1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብዙዎች የሚፈልጉት የካንሰር ህክምና በኢትዮጵያ *ክፍል 2

ማክሰኞ፣ ጥር 4 2013

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ዓመታት በፊት የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ብዙዎችን የጎዳ የካንሰር አይነት ሆኖ ተመዝግቦ ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የጡት ካንሰር በግንባር ቀደምነት ብዙዎች እያጠቃ ነው። እስካሁን ጥቁር አንበሳ ሀኪም ቤት ብቻ ለካንሰር የጨረር ህክምና ይሰጣል። ይኽም በርካቶች ረዥም ጊዜ ወረፋ እንዲጠብቁ ግድ እንደሚል ነው የሚነገረው።

https://p.dw.com/p/3npgw
Russland I International Oncology Centre I Moskau
ምስል picture-alliance/dpa/Tass/M. aparidze

«ለህክምናው ረዥም ወራት ወረፋ መጠበቅ ግድ ነው»

ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙም ሆኑ ሕይወታቸው የሚያልፈው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ይነገራል። ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች አንዱ ካንሰር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ለብዙዎች የጤና እክልም ሆነ ህልፈት ምክንያት እየሆነ ነው። ባለፈው ሳምንት የካንሰር ህክምናን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት ምን እየተደረገ ነው ለሚለው ከባለሙያዎች ምላሽ ለማጠያየቅ የሞከረ መሰናዶ ማቅረባችን ይታወሳል። ጥቁር አንበሳ ሀኪም ቤት ብቻ ለዚህ በሽታ የሚያስፈልገው የጨረር ህክምና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል። ይኽም በርካቶች ረዥም ጊዜ ወረፋ እንዲጠብቁ ግድ እንደሚል ነው የሚነገረው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሀገር ደረጃ የተመዘገበ ቁጥር ባይኖርም አዲስ አበባ ላይ ከጎርጎሪዮሳዊው 2011 እስከ 2014 ድረስ 5701 ሰዎች በካንሰር መያዛቸው ተመዝግቧል። በዚህ መረጃ መሠረት 67 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ 33 በመቶው ወንዶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበረሰብ መረጃ ያሳያል። የታማሚዎች ቁጥር በዋና ከተማዋ ደረጃ ብቻ ቢመዘገብም ከመላው የሀገሪቱ ክፍል ለካንሰር ህክምና ርዳታ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ በርካቶች መሆናቸውን በማቴዎስ ወንዱ የካንሰር ማኅበረሰብ የፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዘላለም መንግሥቱ አባተ ይናገራሉ። ጥቂት ለማይባሉትም ድርጅታቸው ህክምና እንዲያገኙ ተገቢው ድጋፍ ያመቻቻል። አቶ ዘላለም እንደገለፁልን ወደ እነሱ የሚመጡት የጡትና የማሕጸን በር ካንሰር ታካሚዎች አብዛኞቹ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልል ነው። በዚያም ላይ በጥቁር አንበሳ የራዲዮና የጨረር ህክምና ለማግኘት ደግሞ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሕጻናት የካንሰር ታማሚዎችም እንደሚመጡም ይናገራሉ።

ERDF funding Poland 4
ምስል Ministerstwo Inwestycji i Rozwoju

ኢትዮጵያ ውስጥ ለካንሰር የሚያስፈልገውን የህክምና አቅርቦት  በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል  ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ባለፈው ሳምንት በጤና ሚኒስቴር የካንሰር ፕሮግራም ኦፊሰር ታከለች ሞገሥ እንደገለጹልን ይታወሳል።  አሁን ባለው የህክምና ሂደትም ለጨረር ህክምናው ህመምተኞች እስከ አንድ ዓመት ድረስ ወረፋ እንደሚጠብቁ ለመድኃኒት ደግሞ እስከ አንድ ወር መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። መድኃኒቶቹን በተመለከተ መንግሥት ድጎማ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉትም ወደ 12 ሀኪም ቤቶች በአሁኑ ጊዜ ለጡት ካንሰር መድኃኒት ይሰጣሉ።

የካንሰር ህክምና ኢትዮጵያ ውስጥ ካለበት ደረጃ አኳያም ሆነ ችግሩ ሲከሰት ለመዳን ያለው ዕድል የተሻለ እንዲሆንም ቅድመ ምርመራው ላይ ማተኮሮ ወሳኝ መሆኑንም ሲስተር ታከለች አጽንኦት ሰጥተዋል። የካንሰር ህክምና በመላው ዓለም ውድ ከሆኑ የህክምና አይነቶች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ንብረት ሸጠው አንዳንዴም ከወዳጅ ዘመድ አሰባስበው ለመታከም ወደ ተለያዩ ሃገራት ይሄዳሉ። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ፤ ዶክተር ቦጋለ ሰሎሞን በበኩላቸው ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያውቅ የህክምና ባለሙያ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን ገልጸዋል። ማብራሪያ የሰጡንን ባለሙያዎች በማመስገን በኢትዮጵያ የካንሰር ህክምናን በሚመለከት በተከታታይ ያጠናቀርነውን በዚሁ አበቃን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ