ያሕያ ጃሜሕ ስልጣን ለማስረከብ ተስማሙ
ቅዳሜ፣ ጥር 13 2009ማስታወቂያ
ትናንት ማምሻውን ፕሬዘዳንቱ ይህን በመንግስታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ የተናገሩት ከጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ እና ከሞሪታኒያው አቻቸው ሞሐመድ አብዱል አዚዝ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው፡፡ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ወደ ጋምቢያ ያቀኑት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ለጉዳዩ ዕልባት ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ከከሸፈባቸው በኋላ ነው፡፡ የጃሜሕን እምቢተኝነት በኃይል ለመቀልበስ የተንቀሳቀሱት ሁለቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት- ናይጄሪያ እና ሴኔጋል - 7000 የሚጠጉ ወታደሮቻቸውን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ወደ ጋምቢያ ልከዋል፡፡ በታንኮች እና ተዋጊ አውሮፕላኖች የተደገፈው የሁለቱ ሀገራት ጦር ወደ ጋምቢያ ሲገባ ከጃሜህ ሰራዊት ምንም አይነት መከላከል እንዳልገጠመው ተዘግቧል፡፡ የወታደሮቹ አካሄድ ምርጫ ያሳጣቸው የሚመስሉት ጃሜህ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ የወሰኑት ለ“ሀገር ጥቅም” ሲሉ እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡ ሀገሪቱ በገባችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ምንም ዓይነት ደም መፋሰስ አለመከሰቱንም አወድሰዋል፡፡ ወደ ሌላ ሀገር ይሰደዱ አሊያም በሀገር ቤት ይቆዩ እንደሁ በንግግራቸው ፍንጭ አልሰጡም፡፡ የጃሜህን ውሳኔ ተከትሎ ምርጫው ያሸነፉት እና ሐሙስ ዕለት ሴኔጋል በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ቃለ-መሃላ የፈጸሙት አዳማ ባሮው ወደ ባንጁል እንደሚመለሱ ተዘግቧል፡፡
እሸቴ በቀለ
ልደት አበበ