1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተስፋ ያልቆረጠው የቀላል አይሮፕላን ሰሪ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 10 2012

የልጅነት ህልሙን ለማሳካት ተስፋ ሳይቆርጥ የሚያጣጣረዉ አስመላሽ ዘፈሩ ከአራት ዓመት በፊት የመጀመሪያውን ቀላል አይሮፕላን ሰርቶ የሙከራ በረራው ሳይሳካ መቅረቱን አጫውቶን ነበር። አሁን ያለፈዉን ጉድለት «አሻሽዬ» ሌላ አዲስ አይሮፕላን ሰርቼ የሙከራ በረራ ብቻ ለማድረግ እየተጠባበኩኝ ነው ይለናል።

https://p.dw.com/p/3V6Zc
Äthiopien Asmelash Zefer | Bau K-570 A 2 Ultraleicht-Flugzeug
ምስል privat

አስመላሽ ዘፈሩ

የልጅነት ህልሙን ለማሳካት ተስፋ ሳይቆርጥ የሚያጣጣረዉ አስመላሽ ዘፈሩ ከአራት ዓመት በፊት የመጀመሪያውን ቀላል አይሮፕላን ሰርቶ የሙከራ በረራው ሳይሳካ መቅረቱን አጫውቶን ነበር። አሁን ያለፈዉን ጉድለት «አሻሽዬ» ሌላ አዲስ አይሮፕላን ሰርቼ የሙከራ በረራ ብቻ ለማድረግ እየተጠባበኩኝ ነው ይለናል። 
የልጅነት ህልሙን ለማሳካት ተስፋ ሳይቆርጥ የሚያጣጣረዉ አስመላሽ ዘፈሩ ከአራት ዓመት በፊት የመጀመሪያውን ቀላል አይሮፕላን ሰርቶ የሙከራ በረራው ሳይሳካ መቅረቱን አጫውቶን ነበር።

ከአራት ዓመት በፊት በዚሁ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን ከነበረው አስመላሽ ዘፈሩ ጋር ስንሰነባበት ለመጀመርያ ጊዜ የሰራት ባለ ሁለት መቀመጫ አይሮፕላኑ እንደምኞቱ ሳታኮበኩብ የቀረችበትን ምክንያት በሳምንት ጊዜ አጣርቶ ዳግም የሙከራ በረራ እንደሚያደርግ ገልፆልን ነበር። ግን ይህም ሳይሆን ቀረ። ከጣውላ የሰራት የዚያች ቀላል አይሮፕላን ችግር በቀላሉ የሚፈታ አልነበረምና። «ጠቅላላ ክብደቷ ወደ 600 ኪሎ ግራም ነበር። የሞተሯ አቅም ደግሞ ወደ 40 የፈረስ ጉልበት ነበር። እና ያ ስላልተመጣጠነና አቅሙ ውስን ስለነበር ነው መብረር ያልቻለው።» ይላል አስመላሽ ስለሆነም አይሮፕላኑን እንደ አዲስ መስራት ነበረበት።  አስመላሽ ተስፋ ሳይቆርጥ ጊዜ ወስዶ አሁን አዲስ የሰራት ሁለተኛዋ አይሮፕላን ከመጀመሪያው ለየት የሚያደርጋት አንዳንድ ነገሮች አሉ። ያለፈው ጊዜ ሁለት ሰዎችን የምትይዝ ሲሆን የአሁኗ ደግሞ ባለ አንድ መቀመጫ ናት። በዛ ላይ ክብደቷ 115 ኪሎ ግራም ናት።  

Äthiopien Flugshow Asmelash Zeferu
ምስል Asmelash Zeferu

ከዚህ በፊት የሙከራ በረራውን ሰንዳፋ ላይ ያደረገው አስመላሽ አሁን የሰራትንም ቀላል አይሮፕላን በዚሁ አካባቢ ወይም አዳማ አካባቢ ለመሞከር የሚያስችለው ሰፋ ያለ ሜዳ እያፈላለገ ነዉ። ቀረኝ የሚለው ፍቃድ መጠየቅ ብቻ ነው። ይህንንም እስከ መጪው የካቲት ወር ለማጠናቀቅ ይፈልጋል። « ፍቃድ አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ» ይላል። 
ፈተናው መብረር የሚችል አይሮፕላን መስራት ብቻ ሳይሆን ማብረሩም ነው። እስካሁን ድረስ አስመላሽ ራሱን ችሎ ምንም ዓይነት አይሮፕላን አብርሮ አያውቋም። ይሁንና ለዚህም ብቁ ዝግጅት ማድረጉን ይናገራል።« በአንዴ ተነስቼ ለመብረር አይደለም የምመክረው። እየተነሳሁ እያረፍኩ በራሴ አይሮፕላን እየተለማመድኩ ነው የሚሆነው። 
በዚህ ጊዜ ውስጥ አስመላሽ ሌላኛው ህልሙን አሳክቷል። ከቀድሞ ፍቅረኛው ጋር ትዳር መስርቶ የአንድ ልጅ አባት ሆኗል። ልጁንም ሮቢንሰን ነው ያለው። የማብረር ምኞቱን ለማሳካት ጊዜውን ብቻ ሳይሆን ብዙ ገንዘብም እንዳወጣ የሚናገረው አስመላሽ የመጀመሪያው አይሮፕላን 160 000 የኢትዮጵያ ብር ፈጅቶበታል። የአሁኑን አጠቃላይ ወጪ ግን ገና አልደመረውም። በትርፍ ጊዜው ቀላል አይሮፕላን የሰራው አስመላሽ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፈጥሮ እና አካባቢ ጥበቃ የቡድን መሪ ሆኖ በአሁን ሰዓት ያገለግላል።የሚሰራበት የሙያ ዘርፍ ከልጅነት ህልሙ ጋር የተለየበት ምክንያት ግን በራሱ ፍቃድ አልነበረም። « በ1996 ዓም አለማያ ዮንቨርስቲ ስገባ ጤና መኮንን ነበር የተመደብኩት ። ስመደብ በግዴታ ስለነበር ፍላጎቴን ላሏላ አልቻልኩም። በወቅቱ የደሀ ልጅ ስለነበርኩ እና የግድ ዲግሪዬን መያዝ ስለነበረብኝ በግዴታ ተማርኩ»

Äthiopien Asmelash Zeferu Flugzeugbauer EINSCHRÄNKUNG
ምስል Asmelash Zeferu

አስመላሽ አዲስ የሰራት አርትራላይት ወይም እጅግ ቀላል አይሮፕላን መጠሪያ K- 570 A 2 ትባላለች። K  የናቴ ስም ኪሮስ ስለሆነ ነው። ያለፈውን አይሮፕላን ለመስራት ደግሞ የፈጀብኝ ጊዜ 570 ቀናት ነው።  A ደግሞ ኤርክራፍት ለሙለው ነው። » ይላል። በቀጣይ ሙከራው ከተሳካ ተመሳሳይ አይሮፕላኖችን ወደፊት ማምረት ቀጣይ እቅዱ እንደሆነ የሚናገረው አስመላሽ አይሮፕላኖቹ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ ውለው ያስገኛሉ ስለሚለው ጥቅምም ገልፆልናል። በተለይም ለእርሻ ስራ አገልግሎት እና መድሃኒት መርጫነት ሊያገለግል ይችላል ይላል።

አስመላሽ አይሮፕላን ለማብረርም ይሁን አይሮፕላን ለመስራት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ከመፀሀፍት እና ከ ዩ ቱይብ ቢመለከትም ብዙ ያማክሩኛል የሚላቸው ባለሙያዎች አሉ። አብዛኞቹም የቀድሞ የአየር ኃይል ባልደረቦች እና ጡረታ የወጡ የአየር መንገድ ሰራተኞች ናቸው። ስለሆነም አስመላሽ ዘፈሩ የመብረር እድሉ ባሁኑ ከፍተኛ እንደሆነ ያምናል። 


ልደት አበበ 

ነጋሽ መሐመድ