ብዙ የሚቀረው የጡት ካንሰር ግንዛቤ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 16 2014ካንሰርም ሆነ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ነገር ግን እጅግ አደገኛ የጤና እክሎች የበለጸጉት እና ኑሯቸው የተደላደለ፤ በቂ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ ሃገራት ችግር ብቻ መሆኑ ከቀረ ሰነባበተ። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተውም የተሻለ የህክምና ክትትል እና አገልግሎት በሚደረግባቸው ሃገራት በጡት ካንሰር ምክንያት የሚከሰተው ሞት ከጎርጎሪዮሳዊው 1980 እስከ 2020 ድረስ ባለው ጊዜ 40 በመቶ መቀነስ ተችሏል። ይኽ የተሳካው ደግሞ አስቀድሞ በሚደረግ የምርመራ ክትትል እና ህክምና መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከካንሰር ሕመም ጋር በተገናኘ ብዙዎችን እየጎዳ የሚገኘው ግንባር ቀደሙ የጡት ካንሰር መሆኑን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ላለፉት 15 ዓመታት በየዓመቱ በጥቅምት ወር ስለጡት ካንሰር ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ጥረት መደረጉን የሚናገሩት የማትያስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበረሰብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ በቀለ የችግሩን ምንነት በተመለከተ ኅብረተሰቡ በወጉ ተረድቷል ማለት አስቸጋሪ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ፒንክ ሎተስ ኢትዮጵያ የተሰኘ ስለጡት ካንሰር ግንዛቤን ለማስጨበጥ የሚንቀሳቀስ መረዳጃን ከተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ያቋቋሙት ወይዘሮ ሜሮን ከበደም ትዝብት ተመሳሳይ ነው። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ