1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤንሻንጉል ጉሙዝ በፀጥታ ችግር የተነሳ ምርት አሽቆለቆለ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2014

የንጹሃን ሞት፤ የጸጥታ ችግር እና ግጭት የደጋገመው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የድባጤ ወረዳ ከተማ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ትናንት በነዋሪው ላይ ጉዳት በማድረስ ሁለት ሰዎችን መግደላቸው ተገለጠ። በክልሉ ለረዥም ጊዜ የቆየው የፀጥታ ችግር ሕይወት ከመቅጠፉ በተጨማሪ በምርት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩም ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/41vf7
Assosa Town Äthiopien
ምስል DW/N. Dessalegn

የፀጥታው ችግር አልተፈታም

የንጹሃን ሞት፤ የጸጥታ ችግር እና ግጭት የደጋገመው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የድባጤ ወረዳ ከተማ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ትናንት በነዋሪው ላይ ጉዳት በማድረስ ሁለት ሰዎችን መግደላቸው ተገለጠ። በተለይም በካማሺና መተከል ዞን ለረዥም ጊዜ ከቆየው የፀጥታ ችግር ባሻገር ድባጤ ወረዳ ካለፈው መስከረም ወር አንስቶ ተደጋጋሚ ጥቃት አስተናግዳለች። በክልሉ ለረዥም ጊዜ የቆየው የፀጥታ ችግር ሕይወት ከመቅጠፉ በተጨማሪ በምርት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩም ተገልጧል። በጸጥታ ችግር የተነሳ በክልሉ ለዘንድሮ የምርት ዘመን  ከታቀደው ግማሽ ያህሉ ብቻ በምርት መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ዐስታውቋል። ክልሉ ውስጥ ዘንድሮ አንድ ሚሊዩን ያህል ሄክታር መሬትን በምርት ለመሸፍ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ አምስት መቶ ሺ ያህሉ ብቻ በምርት መሸፈኑም ተጠቅሷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም በካማሺ እና መተከል ዞን ለዥም ጊዜያት በቆየው ጸጥታ ችግር ምክንያት በ2013 ምርት ዘመን  በምርት የተሸፈነው መሬት መጠን ዝቅተኛ መሆኑን የክልሉ የግብርና ቢሮ አመልክተዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኃላፊ እንዳስታወቁት በክልል ደረጃ በምርት ዘመኑ የተመረተው ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ለግብርና ምርት አነስተኛ መሆን ደግሞ በአካቢው ለረዥም ጊዜ የቆየ የጸጥታ ችግር መሆኑንም አክለዋል፡፡ በካማሺ ዞን አምስት ወረዳዎች እንዲሁም በመተከል ዞን ደግሞ በአብዛኛው ወረዳዎችም በሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አብዛኛው አርሶ አደር በሥራ ላይ እንዳልነበርም ጠቁመዋል፡፡ በአሶሳ ዞን  ወረዳዎች ደግሞ የተሻለ የግብርና ሥራ መካናወኑን አብራርተዋል፡፡

Äthiopien Vertreibung und Massaker in der Region West-Benishangul Gumuz
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

በክልሉ መተከል ዞን ባለፈው ዓመት ከመሰከረም 2013 አንስቶ በኮማድ ፖስት ወይም አስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር የሚመራ ሲሆን  የዞኑን ጸጥታ ለማሻሻል ሚሊሻዎችን ሲያሰለጥን መቆየቱን እና የአራት ክልሎች ልዩ ፖሊሶች በዞኑ መሰማራታቸውን ከዚህ ቀደም ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል፡፡ በዞኑ ወረዳ ካለፈው መስከረም ወር  መጨረሻ አንስቶ በወረዳው ከተማ እና ጋለሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ የተለያዩ ጥቃቶች መድረሳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ከተማ ትናንት የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪው ላይ ጉዳት ማድረሳቸው የተነገረ ሲሆን ጋለሳ  በተባለው የወረዳው አንድ ቀበሌ ውስጥ ደግሞ በስፋራው የተሰማሩ የጸጥታ ኃይሎች ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በካማሺ ዞን  ያሶ በተባለ ወረዳ ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ቸግር ምክንት በርካቶች ወደ ጫካ ሸሽተው እንዳሉና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ለዶይቸ ቤለ (DW) ገልጸዋል፡፡

የመተከል ዞን የጸጥታ ጉዳን በበላይነት የሚመሩት ለተናል ጀነራል ዓሥራት ዲኔሮ ባለፈው ቅዳሜ በሰጡን ማብራሪያ በዞኑ ድባጤ ወረዳ ጋለሳ ቀበሌ ውስጥ በስፋረው የሚገኙው የጸጥታ ኃይል በነዋሪው ላይ ጥቃት ፈጽዋል ተብለው ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በስፍራው በነዋሪው ላይ ጥቃት ያደረሱት በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ ያሉት ሸማቂ ኃይሎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት መስከረም 26 ቀን፣ 2013 ዓ.ም አንስቶ በነበረው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ከአሶሳ ወደ መተከል ዞን የሚወስደው መደበኛ የመጓጓዣ አገልግሎት ተቋርጦ ይገኛል፡፡ በክልሉ ባጠቃለይ ከ360ሺ በላይ ዜጎችም  በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ  ውስጥ እንደሚገኙም ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ