1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤተ-እስራኤላዉያን ከጥንት እስከ ዛሬ

ሐሙስ፣ ግንቦት 26 2013

ወደ 160 ሺህ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤላዉያን እስራኤል ዉስጥ ይኖራሉ። ማኅበረሰቡ ስለኢትዮጵያ ያስባል ስለኢትዮጵያ ይከታተላል፤ ስለኢትዮጵያ ያገባኛል ይላል። ሃገሪቱ ጠንካራ መንግሥት ሲኖራት ኢትዮጵያ ዉስጥ ቤተ-እስራኤላዉያን ይኖሩበት የነበሩትን ቦታዎች የቱሪስት መስዕብ እንዲሆን እንፈልጋለን። ቅድምያ ግን ለኢትዮጵያ ሰላም ይምጣ።

https://p.dw.com/p/3uOxJ
Äthiopien Dr. Amsalu Mehri
ምስል privat

ቤተ-እስራኤላዉያን ከጥንት እስከ ዛሬ

«ለአያሌ ዘመናት በኢትዮጵያ የኖሩት ቤተ-እስራኤላዉያን ከጥንት ጀምሮ በእደ-ጥበብ ሞያ ይተዳደሩ ስለነበር ዛሬ ከርሰ-ምድር ዉስጥ በቁፋሮ የሚወጡት ብርቅ እና ድንቅዬ የሆኑት የነገስታት ፅዋ እና ዋንጫዎች፤ የእነዚህ  ማኅበረሰብ ፈጠራ ዉጤቶች እንደሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ቤተ-እስራኤሎች በስራ ክህሎት የመጠቁ ናቸዉ።ለሃይማኖታቸዉ የተዋደቁ፤ ለባዕድ አምልኮ ያልተበገሩ፤ መንፈሰ ጠንካራና ልበ ቀና ናቸዉ። ቤተ-እስራኤላዉያን ገና ያልተፃፈና ያልተነገረ ታሪክ እንዳላቸዉ ለመገንዘብም ይቻላል፤ እላለሁ»  

ደራሲንና አርታዒ አምሳሉ መሐሪ በቅርቡ «ቤተ-እስራኤላዉያን ከጥንት እስከ ዛሬ» በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሐፍ ያነበቡልን ነበር። መጽሐፉ ማክሰኞ ግንቦት 24፤ 2013 ዓ.ም በእስራኤል የኢፌዲሪ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ በተገኙበት ተመርቋል።  ደራሲ አምሳሉ መሐሪ በእስራኤል በጎርጎረሳዉያኑ 1996 ዓ.ም የመጀመርያዉ ጥቁር ደራሲ ሆነዉ ተሸላሚም ናቸዉ። ዉድድሩ የነበረዉ ወደ ቅድስቲቱ ሃገር እስራኤል ከተለያየ ሃገራት በመጡ ደራስያን መካከል ነበር። በእስራኤል ራምሌ ጥንታዊ ከተማ በሚገኝ ታዋዊ ቤተ-መጽሐፍት ዉስጥ በእንቁ ኢትዮጵያዉን የተፃፉ  መጻሕፎች በማስመዝገብ ሌሎች እንዲያነቡም አስቀምጠዋል።  ደራሲንና አርታዒ አምሳሉ መሐሪ በቅርቡ ለአንባብያን ያቀረቡት ቤተ-እስራኤላዉያን ከጥንት እስከዛሬ የተሰኘዉ መጽሐፋቸዉ በራምሌ ቤተ መጽሐፍት እንደሚቀመጥም ነግረዉናልም። ደራሲ አምሳሉ በእስራኤል ነዋሪ ከሆኑ ሠላሳ ዓመት ሆንዋቸዋል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በጎንደር አዘዞ፤ በመቀጠል በሃረር እና ደብረዝይት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን እንዳጠቃለሉ ይናገራሉ። የከፍተኛ ትምህርታቸዉንም የሃገር ዉስጥ የትምርት እድል በማግኘት በሥነ-ጽሑፍ እና ቋንቋ ሞያ በአስመራ ዩንቨርስቲ ነዉ ያጠቃለሉት።  በቅርቡ ቤተ-እስራኤላዉያን ከጥንት እስከዛሬ የሚለዉን መጽሐፍ አሳትመዉ ለአንባብያን ያቀረቡት ደራሲ አምሳሉ መጻህፋቸዉ ስለ ቤተ እስራኤላዉያን ባህል ወግ ፤ እና ሃይማኖት ላይ ያተኮረ በተለይ የጥንቱን እንዳይረሳ ለትዉልድ ለማስተላለፍ ነዉ ብለዋል። አቅርበዋል። መፅሐፍ በአንባብያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፉን ደራሲ አምሳሉ መሐሪ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ዉስጥ በቀድሞ በጌምድር የሚል መጠረያ የነበረዉ ጎንደር ዙርያ ጭልጋ አካባቢ ሥርዓተ ሃይማኖቱን የሚከናዉኑበት ሙክራብ እንደነበረም ተናግረዋል። ወደ  እስራኤል እናንተ ቤተ-እስራኤላዉያንን ጨምሮ ብዙዎች እንደሚሉት ወደ ቅድስቲቱ ሃገር ከመጓዛቸዉ በፊት የእብራይስጥ ቋንቋን መሰረታዊ ነገሩን መማራቸዉን ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜም ሁለተኛ ዲግሪያቸዉን በእስራኤል ዩንቨርስቲ እየተከታተሉ ነዉ። ወደ 160 ሺህ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤላዉያን እስራኤል ዉስጥ ይኖራሉ ሲሉ ደራሲ አምሳሉ ነግረዉናል። ማኅበረሰቡ ስለኢትዮጵያ ያስባል ስለኢትዮጵያ ይከታተላል፤ ስለኢትዮጵያ ያገባኛል ብሎም ይጽፋል ይናገራል፤ ይረዳልም ብለዋል። ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት ሲኖራት ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ዉስጥ ቤተ-እስራኤላዉያን ይኖሩበት የነበሩትን ቦታዎች እንዲሁም የፀሎት ማከናወኛዎች በታሪካዊነት ህዝብ እየመጣ እንዲያየዉ የቱሪስት መስዕብ እንዲሆን እንፈልጋለን። ቅድምያ ግን ለኢትዮጵያ ሰላም ይምጣ ብለዋል።

Äthiopien Dr. Amsalu Mehri
ምስል privat

ሙሉ ጥንቅሩን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።     

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ