ተሀድሶ ይደረግበት የሚባለው የዚምባብዌ የምርጫ ሕግ
ሰኞ፣ ሰኔ 4 2010ምርጫው የቀድሞው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ባለፈው ህዳር ወር፣ 2017 ዓም በጦር ኃይሉ ግፊት ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የሚካሄደው የመጀመሪያ ነው። የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ፣ በምህጻሩ፣ ኤምዲሲ የተባለው ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የገዢውን ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የአራት አሰርተ ዓመት ገደማ አመራር ለማብቃት ይቻል ዘንድ ከሌሎች ትናንሽ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ህብረት ፈጥሯል። ህብረቱ በቀጣዩ ሐምሌ ወር የሚደረገውን ምርጫ ካሸነፈ ኤኮኖሚውን በማሳደግ እና የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻሉ ተግባር ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ከሮበርት ሙጋቤ ስልጣን መልቀቅ ጥቂት ቀናት ቀደም ሲል ከተደረገው የአደባባይ ተቃውሞ ወዲህ የተካሄደው የመጀመሪያው ግዙፍ ነው በተባለው የተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉት ዚምባብዌ ዜጎች በአጠቃላዩ ምርጫ ላይ ለሁሉም እኩል የመወዳደሪያ እድል እንዲፈጠር እና እኩል የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲያገኙ ነው ለአስመራጩ ኮሚሽን እና ለሀገሪቱ መንግሥት ባቀረቡት ጽሁፍ በግልጽ አስቀምጠዋል።
ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ በምርጫው ሕግ ላይ የሚደረገው ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ዜጎች ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል አስመራጩ ኮሚሽን በቅድሚያ ገለልተኛ ወገን አዲሱ የመራጮች ስም ዝርዝር የያዘውን ሰነድ እንዲመረምር እንዲፈቅድ፣ የምርጫ ወረቀቶችን የሚያሳትመውን ኩባንያ ስም እንዲያሳውቅ ህትመት ላይ ግልጽ አሰራር እንዲኖር እና የምርጫውን ውጤት እንዲያስጠብቅ የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው። ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው አንዳንድ የተቃዋሚ ደጋፊዎች የተባሉት ተሀድሶ ለውጦች ከምርጫው በፊት ካልተደረጉ ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል በሚል መስጋታቸውን ገልጸዋል።
«ገዢው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ እንቅፋቶች እየደቀነብን እንደሆነ ይሰማናል። እና እያልን ያለነው የፈለገውን እንቅፋት ቢደቅንም እና የጠየቅነውን ለውጥ ባያደርግም፣ እኛ ፣ ያንን ሁሉ ችግር እናልፋለን ነው። »
«በዚምባብዌ ትክክለኛ እና ነፃ ምርጫ ማየት እንፈልጋለን። ለይስሙላ ብቻ የሚቆሙ የምርጫ ጣቢያዎችን አንፈልግም፣ ምክንያቱም፣ የማጭበርበር ተግባር ሊፈጸምባቸው ይችላል። ይህን ምርጫ እንደምናሸንፍ እናውቃለን። እና ያንን ለማደናቀፍ ካሁኑ እያጭበረበሩ ነው። »
የዚምባብዌ ምርጫዎች ወቀሳ ሲቀርብባቸው ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ዓም ምርጫ ከጥቂት ጊዜ በፊት የሞቱት የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ፣ ፣ በምህጻሩ፣ ኤምዲሲ የተባለው መሪ ሞርጋን ቻንጊራይ አሸንፈው እንደነበር፣ ግን፣ የቀድሞው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣኑን ለማስረከብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ ነው የሚነገረው።
በተቃውሞው ሰልፍ ላይ ንግግር ያሰሙት በፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አንፃር የሚፎካከሩት የተቃዋሚዎች ቡድኖች ህብረት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እጩ የ40 ዓመቱ ኔልሰን ቻሚሳ የዚምባብዌ ዜጎች ግልጽነት እንዲኖር እስከጠየቁ ድረስ የማጭበርበር ተግባር ሊፈጸም እንደማይችል አስታውቀዋል።
«ይህ ምርጫ አይጭበረበርም። ያ እንዳይሆን እኛ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን። ጥሩው ነገር ፣ የዚምባብዌ ሕዝብ ድጋፍ አለን። ምርጫ አያስፈራንም። ለውጥ እንዲደረግ የጠየቅነው ምናንጋግዋን ስለምንወዳቸው ነው። ራሳቸውን እንዲያታልሉ አንፈልግም። ራሳቸውን በማታለል ለድል እንዲበቁ አንፈልግም። ራሳቸውን በሚያታልሉበት ጊዜ ሁላችንንም ነው የሚያታልሉት። እና ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ በማካሄድ ዛኑ ፒኤፍን ለማዳን እንፈልጋለን። »የአስመራጩ ኮሚሽን የምርጫ ቀን ከተወሰነ በኋላ በምርጫ ሕግ ላይ ተሀድሶ ማድረግ እንeደማይቻል በማስታወቅ ዘግይቶ ቀርቧል ያለውን የተቃዋሚዎች ቡድን ህብረት ጥያቄን ውድቅ አድርጓል።
ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሀገሪቱን ወታደሮች የሲቭል ልብስ አስለብሰው በገጠሩ አካባቢ ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ዘመቻ እያካሄዱ ነው በሚል የተቃዋሚው ወገን ካለማስረጃ ወቀሳ በመሰንዘር፣ የጦር ኃይሉ በፖለቲካው እና በሲቭል ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ አሳስበዋል። ዛኑ ፒኤፍ ይህን ሀሰት ሲል አስተባብሏል፣ የጦር ኃይሉም ቀደም ባለ ጊዜ ማስተባበያውን አሰምቷል።
የአካባቢ እና የአፍሪቃ ህብረት መሪዎችም በምርጫው ሕግ ላይ የተሀድሶ ለውጥ እንዲደረግ ግፊት እንዲያሳርፉ ቻሚሳ ጥረት እንደሚያደርጉ እና በመዲናዋ የታየውን ዓይነት ተቃውሞ በመላ ዚምባብዌ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል። ፕሬዚደንት ምናንጋግዋ ከሁለት አሰርተ ዓመት በኋላ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ቡድኖች የዚምባብዌን ምርጫ በታዛቢነት እንዲከታተሉ ጋብዘዋል።
አርያም ተክሌ
ተስፋለም ወልደየስ