1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሔራዊ መግባባትና ጠ/ሚኒስትሩ ከሶሪያውያን ስደተኞች ጋር

ዓርብ፣ ሚያዝያ 22 2013

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ኢትዮጵያ ከሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች ጋር በቤተ መንግሥት ማፍጠራቸው በርካታ አስተያየቶችን አስተናግዷል።ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ውዳሴና አክብሮታቸውን የቸሩ እንዳሉ ሁሉ ድርጊቱን አምረው የኮነኑና የተቹም አልጠፉም።

https://p.dw.com/p/3so3r
Äthiopien, Addis Abeba | Premierminister Abiy Ahmend mit syrischen Geflüchteten
ምስል Prime Minister office of Ethiopia

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከስደተኞች ጋር ማፍጠራቸው

በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በሁለቱ ላይ እናተኩራለን።ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደጋግመው የሚያነሱት ብሔራዊ መግባባትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቤተ መንግስታት ከሶሪያውያን ስደተኞች ጋር ማፍጠራቸው ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን እንዳስሳለን።

ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር መፍቻ፣ከአንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል በመፍትሄነት የሚቀርበው ብሔራዊ መግባባት» በዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ካነጋገሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በምህጻሩ ኦፌኮ መንግሥት ከምርጫ በፊት  ብሔራዊ መግባባትን እንዲያስቀድም ትናንት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።በመግለጫው«ለመምረጥ የተመዘገበው ቁጥር ከሚጠበቀው በታች መሆኑን፣ ጊዜው ብዙዎች የተፈናቀሉበት ከጎረቤት አገሮች ጋር የነበሩ ግንኙነቶች እየሻከሩ የመጡበት፣ ዜጎችም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙበት እንደሆነ ጠቅሶ  ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት መንግሥትና ገዥው ፓርቲ  የእርቅና ብሔራዊ መግባባት መድረክ እንዲያመቻቹ በገዥው ፓርቲ ጫና ከምርጫ ውድድሩ መውጣቱን የገለጸው ኦፌኮ ጠይቋል።

ገብረ ገረ ቢራ በፌስቡክ «ትክክል፣ነው፧ብሔራዊ፣እርቅ፣ያስፈልጋል፣ሕዝቡም፣ችግር፣አለበት፣ብለዋል

ዳዊት ሙሉጌታ የኦፌኮን ጥሪ «የሀገራችንን ወቅታዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና የተጋረጡብንን አካባቢያዊ አደጋዎች በሚገባ ያገናዘበ የበሰለ ምክር ነው! ካሉ በኋላ  መንግስት ግን የሚሰማ አይመስለኝም።»ሲሉ በፌስቡክ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል ።ጌታሁን ኪዳኔ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል።«ለምንድን ነው መንግሥት ብሔራዊ መግባባት ወይም ተቀራርቦ መነጋገርና በጋራ መፍትሄ ላይ መድረስን የፈራው?ሲሉ። ማልኮልም ገብረ ማርያም ደግሞ  ለኦፌኮ፤  ጥያቄ አላቸው«ባለፈው ምርጫ አልተደረገም ብላችሁ ቅቡልነት የሌለው መንግሥት አላችሁ፤ ምርጫ ሲመጣ ደግሞ ብሄራዊ መግባባት ትላላችሁ እንዴ? ባጭሩ ስልጣን ይሰጠን በሉ።ሲሉ ጥያቄና ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

Äthiopien Büro des Oromo-Föderalistenkongresses
ምስል DW/S. Muchie

«በኦፌኮ አተያይ ብሄራዊ መግባባት ምንም ማለት ይሆን? እኔ ስልጣን ካልያዝኩ አገር አትኑር፡ የሚል ወይም ከውጪ ኅይል ገንዘብ ተቀብሎ ወገኑን የሚገድል አካል የሚያደርገው፣ በብሄራዊ መግባባት አለመኖር ነውን? እውን ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝቡ መካከል ይህን ያህል "አለመግባባት" አለ? አለመግባባት ካለስ ህዝባዊ መሰረት በሌላቸው ፓርቲዎች ድርድር ይፈታል?ሲሉ ኦፌኮን የጠየቁት በረከት በዛብህ ናቸው።እንግዳ ኦርካይዶ ደግሞ ከዚህ የተለየ ሃሳብ ነው ያቀረቡት« ሃገሪቱን ለማስቀጠል ሁሉን አሳታፊ ውይይት የግድ መደረግ አለበት።»የሚል።ወንድማገኝ ታፈሰም  «ከምርጫ በኋላ ብሔራዊ መግባባት ቶሎ መደረግ አለበት፤ብለዋል። »አስፋው TA በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት መፍትሄ የሚለውን የሚከተለውን ሃሳብ አቅርቧል።«የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት በብሔር እና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ስርዓትን በመተው ሰውን በሰውነቱ የሚያከብር ስረአት ማስፈን ነው።የሚል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ኢትዮጵያ ከሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች ጋር በቤተ መንግሥት ማፍጠራቸው በርካታ አስተያየቶችን አስተናግዷል።ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ውዳሴና አክብሮታቸውን የቸሩ እንዳሉ ሁሉ ድርጊቱን አምረው የኮነኑና የተቹም አልጠፉም። ከአድናቂዎችም ከተችዎችም ጽንፍ የያዙ፣ ዘለፋዎች የሚያመዝንባቸው በርካታ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል።እነርሱን ወደ ጎን ትተን በታረመ ቋንቋ የቀረቡትን የተለያዩ ሃሳቦች እንቃኛለን። ጌድዮን ተስፋዬ በፌስቡክ «ውድ ክቡር ጠ/ሚ እንድ ትልቅ ታሪክ ሰርተዋል። አላህ ያክብርዎ»ሲሉ መሐመድ ዋርሳሜ ሩሽም ለሶሪያ ስደተኞች ላደረጉት በጎ ተግባር አመሰግንዎታለሁ ብለዋል። «የአባትህን ሰራ ትሰራለህ መልካምነትህ የተለመደ ነዉ ዘመንህ ይባረክ ሰደተኛዉን የምታስብ ከፍ ብለሀል ከፍ በል »ይላል የኩላኒ መልካሙ መልዕክት ። «ይህ ለብዙ አሥርት ዓመታት የተረሳ በቀደመው መንግሥት ዘመን ተቀብሮ የነበረ ታላቅ እሴታችን ነው። ስላደሱት እመሰግናለሁ ጠቅላይ ሚኒስትራችን።ያሉት ደግሞ ሞሀመድ ሶማ ናቸው።

« የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጊላ ሜርክልን ለስደተኞች ካላቸው ቅን ልብ የተነሳ 'የስደተኞች እናት' ይሏቸዋል።ይህ ስያሜ ለጀርመንም ኩራት ነው።የአገሬም ጠቅላይ ሚንስትር ለስደተኞች ቅን ልብ ማሳየታቸው ለኢትዮጵያ ኩራት ነዉ።»ሲል የሚጀምረው ጃሽ አቡል አሀብሽ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት « መራሂተ መንግሥቷን የሚቃወሙ ጀርመናዊያን 'ስስታሞች' እንዳሉ ሁሉ ኢትዮጵያዉያን 'ስስታሞችም' አለን።ጠቅላይ ሚንስትሩ በአደገኛ የሽቦ አጥር ዉስጥ ሆነው ብቻቸውን አለመብላታቸው እንደ አገር ንፉግ አለመሆናችንን ያሣያል።»ይላል  የኦስማን አስማን አስተያየት ደግሞ ከዚህ ይለያል «አዎ እናውቃለን ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይናት። ግን አጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ እግዝአብሔርን እወድሀለሁ ብትለው አይሰማህም»ብለዋል። ማኅሌት ሊብሳ «የራሳ አሮባት የሰው ታማስላለች፤ ማድረጉ ባልከፋ ያገሩ ዜጐች በራብ እያለቁ እየተሰደዱ ባላየ ባልሰማ መሆኑ ያሳዝናል።»ሲሉ ተችተዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው« ኢትዮጵያ ከተጠጉ የሶሪያ ስደተኞች ጋር የረመዳን ኢፍጣር ማዕድን መጋራታቸው « አያቶቻችን የነብዩ ሙሐመድ  የቅርብ ዘመዶችና ሶሃቦችን ተቀብለው ያስተናገዱበትን አንፀባራቂ ታሪክ የሚያስታውሰን» ሲሉ ጠቅሰው «በዚህ ድንቅና ውብ ታሪካችን እንደምኮራው ሁሉ፤ ሕዝባችን በተለይም በወጣቱ ትውልድ ውስጥ ለተቸገሩ፣ ለተሰደዱና ጎዳና ላይ ለወደቁ የሰብአዊነትና የእምነት ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ትኩረት እንዲሰጡ እንሻለን።»ካሉ በኋላ  ይህ ሁኔታ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዛሬም ወደፊትም ከሙስሊም ሀገራትና ሕዝቦች ጋር በወዳጅነት፣ በፍቅርና በሰላም ለመኖር ያለንን ጠንካራ ፍላጎትና እምነት የሚያጸና ነው። ብለዋል ።አይሻ መሐመድ የተባሉ አስተያየት ሰጭ  « አንዳንዴ ሐበሻነቴ ኩራቴ ነው ምክንያቱም እኛ ያልተሰደድንበት ሀገር የለም እና እንኳን ቤተ መንግስት ሊያስገቡን ያውም ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖረን ከሸቃላና ከሹፌርነት ያለፈ ስራ አይሰጡንም በዛ ላይ ንቀታቸው አልሃምዱሊላህ።» በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል ። «የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ቢሆን የተቸገረን ሰው ከማብላት ወደሗላ አላለም »የሚለውን ሃሳብ ያስቀደሙት «ዝምታ ነው መልሴ» በሚል ስም በፌስቡክ ሃሳባቸውን ያሰፈሩ ሌላ አስተያየት ሰጭ «የሚያፈጥሩትን ሄደህ ዝያራ እንዳረክ ለሞቱትም ነብስ ይማር ማለትም ትልቅ ክብር አለው። የመንግሥት ምላሽ አጣን እያለ በጾሙ ሰዓት ከቤቱ ወቶ ጎዳና ላይ የወደቀ ሕዝብ ማን ወደቤቱ ይመልሰው ቤቱ ንብረት የወደመባቸው ወደማን አቤት ይበሉ ነገም ጎዳና ላይ ተቀምጠው ችግር እንደማይደርስባቸው ምን አይነት ዋስትና አላቸው እባክህ በማልቀስ ላይ እና ሐዘን ላይ ለተቀመጡ ሰዎች መልስ ስጣቸው።» በማለት አሳስበዋል።ጌታቸው ሰሎሞን ጌት «ለሶሪያውያኑ የተደረገውን በበጎ ነው ያዩት ።«በጣም ደስ የሚል እና የሚደገፍ ሀሳብ ነው! በእውነት ይህን ጥሩ እና መልካም ስራ ሰይጣን ካልሆነ በስተቀር ሰው ይቃወመዋል ብዬ አላስብም!።እንግዶችንንና ስደተኞችን መቀበል ኢትዮጵያዊ ባህላችን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርም ቃል የሚያዘው ነው። በማለት ሚራክል ዩኒክ ክዊን ግን «የራስን ልጅ አስርቦ የሌላን መመገብ ደግነት ነው እንዴ የሃገርህ ሙስሊሞች ክርስቲያኖች መጠለያ አተው ህፃናት ተርበው በገዛ አገራቸው ወድቀዋል እኮ ነው እነሱ እንደ ሰው አልተኮጠሩም መልካምነት ከቤት ሲጀምር ነው ደስ የሚለው»ብለዋል።«ማሻአላህ እስኪ እስርኞችንም አስፈታችው ደግ ከስራህ አይቀር።»የ ዘ ነኝ ሀበሻዊት» ጥያቄ ነው።ኃይለ ገብርኤል እንደሻው ግዛው «ውድ ጠ/ሚ፣ ከወለጋ ከተፈናቀሉ  ሙስሊሞች ጋር አፍጥረው ቢሆን ኖሮ እንዴት ባደነቅሁዎት!» ሲሉ ሀሊሽ አለሙ  «በሠላም ዕጦት ከሀገራቸው የተሠደዱትን መጎብኘት መልካም ነው ፡፡ ነገር ግን በገዛ ሀገራቸው በራሳቸው ወገን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እዲጎበኙቸው እመክራለሁ ። ብለዋል።»ብሥራት ግርማ ደግሞ አንድ የሀገር መሪ የተቀበላቸውን ስደተኞች ይህን ያህል ሲያከብር ሰምቼ አላውቅም።»

Äthiopien, Addis Abeba | Premierminister Abiy Ahmend mit syrischen Geflüchteten
ምስል Prime Minister office of Ethiopia