1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተራኪ፤ ኢትዮጵያዊ መፅሃፍትን የሚያስደምጠው መተግበሪያ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 8 2013

አቤል እንግዳ እና ናሆም ፀጋዬ በተባሉ ሁለት ወጣቶች የተሰራው ይህ መተግበሪያ በድምፅ የተቀረፁ መፅሐፍትን፣የተመረጡ የራዲዮ ፕሮግራሞችን እና የተለያዩ ትረካዎችን በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አድማጮች ተደራሽ የሚያደርግ ነው።በድምፅ የሚጫኑት መፃህፍትም በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የተተረኩ ናቸው።

https://p.dw.com/p/3wTjc
Äthiopien | Teraki Application

ተራኪ፤ ኢትዮጵያዊ መፅሃፍትን የሚያስደምጠው መተግበሪያ


ቴክኖሎጅ በተለይም መተግበሪያዎች የዕለት ተዕለት ኑሮን ለማቃለል የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም።ይህንን በመገንዘብ ይመስላል አሁን አሁን በኢትዮጵያ ችግር ፈች ፈጠራዎችን የሚያቀርቡ  ወጣቶች  እየተበራከቱ ነው።ከወደ አዲስ አበባም ሁለት ወጣቶች መፅሀፍትን በድምፅ  ያሉበት ድረስ የሚያደርስ መተግበሪያ ሰርተዋል። የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም ከዚህ መተግበሪያ ፈጣሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የንባብ ባህል እንዳያድግ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የመፃህፍትና የቤተ-መፅሃፍት እጥረቶች  ይጠቀሳሉ ። ወጣቶቹ  የሰሩት «ተራኪ» የተሰኘ መተግበሪያም ይህንን ችግር  በመጠኑም ቢሆን ለመፍታት ያግዛል ተብሏል። አቤል እንግዳ እና ናሆም ፀጋዬ በተባሉ ሁለት ወጣቶች የተሰራው  ይህ  መተግበሪያ በድምፅ የተቀረፁ መፅሐፍትን፣የተመረጡ  የራዲዮ ፕሮግራሞችን እና የተለያዩ ትረካዎችን በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አድማጮች ተደራሽ የሚያደርግ ነው። ወጣት አቤል  እንደሚለው  «ኦል ብራይትስ ቴክኖሎጅ» በተሰኘ ድርጅታቸው አማካኝነት ለሰሩት ለዚህ መተግበሪያ፤  ታሪኮችንና  ተረቶችን በቃል የማስተላለፍ የኢትዮጵያዊ ባህል አንዱ መነሻቸው ነው።

Äthiopien | Nahom Tsegaye and Abel Engida | Gründer Streamingplattform Teraki
ምስል Privat

ናሆም በበኩሉ አብዛኛው ወጣት  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ጊዜውን ሲያሳልፍ ማየታቸውም መተግበሪያውን ለመስራት ሌላው ምክንያት መሆኑን ይገልፃል። ምንም እንኳ መነሻቸው ወጣቶች ቢሆኑም መተግበሪያው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተፃፉ መፃህፍትን በሁሉም ዕድሜ ክልል ለሚገኙ አድማጮች የሚያቀርበ ነው።
 የ«ተራኪ» መስራቾች  እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት  አዝናኝና አስተማሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ የድምፅ ይዘቶችን ማግኘትና መጠቀም አስቸጋሪ ነው። የይዘቶቹ ባለቤቶችም ስራዎቻቸውን  በሁሉም ቦታ ገበያ ላይ የማዋል አቅማቸው ውሱን በመሆኑ ለተጠቃሚው  ማድረስ  ሲቸገሩ ይታያል።ስለሆነም መተግበሪያው  ደራሲያንና እና አድማጭን ድልድይ ሆኖ በማገናኘት  የተለያዩ የኅበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ይጠቅማል ይላል ወጣት ናሆም። 
ቋንቋውን የሚናገሩ ነገር ግን ማንበብና መፃፍ ለማይችሉ  እንዲሁም ማየት ለተሳናቸው ወገኖች  ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ አቤል እንደሚለው «ተራኪ »ለወጣቱም ጥሩ የመረጃ አማራጭ ይሆናል።

Äthiopien | Teraki Application

ወጣቶቹ  መተግበሪያው ላይ የሚጭኗቸውን መፃህፍት ተራኪ ፕሮዳክሽን በተሰኘው የራሳቸው ስቱዲዮ  ከደራሲያን ጋር በመሆን ወደ ድምፅ  እንደቀየሩ ያደርጋሉ።ይህም ከደራሲያኑና ከአድማጩ በተጨማሪ መፅሀፍቱን ለሚተርኩ ወጣቶችም ዕድል የሚሰጥ ነው ተብሏል።-
በሌላ በኩል መተግበሪያው ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን በእንግሊዝኛና በአማርኛ የሚሰራ ሲሆን፤ በድምፅ የሚጫኑት መፃህፍትም  በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ  ቋንቋዎች  የተተረኩ ናቸው።ናሆም እንደሚለው በቀጠይ   በተለያዩ  የኢትዮጵያ ቋንቋዎች  የተተረኩ መፃህፍትን ለአድማጩ ለማቅረብ ይሻሉ።

Äthiopien | Nahom Tsegaye
ምስል privat

«ተራኪ»ይፋ ከተደረገ ካለፈው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ  30  መጽሐፍት እና 100  «ፖድካስትን» እስካሁን ለተጠቃሚው  አቅርቧል። ድምፆቹን ከመተግበሪያው ለማውረድ የበይነመረብ ግንኑነት የሚያስፈልግ ቢሆንም፤  ድምፆቹን ካወረዱ በኋላ  ተጠቃሚዎች ያለበይነመረብ  ግንኙነት በነፃ  ማድመጥ እንደሚችሉ አስረድተዋል።ለወደ ፊቱ ግን የተለያዩ የክፍያ ዘዴዎችን በመጠቀም ክፍያ ለመጀመር ማቀዳቸውን ወጣት አቤል ይገልፃል። 

Äthiopien | Abel Engida
ምስል privat

አቤልና ናሆም መተግበሪያውን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት  ቢያንስ ለመቶ ሺህ ተጠቃሚዎች የማድረስ ዕቅድ አላቸው።ተራኪ ይፋ ከተደረገ  ከቅርብ ሳምንታት ወዲህም ከ1500 በላይ ሰዎች መተግበሪያውን እንደጫኑትና  ያገኙት ምላሽ መልካም መሆኑን ይገልፃሉ።ናሆም እንደሚለው ተራኪ ለጊዜው በአንሮይድ የቀረበ መተግበሪያ ሲሆን ለወደፊቱ ግን  ማሻሻያዎች ይደረጉበታል።
ሁለቱ ወጣቶች ከተለያየ ሙያ መስክ የመጡ ናቸው። ናሆም የመረጃ ቴክኖሎጅ፤ አቤል ደግሞ የህንፃ ዲዛይን ምህንድስና ሙያ ባለቤቶች ናቸው። ያም ሆኖ የጋራ ራዕይ በመሰነቅ «ኦልብራይትስ ቴክኖሎጅ» የተባለ ድርጅት መስርተው በአዲስ አበባ ከተማ በቴክኖሎጅው ዘርፍ በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ እንደሚሉት በዘርፉ ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ ባለመሆኑ የሚያጋጥመው ውጣውረድ ቀላል አይደለም።ያም ሆኖ  ቴክኖሎጅ የችግር መፍቻ መሆኑን በመገንዘብ   የፈጠራ ባለሙያዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እንዲሰሩ ወጣቶቹ መክረዋል። 

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን ። 

 

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ