1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች

ሐሙስ፣ ሐምሌ 25 2011

33 በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅርቡ በተቋቋመው የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተዘጋጅቶ የቀረበው የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ይዘቱ የዜጎችን የመደራጀት፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የሚገድብ በመሆኑ ከመጽደቁ በፊት ተመልሶ ለውይይት መቅረብ አለበት ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3NBNt
Äthiopien | Parteien lehnen das neue Parteien- und Wahlgesetz ab
ምስል DW/S. Muchie

«አዲሱ ረቂቅ ከመጽደቁ በፊት ለውይይት እንዲቀርብ»

ፓርቲዎቹ ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ቢሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ ሕጉ ላይ ውይይት አድርገንበት የነበር ቢሆንም አሁን የቀረበው ግን ከተወያየንበት ውጭ የሆነና የማናውቀው ሕግ በመሆኑ በምርጫ ቦርድ ክህደት ተፈጽሞብናል ብለዋል። ፓርቲዎቹ እንዳሉት የተዘጋጀው ሕግ ነባር የፓለቲካ ፓርቲዎችን የሚያከስም ፤ አዳዲሶችም እንዳይታሰቡ የሚያደርግ አፋኝ ሕግ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ የሚወዳደሩ ከሆነ የ6 ወር ደሞዛቸው ሳይከፈላቸው መደረግ ይኖርበታል የተባለውም ተገቢ ያልሆነ ነው ካሉ በኋላ ተግባራዊ ይሁን ከተባለ ግን መጀመር ያለበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሆኑን መንግሥት ሊያረጋግጥ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል። መንግሥት አጠቃላይ የምርጫ ሥርአቱን አሻሽላለሁ በሚል ቃል የገባውን ነገርም ከመተግበር መቆጠበን እየተገነዘብን በመሆኑ ይህ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል። ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝሩን ልኮልናል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ