1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተስፋ የተጣለባት ኢትዮጵያዊቷ ወጣት የአውሮፕላን መሀንዲስ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 12 2013

ወጣት ቤቴልሄም ግርማ በኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ረዳት ተመራማሪ ስትሆን በእርሻ ድሮን ዲዛይን እና ልማት በመስራት ላይ ትገኛለች። ወጣቷ ከ 30 ዓመት በታች ካሉ ምርጥ 10 የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዝርዝር ከተካተቱ ጥቂት የአፍሪቃ ሴቶች መካከል አንዷ ሆና የተመረጠች ኢትዮጵያዊት ወጣት ነች።

https://p.dw.com/p/3z8N7
Bethelehem Girma
ምስል privat

ተስፋ የተጣለባት ኢትዮጵያዊቷ ወጣት የአውሮፕላን መሀንዲስ 



አፍሪቃ ከዓለም ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ያላት አህጉር ስትሆን ፣አሁን አሁን እነዚህ ወጣቶች   አህጉሪቱን  ሊያሻሽል የሚችል  ፈጠራ እና መሠረተ -ሐሳቦችን እያበረከቱ በመሆናቸው  የአህጉሪቱ የጠፈር  ምርምር  ኢንዱስትሪ እያደገ  መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
 እነዚህ ወጣቶች አፍሪቃ በዓለም የጠፈር ሳይንስ ምርምር ውስጥ ቦታ እንዲኖራት ለማድረግ የሚደረገውን ሂደት በማበረታታት ለኢንዱስትሪው የላቀ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን  የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ሽልማት ድርጅት በቅርቡ የወጣው መረጃ ያሳያል። ከነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊቷ የአውሮፕላን  ምህድስና ባለሙያ ቤተልሄም ግርማ አንዷ ነች።
ወጣት ቤቴልሄም ግርማ በኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ረዳት ተመራማሪ ስትሆን  በእርሻ ድሮን ዲዛይን እና ልማት  በመስራት ላይ ትገኛለች። ወጣቷ እንደምትለው በዚህ ዘርፍ እንድትሰራ ያደረጋት በኢትዮጵያ የሚታየው ኋላ ቀር  የግብርና ዘዴ  ነው።
«በሃገራችን የተለያዩ አርሶአደሮች የሚጠቀሙት የተለያዩ ዘዴዎች  ኋላቀር የሆኑ አሰራር ነው ያላቸው። በመጀመሪያ ደረጃ በአርሶ አደሩ ላይ የሚያመጡት ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር አለ። ይህ የሚከሰተው አርሶአደሩ ፀረ-ተባይ ወይም ደግሞ ማዳበሪያ ለመርጨት ብዙ ጊዜ ተጋላጭ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ ኬሚካሎች በጤናው ላይ የሚያደርሱት ትልቅ የሆነ ተፅዕኖ አለ።ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ምርታማነትን በጣም የሚቀንሱ አሠራሮች ናቸው በብዛት ያሉት። ለምሳሌ ስንመለከት ብዙ ጊዜ አርሶአደሩ በዓይኑ በሚመለከተው ነገር ብቻ ላይ  ብቻ ነዉ የሚመሰረተው ። ስለዚህ መጠኑ ሳይታወቅ በግምት ብቻ ፀረ-ተባዩን ወይም ማዳበሪያውን  ደርጋል። ይብዛ እና  ይነስ አይታወቅም። እሱን የሚያውቀው በቃ ውጤቱን እያየ ነው።» 

Bethelehem Girma
ምስል privat

በመሆኑም በግብርና ስራዉ ላይ የሚታዩትን እነዚህን መሰል  ችግሮች ለመፍታት በዘርፉ ድሮኖችን  መጠቀም ጥሩ መፍትሄ መሆኑን ታስረዳለች።
«አሁን ለምሳሌ እኛ በኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ተቋም እየሰራን ያለነዉ ድሮን የፀረ-ተባይ  ኬሚካል የሚረጭ ድሮን ነው። ይህ ድሮን የሚረጨው እየበረረ ስለሆነ አንደኛ ጊዜ ይቆጥባል። በትንሽ ጊዜ ውስጥ ሰፋ ያለ ቦታ በመሸፈን ረጭቶ መጨረስ ይችላል።  ሁለተኛ ነገር ደግሞ  በተስተካከለ ሁኔታ ስለሚረጭ በአንድ ቦታ ብዙ በሌላ ቦታ ደግሞ ትንሽ ይሆንም። ከላይ ሆኖ በተመሳሳይ ፍጥነት ስለሚረጭ ማለት ነው። ስለዚህ አንደኛ ነገር ብክነትን ይቀንሳል። ሁለተኛ ነገር ደግሞ ጊዜ መቆጠብ ይችላል። » በማለት አብራርታለች ።
ከዚህ በተጨማሪም የድሮን ቴክኖሎጅ አርሶ አደሩ በፀረ ተባይና በማዳበሪያ ርጭት ወቅት ለኬሚካል እንዳይጋለጥና ጤንነቱን እንዲጠብቅ እንዲሁም በአይን የማይታዩ የሰብል ጉዳቶችን በካሜራ በመመለከት ለችግሩ ቀድሞ መፍትሄ በመስጠት  ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ትላለች። ያ በመሆኑ  ቴክኖሎጅውን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ላይ መሆናቸውን ትገልፃለች።
ወጣቷ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው  ካቴድራል ትምህርት ቤት ነው። የምህንድስና ትምህርቷን የጀመረችው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አምስት ኪሎ ግቢ  ሲሆን፤ በመሃል ነፃ የትምህርት ዕድል በማግኘቷ ወደ ቻይና በማቅናት ከቻይናው  ናንጂንግ  የአውሮፕላንና የህዋ ሳይንስ ምንድስና /የኤሮናውቲክስ እና አስትሮኖቲክስ/ዩንቨርሲቲ  በአውሮፕላን ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች። ከተመረቀች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ተቋም በጠፈር ምህንድስና ምርምር እና ልማት ዳይሬክቶሬት ስር በድሮን ዲዛይን እና ልማት ላይ ከምትሰራው ስራ ጎን ለጎን በተቋሙ«ኢትዮ ስፔስ ኪዲስ ክለብ»ተብሎ በሚጠራው  የልጆች የህዋ ሳይንስ  ክበብ  አስተባባሪ በመሆን  ስልጠናዎችን ትሰጣለች።

Bethelehem Girma
ምስል privat

«ዓላማችን  «ታለንትድ» የሆኑ እና «ኢንተርስት» ያላቸው ልጆችን በዚህ ዘርፍ  ቦታ ሰጥተን አሰልጥነን ወደፊት ለሚገጥማቸው «ኔክስት ስቴፕ» ዝግጁ  አድርገን ማቅረብ ነው። ጥሩ «ሂዉማን ፓወር» መፍጠር መቻል ነው። አሁን የመጀመሪያውን «ባች ትሬኒንግ» ጀምረናል። 6 ልጆች አሉ በዚህ ውስጥ። «ሰመር እስኩል» ከፍተን በዚያ ውስጥ አንዳንድ የመጀመሪያ «ሌብል» የሆኑ ኮርሶችን በተለያዩ መስኮች በ«አስትሮኖሚ» በ»ኤሮስፔስ» እና በሌሎችም ዘርፎች የክረምት ኮርስ እየሰጠናቸው ነው።  እነዚህ ልጆች 4 ዓመት ነው ከኛ ጋር የሚቀጥሉት። አዳዲስም እንቀበላለን»
ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ ለህዋ ሳይንስ ምርምር ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራት የምትናገረው ቤተልሄም፤ይሁን እንጅ በዘርፉ ለልጆች ድጋፍ የሚያደርግ አልነበረም። በመሆኑም ይህ ስልጠና በእሷ የልጅነት ጊዜ  ያላገኘችውን ዕድል በዘርፉ ፍላጎትና ተሰጥኦ ላላቸው ልጆች ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልፃለች።ድህነት በፈጠራ ስራዎቻችን  ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል የምትለው ቤተልሄም፤ባለሀብቶችና የዘርፉ ሙህራን በዚህ ዘርፍ ለሚሰሩና ተሰጥኦ ላላቸው  ልጆችና ወጣቶች  ተገቢውን ድጋፍ ቢያደርጉ ውጤታማ ዜጋ ማፍራት ይቻላል ባይ ነች።
በ20ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ቤተልሄም ፤በእነዚህ ስራዎቿ በአፍሪካ የጠፈር ኢንዱስትሪ ውስጥ  ከ 30 ዓመት በታች ያሉ  ምርጥ 10 የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዝርዝር ከተካተቱ ጥቂት  ሴቶች  ውስጥ በዚህ ዓመት አንዷ ሆና  የተመረጠች ኢትዮጵያዊ ወጣት ሆናለች ።
«ሽልማቱ ለእኔ በጣም አስደናቂ ነበር። አልጠበቁትም ነበረ። በድንገት ነበር የመጣ።በኋላ በመገናኛ ብዙሃን ብዙ ሽፋን ያገኛል ብዬም  አልጠበኩም።  እግዚአብሔርን በጣም አመሰግንሃለሁ። እኔ ገና እንደሆንኩ ነው የማስበው ።ገና ብዙ የሚጠብቀኝ ስራ አለ። ብዙ መስራት የሚፈልጋቸው ነገሮች አሉ። ለእነዚህ ስራዎች ብርታት እንዳገኝ  አድርጎኛል ።»ብላለች ስለሽልማቱ።
ያም ሆኖ የተጓዘችበት መንገድ  አልጋ በአልጋ አልነበረም።በምትማርበት ወቅት በሙያው  የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ በመሆኑ አርአያ የማጣት ችግር፣ተምራ ስትጨርስም በሙያዋ ስራ የመቀጠር ችግር እነዚህ ሁሉ ፈተናወቿ ነበሩ።ከዚህ በተጨማሪም የ2ተኛ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለች ያጋጠማት አደጋ የማትረሳው ነበር።

Bethelehem Girma
ምስል privat

«ከምንም በላይ ደግሞ 2ኛ ዓመት እያለሁ «ኢንተርን ሽፕ» ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መጥቼ ነበር። ክረምት ላይ። እሱን እንዳጠናቀኩ  ወደ ቻይና ከመመለሴ በፊት ትልቅ የመኪና አደጋ ደርሶብኝ ነበር።»  በዚህ አደጋ በተለያዩ የሰውነት ክፍሏ ጉዳቶች እንደደረሱባት እንዲሁም  ለአጭር ጊዜ የመርሳት አደጋ አጋጥሟት እንደነበር ካብራራች በኋላ፤ « ዶክተሩ መቆየት እንዳለብኝ ቢነግረኝም «ካምፓስ ሰስፔንድ»ልደረግ  ስለሆነ ወደ «ካምፓስ ተመልሸ ነበር።»  እና አስቸጋሪ ቢሆንም ያኔ የተረዳሁት ነገር ህይወት ውድ የሆነ ስጦታ መሆኑን  ነው። ሁለተኛ ደግሞ ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች መትረፍ እንደሚቻል። ብዙ አይነት ተግዳሮቶች ቢገጥመኝ የሚያመጣው እድገት እንዳለ አስባለሁ። እና «ቻሌንጅ» ይኖረዋል «ቻሌንጅ» ግን ያስፈልጋል ጠንካራ ለመሆን።» ብላለች።
በልጅነት ዕድሜዋ በወላጅ አባቷ ይነገራት የነበረው «ከጠነከርሽ ሁሉን ማድረግና  መሆን ትችያለሽ»ምክር ፤እንዲሁም የታላቅ ወንድሟ  ድጋፍ ችግሮችን  ተቋቁማ ያሰበችበት እንድትደርስ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ገልፃለች።
ወጣቷ ለወደፊቱ በትምህሪቷ የመግፋት እንዲሁም  የአሜሪካውን የጠፈር ምርምር ጣቢያ  /NSSA/ን በመጎብኘትና ልምድ በመቅሰም በሀገሯ የመተግበር ዕቅድ አላት።ከዚህ በተጨማሪ ለአፍሪቃ የቴክኖሎጅ ኢንደስትሪ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን የማቅረብ ፍላጎትም አላት።
«ባለሁበት «የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ» ዘርፍ መስራትን  መቀጠል  እፈልጋለሁ። «ኢንተርፕረነር» መሆን እፈልጋለሁ። በዚህ በቴክ «ስታርት አፕ» እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። አሁንም እየሰራሁባቸው ያሉ ነገሮች አሉ።  ወደፊት ደግሞ ይህንን አሳድጌ በዚህ«ስታርታአፕ»  ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች «አድቫንስድ የሆኑ ቴክኖሎጂ»ን በማቅረብ የተለያዩ መፍትሔዎችን በዚህ « ስታርት አፕ»ውስጥ መስራት እፈልጋለሁ።»

 

 ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ