1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብዙዎች የሚፈልጉት የካንሰር ህክምና በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2013

ካንሰር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበለጸጉት ሃገራት በሽታና ስጋት ብቻ መሆኑ መቅረቱን ይነገራል። የተለያዩ የህክምና መረጃዎችም ሰዎች የአኗኗር ልማዳቸው ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበራከቱ ይነገራል። የታማሚዎች ቁጥር መጨመሩ እንዳለ ሆኖ የህክምና አቅምና አቅርቦቱ ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/3nTG4
Krebs Krebszelle Illustration Lungenkrebs
ምስል Imago/Science Photo Library

«የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ»

 

የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ከሃያ ዓመታት በላይ በዚሁ የህክምና ዘርፍ በመሥራት ላይ የሚገኙት ከፍተኛ  ባለሙያ ዶክተር ቦጋለ ሰሎሞን ይናገራሉ። በተለይም ሴቶች ለጡትና የማሕጸን በር ካንሰር በብዛት ሲጋለጡ ወንዶች ደግሞ ለትልቁ አንጀትና ለፕሮስቴት ካንሰር መጋለጣቸውንም ነው ዶክተር ቦጋለ የተናገሩት። በጤና ጥበቃ የካንሰር ፕሮግራም ኦፊሰር  የሆኑት ሲስተር ታከለች ሞገሥም የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር በሌላው ሀገር እንደሚታየው ኢትዮጵያ ውስጥም እየጨመረ ለመሆኑ አጽንኦት ይሰጣሉ። እሳቸው እንደሚሉትም ካንሰር ብቻ ሳይሆን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ታማሚዎችም ቁጥር እየጨመረ ነው።

 በየዓመቱ  በጥቅምት ወር የጡር ካንሰርን አስመልክቶ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ደረጃ ይደረጋሉ።  ባሳለፍነው የጥቅምት ወር እኛም ይህን አስመልክተን ባቀረብነው አንድ ዝግጅት ለጡት ካንሰር ህክምና ወደ ውጭ ሀገር መሄድ ግድ የሆነባቸው አንዲት ኢትዮጵያዊት የግል ተሞክሯቸውን አካፍለውን ነበር። ወይዘሮዋ ለካንሰር ላለመጋለጥ የሚደረጉ ቅድመ ምርመራዎችን ይከታተሉ ነበር ። የጤና ችግሩ እንዳለ ሲገነዘቡ በሀገር ውስጥ ለመታከም ረዥም ወራት መጠበቅ ግድ መሆኑን በመረዳታቸው በወዳጆቻቸው ትብብር ወደ ውጭ ሄደው መታከማቸውን ገልጸውልናል። ይህ ገጠመኝ የእሳቸው ብቻ አይደለም፤ እጅግ በርካቶች ያላቸውን ጥሪት አራግፈው አንዳንዶችም ተበድረውና ርዳታ አሰባስበው ለህክምና ወደውጭ ሃገራት እንደሚሄዱ ይነገራል። አብዛኞቹ ታማሚዎች ከሚያስፈልጋቸው አንዱ የጨረር ህክምና መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። እስካሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ህክምና የሚገኘው በጥቁር አንበሳ ሀኪም ቤት ነው። ለህክምናው ያለው ፍላጎት ከፍ በማለቱ የጤና ሚኒስቴር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለካንስርም ሆነ ተላላፊ ላልሆኑ ህመሞች የሚሰጠው ህክምና እንዲስፋፋ እየሠራ ነው ይላሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የካንሰር ፕሮግራም ኦፊሰር ሲስተር ታከለች።

Krebs Krebszelle Illustration
ምስል Imago/Science Photo Library

የካንሰር ህክምናን የህክምና ተቋማቸው እጅግም ላልተጠናከረ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ነዋሪ በህክምና የመድህን ዋስትና አማካኝነት እየተደገፈ ተገቢው የጤና ክትትል በሚደረግባቸው ለምሳሌ እንደ ጀርመን ባሉ ሃገራትም ወጪው ከፍተኛ ነው። የህክምናው ውድነት ከአቅም ዝቅተኛነት ጋር ሲዳመር ደግሞ ችግሩን እንደሚያከብደው ነው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች የሚናገሩት። አቅም የሌላቸውን ጥቂት የማይባሉ ወገኖች ለመርዳት ከሚንቀሳቀሱ አካላት አንዱ የሚያስተውሉትን አጋርተውናል፤ መፍትሄ ያሉትን እንዲያጋሩም ባለሙያዎቹ ጠይቀናል። ሳምንት እንመለስበታል። እናንተም የምታውቁትን አካፍሉን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ