1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተሰጥቷል የተባለው የጳጳሳት ሹመትና ዉዝግቡ

ሰኞ፣ ጥር 15 2015

በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሃይማኖቷ እንቆረቆራለን ያሉ የእምነት አባቶች ለ26 ጳጳሳት ሹመት ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ የተወሰኑ የቤተክርስታኗ አባቶች ሰጥተዋል የተባለው ይህ ሃይማኖታዊ ሹመት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ነው በሚል ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጿል፤ ውዝግብም አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/4Mb8M
Äthiopien Kidiste Silasie-Kathedralenkirche
ምስል Seyoum Getu/DW

“የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዘር ለመክፈል የተኬደው ርቀት አደገኛም አሳዛኝም ነው” ዳንኤል ክብረት

በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሃይማኖቷ እንቆረቆራለን ያሉ የእምነት አባቶች በትናንትናው እለት ለ26 ጳጳሳት ሹመት ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ የተወሰኑ የቤተክርስታኗ አባቶች ተሰብስበው ሰጥቷል የተባለው ይህ ሃይማኖታዊ ሹመት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ነው በሚል ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጿል፤  ውዝግብም አስከትሏል። የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ስለተከሰተው ሁኔታ ለመነጋገር ትናንት እሁድ ከቀትር በኋላ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ አስተላልፈዋል።

“ሹመቱ በአባቶች እንዲሰጥ የሆነበት ዋናው ምክኒያት የምዕመናን ቁጥር ከቤተክርስቲያን እየተመናመነ መምጣት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ብፁሃን አባቶች በተለያዩ ጊዜያት በሲኖዶስ ላይ በደብዳቤም ጭምር ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ጥያቄው ደግሞ የአባቶች ብቻ ሳይሆን የትውልዱም ጥያቄ ነው፡፡ የተጠየቀውም በአንድ አከባቢ (ክልል) ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተጠና ጥናትም ከቤተክርስቲያን ምዕመናን እየቀነሱ መሆኑን ቢያሳይም መፍትሄ ሊሰጥ ስላልተቻለ ነው አባቶች ወደ ውሳኔው የገቡት፡፡”

Äthiopien neuer Erzbischof Oromia
ምስል Seyoum Getu/DW

ሰባኪ ወንጌል መምህር ዳኔኤል ጫላ ትናንት ውዝግብ ያስነሳውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዳዲስ ጳጳሳት ሃይማኖታዊ ሹመትና የስራ ምደባ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል በሰጡን ቃለምልልስ ያብራሩት  ነው፡፡ መምህር ዳኒኤል ጥያቄው የአባቶች ብቻ ሳይሆን የህዝበ ክርስቲያኑ ጥያቄም ጭምር ነው በማለት ነው ገለጻቸውን የቀጠሉት፡፡ “ጥያቄው በሚገባኝ ቋንቋ በሚገባኝ አረዳድ ፈጣሪየን ላመስግን ላምልክ የሚል ነው፡፡ በቤተክርስቲያንቷ የአከባቢው ማህበረሰብ ለመረዳት በሚቸገረው በሌላ ቋንቋ የሚሰጥ አገልግሎትም ቅሬታ ሲፈጥር ነበር፡፡ ከተለያዩ ክልሎች የሚነሳው ይሄ ጥያቄ መልስ ስላላገኘ ነው አባቶች በዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ሁኔታው የገፋቸው፡፡”

ትናንት እሁድ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ ተከናወነ የተባለው የጳጳሳት ሹመት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዋነኛ መነጋገሪያም ሆኖ ነው የዋለው፡፡ “የጳጳሳቱን የሹመት ሥነ ሥርዓት” እና “አዲስ የተሾሙ ናቸው የተባሉትን ጳጳሳት” የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ትናንት እሁድ በስፋት ሲዘዋወሩም ውለዋል።

ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እና ደንብ ውጪ ተሾሙ የተባሉት ጳጳሳት በተገኙበት ዝርዝር መግለጫ ሲሰጥም፤ ሦስት አባቶች ከፊት በመሆን በተነበበው መግለጫ ላይ አሁን ባለው የቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ ውስጥ “በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር አልቻልንም፣ ሲኖዶሱ ከአንድ አካባቢ ብቻ የተዋቀረ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ምዕመናን በአፍ መፍቻቸው ቋንቋቸው ወንጌልን ለመማር እና ሥርዓትተ አምልኮ፤ ለመፈፀም እንዲሁም ለመገልገል እና ለማገልገል ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤት ድረስ ጥያቄ ቢቀርብም”  ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቅሰው፡ “ከአንድ ወገን ብቻ በመመደብ ከምዕመናን ጋር በቋንቋ እና ባሕል ሳይግባቡ በመቅረታቸው በርካታ ምዕመናን ባለፉት ዘመናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስትያንን ለቅቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

እንዲህ ያለው ሁኔታ በተለይ በኦሮሚያ እና በደቡብ አካባቢ ይሰፋል ያሉት አባቶቹ ከ85 በመቶ በላይ ከአንድ ወገን ተዋቅሯል ያሉት ሲኖዶስ “ሁሉንም የአገሪቱን ሕዝቦች ያቀፈ ቅዱስ ሲኖዶስ” አቋቁመው በይፋ ሥራ መጀመራቸውን በመግለጫቸው አብራርተዋል። በዚሁ መሰረት ተሰጥቷል ባሉት የ26 ጳጳሳቱ ሹመት አብዛኛዎቹ ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ሲሆኑ፤ የደቡብ ክልል አካባቢዎችም ተካተዋል።

Äthiopien neuer Erzbischof Oromia
ምስል Seyoum Getu/DW

ዶይቼ ቬለ ተሰጥቷል ስለተባለው የሃይማኖት አባቶቹ ሹመት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምላሽ እና ቤተክርስቲያኗ በቀጣይ ልትወስድ የምትችለውን እርምጃ በተመለከተ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጋ በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ በማድረግ እና መልእክት በመላክ አስተያየታቸውን በዚህ ዘገባ ለማካተት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልሰመረም፡፡

ብጹህ አቡነ አብርሃም ትናንት በቤተክርስቲያኗ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ግን “ሕገ ወጥ ሲመተ ጳጳሳት” ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ በሕገ ወጥነት የተከናወነ ነው በማለት ሹመቱን ነቅፈዋል፡፡

የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስም ሊቃነ ጳጳሳት በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪ በማቅረብ፤ መንግስት “ክስተቱ በአገር ላይ ጭምር የሚያስከትለውን ጉዳት ተመልክቶ” በጉዳዩ ላይ ሕጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሲሉ አሳስበዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር  ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዘር ለመክፈል የተኬደው ርቀት አደገኛም አሳዛኝም ነው” በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። “ሕገ ወጥ የጳጳሳት ሹመት ገጠር ውስጥ ተደብቆ በመፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ኃጢአት ተሠርቷል” በማለትም በውል ያልጠቀሷቸውን አካላት ወቅሰዋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው “ከአንዱ የቤተክህነታችን ክፍል ዛሬ የሰማነው ድርጊት አሳዛኝ ነው” በማለት አባቶች በትዕግሥት እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ችግሩን ይፈቱታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው አስፍረዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የኦሮሚያ ክልል ቤተክህነትን የመመስረት እንቅስቃሴ ሲካሄድ ቆይቶ ጉዳዩ በስፋት መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል በተደረጉ ውይይቶች እልባት ማግኘቱ መገለጹ ይታወሳል።  

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ