1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለ ዲግሪዉ መፅሐፍ አዟሪ

ዓርብ፣ የካቲት 13 2012

ወጣት አንዱዓለም ይስሃቅ ትዉልድና ዕድገቱ አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን በሰላሳዎቹ አጋማሽ  ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነዉ።በ2001 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በትያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪዉን ያገኜ ሲሆን ገጣሚና ጋዜጠኛም ነዉ።

https://p.dw.com/p/3Y7Mk
Äthiopien Buchverkäufer aus Addis Abeba
ምስል Privat

ባለ ዲግሪዉ መፅሀፍ አዟሪ


የወጣትነት ዕድሜ በርትተዉ ከሰሩበት ወርቃማ የህይወት ክፍል ሲሆን  በዚያዉ ልክ ደግሞ በስሜታዊነትና በአቻ ግፊት ለሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችም የተጋለጠ ነዉ።በዛሬዉ የወጣቶች ዓለም ዝግጅትም ከሱስ ተላቆ የንባብ ባህልን ለማዳበር መፅሀፍትን እያዞረ በመሸጥ ላይ ከሚገኝና በዚህ ስራዉ ተሸላሚ ከሆነ አንድ ወጣት ጋር ቆይታ አድጓል። 
ወጣት አንዱአለም ይስሃቅ ይባላል።ትዉልድና ዕድገቱ አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን በሰላሳዎቹ አጋማሽ  ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነዉ።በ2001 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በትያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪዉን ያገኜ ሲሆን ገጣሚና ጋዜጠኛም ነዉ።«የተፈሩ ህልሞች» በሚል ርዕስ አንድ የግጥም መድብል ለህትመት ያበቃ ሲሆን «ናፍቆት የተከለዉ ሀዉልት» በሚል ርዕስም  የግጥም ሲዲ አለዉ።ያም ሆኖ ግን ይህንን ስኬቱን በመመልከታቸዉና ተምሮ ለወግ ለማዕረግ በመብቃቱ የተደሰቱ ቤተሰቦቹንና ጓደኞቹን የሚያሳዝን አንድ ነገር በህይወቱ ተከሰተ።በስራዉ ብዙም ሳይገፋበት «ለመደበሪያ» በሚሉት ፈሊጥ እንደ ቀልድ በጀመራቸዉ መጠጥ፣ሲጋራና ሌሎች ሱስ አስያዥ ነገሮች ዉስጥ ወደቀ። እየዋለ ሲያድር ሱስ እየበረታበት በመሄዱ ከሚወደዉ የጥበብ ሙያና ከቤተሰቦቹ ተነጥሎ ጎዳና ላይ መዋል ማደር ጀመረ።
በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ ጊዜያትን ያሳለፈዉ አንዱዓለም ሁለት ጊዜ በቤተሰቡ ድጋፍ ወደ ማገገሚያ የገባ ቢሆንም ከተጠናወተዉ ሱስ ግን መላቀቅ አልቻለም ነበር።ያ በመሆኑ  ቤተሰቡም ሆነ ጓደኞቹ እንዲሁም የሚያዉቁት ሁሉ ተስፋ ቆርጠዉ እርግፍ አድርገዉ ተዉት።እናም በአስቸጋሪ ሁኔታ ህይወቱን ጎዳና ላይ መግፋት ቀጠለ። ከዕለታት አንድ ቀን ግን ከወደቀበት የጎዳና ህይወት ተነስቶ ተስፋ ባለመቁረጥ በድጋሚ  እርዳታ ወደሚያገኝበት የህክምና ተቋም አመራ።
በ2007 ዓ/ም ከገባበት የሱስ ህይወት በባለሙያ እርዳታ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ሲመለስ ግን ስራ ፣ገንዘብ፣ዘመድ ፣ጓደኛ ሁሉም አጠገቡ የሉም።አንዳንድ ድሮ የሚያዉቃቸዉ ሰዎችም  ቢሆን  ስለማገገሙ እርግጠኞች አልነበሩም።ግራ ሲገባዉ በቀጥታ ያመራዉ ድሮ ያዉቃቸዉ ወደነበሩ መፅሀፍ አዟሪ ጓደኞቹ ነበር።መፅሀፍትን ከእነዚሁ ጓደኞቹ  በመዋስ  ንባብን  መሸሸጊያዉ  አደረገ። ቆይቶም የተወሰኑ መፅሀፍትን  እያዞረ መሸጥ ጀመረ።
ቀስ በቀስም ጥቂት መፅሀፍትን በዕጁ ይዞ በማዞር የጀመረዉን የመፅሀፍ ሽያጭ በጋሪ በማዞር በርከት ያሉ መፅሀፍትን ወደ መሸጥ ተሸጋገረ።የወጣቱን በእጅጉ መለወጥ የተመለከቱ ጓደኞቹና የቀድሞ የስራ ባልደረቦቹ በብሄራዊ ትያትር አንድ ምሽት በእሱ ስም የኪነ-ጥበብ መድረክ አዘጋጁለት።በዚህ መድረክ ላይ የወጣቱን ታሪክ የሰማዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በኩል አንድ ያገለገለ ሚኒባስ ተሽከርካሪ በስጦታ አበረከተለት።
ይህችን በስጦታ ያገኛትን መኪና ለቅንጦት ከማዋል ይልቅ ከመፅሀፍ ሽያጭ ባፈራዉ ገንዘብ የመፅሀፍት መደርደሪያ ሸልፍ በማስገጠም ወደ ተንቀሳቃሽ መፅሀፍ መሸጫነትና ቤተ-መፅሀፍትነት  ለዉጧታል።
እናም ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ ከተማ  ከጠዋት እስከ ማታ የአንባቢያንን ፍላጎት ለማሟላት ሲታትር ይዉላል።ከደንበኞቹ የሚያገኜዉ ምላሽም ስራዉን የበለጠ እንዲገፋበት ብርታት ሰጥቶታል። ወጣቱ ዉሎዉን ከመፃህፍት ጋር በማድረጉም በሁለት ነገር ተጠቅሚያለሁ ይላል።አንድም በኢኮኖሚ ራሱን ለመደጎም በሌላ በኩል ደግሞ ራሱን ከሱስ ለማፅዳት ረድቶታል።
ከምንም በላይ በሱስ ምክንያት ያጣቸዉን እንደሰዉ የመከበርን፣ ደስታን፣ ተስፋና ፍቅርን ከሚሸጣቸዉና ከሚያነባቸዉ መፅሀፍት እንዳገኜ ይናገራል።በዚህ የተነሳ ይህንን ተንቀሳቃሽ ቤተ-መፃህፍት የሱን የህይወት ዉጣዉረድ ለሌሎች ለማካፈልም ይጠቀምበታል።«የኔ ሽንፈትና ወድቆ መነሳት ለሌሎች መማሪያ መሆን አለበትም» ይላል።
ሌላዉ ሱስ አሳጥቶኝ ነበር ከሚለዉ ነገር አንዱ ለራስ ዋጋ አለመስጠት እንደነበረ የሚናገረዉ ወጣት አንዱዓለም፤ አሁን ግን ከራሱ አልፎ ስለ ሀገርና ስለ ትዉልድ ያስባል።መፅሀፍ ገዝተዉ ማንበብ ለማይችሉ ሰዎችም በትዉስት መልክ ይሰጣል።
ድሮ በጋሪ እየዞረ ከሚሸጠዉ ጋር ሲነፃፀር  የአሁኑ የመኪና ላይ መፅሀፍ ሽያጭ ወጭዉ ከፍተኛ ገቢዉ ደግሞ አነስተኛ መሆኑን ይናገራል።ያም ሆኖ በስራዉ ደስተኛ ነዉ።ለወደፊቱም  ይህንኑ  ስራ የበለጠ  ለማስፋፋት ዕቅድ አለዉ። የገንዘብና የቁሳቁስ እጥረት ግን አላላዉስ እንዳለዉ ይገልፃል። ስለሆነም  ይህንን ዕቅዱን በገንዘብም ይሁን በሀሳብ የሚደግፈዉ አካል  ቢያገኝ ደስተኛ መሆኑንም አጫዉቶናል።

Äthiopien Buchverkäufer aus Addis Abeba
ምስል Privat
Äthiopien Buchverkäufer aus Addis Abeba
ምስል Privat

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ