎክሎር ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ውስጥ በተለያዩ ማዕረጎችና ኃላፊነቶች አገልግለዋል። ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በርካታ ተማሪዎችን ከማስተማርና ከማሰልጠን ጎን ለጎን 143 የመጀመሪያ ፣ 80 የማስተርስ ፣ እንዲሁም 20 የዶክቶሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በምርምር ሥራዎቻቸው ማማከራቸው ተዘርዝሯል። ከእነዚህ ምካከል አንዱ ከያኒ አንዱዓለም አባተ የአፀደ ልጅ ይገኝበታል።

ጥቅምት 10 ቀን 1944 ዓ.ም በደሴ ከተማ የተወለዱት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ደሴ ተከታትለዋል። ሌሎች የትምህርት ደረጃዎችን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከውነዋል። የቅርብ ወዳጅ ባልደረቦቻቸው ታዲያ «መረጃችንን ተነጠቅን» በማለት እንደ ህያው ማጣቀሻ ሆነው ለብዙዎች ማብራታቸውን ይመሰክራሉ።

የሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን ፣ ልቦለዳዊያንና የቀደምት ደራስያን አጫጭር ትረካዎች ፣ ሥነ ጽሑፍ ለማኅበራዊ ለውጥ ፣ ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ ፣ በሥነ ጽሑፍና በፎክሎር የተሰሩ የዲግሪ ማሟያ ጥናቶችና አጠቃሎ ስብስብ የሚሉት አምስት ሥራዎች እኒህ አንጋፋ ባለሙያ ለንባብ ያበቋቸው የሕትመት ውጤቶች ናቸው።
እኒህን ሰው ማጣት «የተደገፍክበት ወንበር ድንገት ሸርተት ሲልብህ» ያለውን ስሜት የሚፈጥር ነው በማለት ከያኒ አንዷለም አባተ ገልጿል።

Assistant Professor Zerihun Assfaw
የተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ሥርዓተ ቀብር ምስል Solmon Muche/DW

በተወለዱ በ71 ዓመታቸው የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ያለፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ለ40 ዓመታት በትዳር አብረው ከቆዩት ከባለቤታቸው ከወ/ሮ የትምወርቅ አካሉ ሦስት ወንድና አንድ ሴት፤ አምስት ልጆች አፍርተው እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል። ደራሲት የዝና ወርቁ ስለ አስተማሪያቸው ሲገልጹ «ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሐፍ ምን ያላበረከተው አለ» ብሎ በመጠየቅ ነው።

አርቲስት ተስፋዬ አበበ ( ፋዘር ) እንዳስተማሯቸው፣ በልጅነት ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት እያሉ ሙዚቃ ይጫወቱ እንደነበር፣ ብዙ የህይወት ልምዶች እንደነበሯቸው ፣ ነገር ግን «ምን ሠራሁ» የሚል ትህትና የተላበሱ እና በመገናኛ ብዙኃን ብዙም ቀርበው የማይታዩና የማይደመጡ ቁጥብ ሰው እንደነበሩ በቅርበት የሚያውቃቸው ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ አጫውቶናል። ነፍስ ይማር።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ