1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብርቱ የተቃውሞ ሰልፎች በአማራ ክልል ከተሞች

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2013

መንግስትን በብርቱ የሚቃወሙ ሰልፎች በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ዛሬ ተካኼዱ። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት እና የግፍ ጭፍጨፋ በመቃወም ወደ አደባባይ ተመዋል።

https://p.dw.com/p/3sHyI
Äthiopien Bahir Dar | Proteste gegen Ermordung und Vertreibung von ethnischen Amharas
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ላይ ያነጣጠረዉ ግድያና መፈናቀል ይቁም

 መንግስትን በብርቱ የሚቃወሙ ሰልፎች በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ዛሬ ተካኼዱ።  የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት እና የግፍ ጭፍጨፋ በመቃወም ወደ አደባባይ ተመዋል። በመፈክሮቻቸው ባሰተጋቧቸው መልእክቶችም የክልሉ እና የፌዴራሉ መንግሥትን ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ፣ ሞትና መፈናቀል እንዲቆምም አበክረው ጠይቀዋል። በባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ወልዲያ ኮምቦልቻ፣ ሐይቅ፣ ደብረማርቆስና በሌሎችም የአማራ ክልል ከተሞች ዛሬ የተከናወኑት የተቃዉ ሰልፎች ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እጅግ የተቆጡ የተቃውሞ ሰልፈኞች ታድመዋል። የባሕር ዳሩ ሰልፍ ላይ የነበረው ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ስለባሕር ዳሩ እና ሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል። 

በምስራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በሁሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በመተከል፣ በቅርቡ ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ ወረዳዎች በተለይም ደግሞ በአጣዬና አካባቢው ታጣቂዎች በአደረሷቸው ጥቃቶች የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል።
ይህን በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወምና መንግስት ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም በሚል ሰልፎች ተካሂደዋል።
በወልዲያ ሰልፍ ከተሳተፉት መካከል አንዱ የሰልፉ ዓላማ መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመውን ወከባ እንዲያስቆም መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። አስተያየት ሰጪው እንደነገሩን በሰልፉ አብዛኛው የከተማው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን የብልፅግና አመራሮች በሰልፉ አለመገኘታቸው ህብረተሰቡን አበሳጭቷል።
በደሴ ከተማ ትናንት ሰልፍ የተካሄደ ቢሆንም ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ የተቃዉሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን በሰልፉ ላይ ከተገኙት መካከል አንዱ በስልክ ነግረውናል።
በባሕር ዳርም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰልፈኛ መንግስትን ሲተች አርፍዷል፣ የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዳልሠራ ነው በመፈክሮቻቸው ሲከስሱ ያረፈዱት።
በደብረ ማርቆስ ከተማ ተመሳሳይ የተቃወሞ ሰልፍ መካሄዱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያሳያል።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ችግር በተፈጠረበት ሁሉ ለሕይወቱ ሳይሳሳ መስዋዕት እየከፈለ እያለ አንዳንዶቹ የማይገባውን ስም እየሰጡት ስለሆነ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
በቅርቡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ተመሳሳይ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን በወቅቱ በሰልፈኛውና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ የፖሊስ አባል ሕይወት አልፏል።
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ