1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተምሳሌት የወጣቶች በጎ አድራጎት ማኅበር

ዓርብ፣ ጥር 15 2012

የሚያውቋቸው እንደሚናገሩት ወጣቶቹ በከተማው የመሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነዋሪዎች ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተምሳሌት የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር በሚል ራሳቸውን አደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/3Wmpz
Äthiopien Addis Ababa | Schuhputzer
ምስል DW/S. Wegayehu

የወጣቶች ዓለም፦ችግረኞችን ለመርዳትየጫማ ጠረጋ ዘመቻ

ቦታው በይርጋዓለም ከተማ አቦስቶ በተባለ ቀበሌ የሚገኝ አውራ ጎዳና ነው ። በዚህ ስፍራ በርከት ያሉ ወጣቶች ከመንገድ ግራና ቀኝ እንደችቦ ሰብሰብ ብለው ይስተዋላሉ። ተመሳሳይ ቲሸርቶችን ( ካኒቴራዎቹን ) ለብሰው የተሰባሰቡትን እነኝህን ወጣቶች የተመለከት ምናልባትም << የምንትስ ቀን >> የተሰኘ በዓል ሊያከብሩ ይሆናል ብሎ ሊገምት ይችላል ። ይሁን እንጂ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደተረዳሁት ወጣቶቹ በስፍራው የተሰባሰቡት በተለምዶ ሊስትሮ በመባል የሚታወቀውን የጫማ ማጽዳት ስራ ለማከናወን ነበር።

የሚያውቋቸው እንደሚናገሩት ወጣቶቹ በከተማው የመሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነዋሪዎች ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተምሳሌት የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር በሚል ራሳቸውን አደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ ። በማህበራቸው ችግረና ተማሪዎችን ፣ ህጻናትን ፣ ሴቶችንና ሐረጋዊያንን የሚደግፉት ግን ለምነው አሊያም ደጅ ጠንተው ሳይሆን ጫማ በማጽዳት ባሰባሰቡት ገቢ መሆኑ የበርካቶችን ትኩረት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

Äthiopien Addis Ababa | Schuhputzer
ምስል DW/S. Wegayehu

በይርጋዓለም ከተማ አቦስቶ ቀበሌ በሚገኘው ጎዳና ላይ የደንበኞችን ጫማ እያጸዱ ከሚገኙት የማህበሩ አባላት መካከል ቤቴልሄም ደጉና ልደቱ ዮሀንስ ይገኙበታል ።ቤቴልሄምና ልደቱ ሲናገሩ << ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በተምሳሌት የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ በመሳተፍ ላይ እንገኛለን። በአሁኑወቅት በማህበሩ አማካኝነት ችግረኛ ተማሪዎችን ፣ ህጻናትን ፣ ሴቶችንና ሐረጋዊያንን እየደገፍን እንገኛለን ። ለድጋፍ የሚያስፈልገንን ገንዘብ የምናገኘው የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሰራዎችን በመስራት ነው ። ለምሳሌ በዛሬው ዕለት በማከናወን ላይ የምንገኘው የጫማ ማጽዳት ስራ ትዕግስት የተባለች የአስር ዓመት ታዳጊን የህምና ውጪ ለመሸፈን ነው። ምክንያቱም የታዳጊዋን በሽታ የመረመሩት የይርጋዓለም ሀኪሞች ታዳጊዋ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል መሄድ እንዳለባት ወስነዋል። የትዕግስት ቤተሰቦች ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም የሌላቸው በመሆኑ እኛ የሚያስፈልገውን የህክምና ወጪ ለመሸፈን ሃላፊነት ወስደን እየሰራን እንገኛለን >> ብለዋል።

የይርጋዓለም ተምሳሌት የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር አባላት ሰዎች አገልግሎት እያገኙ እግረ መንገዳቸውን የተቸገሩ ወገኖችን እንዲደግፉ የጀመሩት ጥረት አሁን አሁን ተቀባይነቱ እየሰፋ እንደሚገኝ አባላቱ ይናገራሉ። በአሁኑወቅትም በማህበሩ አባላት የሚሰጠውን የጫማ ጽዳት አገልገሎት የሚጠቀሙ በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት መቻሉንም አስረድተዋል። በማህበሩ አባላት ጫማቸውን በማጸዳት ላይ ከሚገኙት መካከል አቶ ዳንኤል ጌጌሶ << ወጣቶቹ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት የሚያደረጉት ስራ የሚያስመሰግናቸው ነው ። በዚህም እኔን ጨምሮ አብዛኛው ነዋሪ የማህበሩ ደንበኛ በመሆን የጫማ ጽዳት አገልገሎቱን እንዲሰጡን እያደረግን እንገኛለን >> ብለዋል።

Äthiopien Addis Ababa | Schuhputzer
ምስል DW/S. Wegayehu

ወጣት ብዙነህ ጌታቸው የተምሳሌት የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ነው። ማህበራቸው ከተቋቋመበት ከባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ለበርካታ ችግረኛ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉንና አሁንም ይህንን ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ወጣት ብዙነህ ይናገራል።

ወጣቱ በማያያዝም << ማህበራችን በቀጣይ ከበጎ አድራጎት ስራዎች በተጨማሪ ወጣቶችን ከአጉል ባህሪ ሊታደጉ የሚችሉ ስራዎችን ለማከናወን አቅዷል። በተለይም በያዝነው ዓመት ስፖርትን ጨምሮ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያስችሉ ክበባትንና ቡድኖችን በማቋቋም ላይ እንገኛለን >> ብሏል።

 ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ   

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ