1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቢብሎኪ፤ልጆችን በጨዋታ የሚያስተምረው ኢትዮጵያዊ መተግበሪያ

ረቡዕ፣ ግንቦት 25 2013

ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዘርፎች ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ አስፈላጊ ክህሎት ነው። በዚህ የቴክኖሎጅ ዓለም ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከዚህ ክህሎት ጋር ማስተዋወቅ ወሳኝ መሆኑ ይነገራል።«ቢቤሎኪ» የተባለ ኢትዮጵያዊ ትምህርት ነክ መተግበሪያ ልጆችን በጨዋታ መልክ በማስተማር ለዚህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

https://p.dw.com/p/3uL4c
Nathan Damitew
ምስል Privat

«ቢብሎኪ»ልጆችን በጨዋታ የሚያስተምረው ኢትዮጵያዊ መተግበሪያ



ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት የዓለምን እድገትና እያንዳንዱን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚዘውር ሞተር ሆኗል።በዚህ የተነሳ  የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል። 
በዚህ  ለቴክኖሎጂ ጥገኛ በሆነ ዓለም ውስጥ  ታዲያ  የልጆች አስተዳደግና ትምህርትም ከዓመታት በፊት ከነበረው በዕጅጉ የተለዬ ሆኗል። ያ በመሆኑ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ፣ ታብሌቶች እና ዲጂታል ጨዋታዎች በልጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ  ውስጥ እየተካተቱ ነው።ስለሆነም ልጆች እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በሚጠቀሙ ጊዜ  ከእነዚህ ቴክኖሎጅዎች ጀርባ ያለውን አመክንዮ በመረዳት የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና  አዳዲስ ነገሮችን እንዲማሩ ማድረግም ወሳኝ ነው። 
ይህንን በመገንዘብ ይመስላል  «ቢብሎኪ»የተባለ ኢትዮጵያዊ መተግበሪያ ልጆችን በጨዋታ መልክ በማስተማር ዕውቀት እንዲጨብጡ በማበረታታት ላይ ይገኛል።ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በዚሁ መተግበሪያ ላይ ያተኩራል አብራችሁን ቆዩ።
«ቢብሎኪ»  ናታን ዳምጠው በተባለ ኢትዮጵያዊ ወጣት የተሰራ መተግበሪያ ሲሆን፤ ዓላማውም ልጆች  መሰረታዊ የኮምፒተር ፕሮግራም  ዕውቀት  እንዲኖራቸው ለማድረግ በጨዋታ መልክ ትምህርት መስጠት ነው።  መተግበሪያው «ኮድ» ወይም የመለያ ስም  አሰጣጥን ልጆች ሊገነዘቡት በሚችሉት ሁኔታ በቀላሉ ለመማር የሚረዳ ሲሆን፤ የመማር ሂደቱን ለልጆች አስደሳች እና  ሳቢ ለማድረግም ስዕላዊ  መግለጫዎችን ይጠቀማል። 
የ«ቢብሎኪ» መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ወጣት ናታን ዳምጠው  ይህንን መተግበሪያ  የሰራው የኮሚፒዩተር ሳይንስ የመጨረሻ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለ በ2010 ዓ/ም  ሲሆን፤ መነሻውም በዩንቨርሲቲ ቆይታው ያጋጠመው ችግር ነበር።
ይህ ትምህርት ነክ ቴክኖሎጅ ከ7 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ላላቸው ልጆች የተዘጋጀ ሲሆን ምንም አይነት የኮምፒዩተር እውቀት የማይጠይቅ በመሆኑ ለጀማሪ ልጆችም  ተስማሚ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  አፍሪቃዊ  መተግበሪያው እንደመሆኑ መጠን  የአህጉሪቱን ተግዳሮቶች በመረዳት  በተንቀሳቃሽ ስልክ ያለ በይነመረብ  ግንኙነት  የሚሰራም  ነው።

Nathan Damitew
ምስል Privat

መተግበሪያውን የበለጠ አሳታፊና  እና አስደሳች ለማድረግ  የጨዋታውን አጠቃላይ ሁኔታ ወደ እውነተኛው ዓለም ለማምጣት ገፀ ባህሪያትን ይጠቀማል።በዚህም ልጆች እንደ «ፐዝል»ያሉ  ምርምርና ብዙ ማሰብ የሚጠይቁ  ጨዋታቸውን ሲጫወቱ  የጨዋታውን እንቆቅልሽ ለመፍታት በሚጥሩበት ጊዜ   አዲስና የተሻለ የመማሪያ መንገድን መለማመድ ይችላሉ ፡፡ 
በመተግበሪያው ልጆች በቅደም ተከተል መስቀመጥን፣ ቀለበት መስራትን በመሳሰሉ ጨዋታዎች  መሰረታዊ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችን የሚማሩ ሲሆን፤ለዚህ የሚያግዙ 100 ፈታኝ ደረጃዎች አሉት። ልጆች እያንዳንዱን ደረጃ ሲጨርሱ እንደ አፈፃፀም ውጤታቸው  አዲስ «ብሎኪ»ዎች ለመግዛት የሚጠቀሙት ምዕናባዊ ሳንቲሞችን ይሸለማሉ። ብሎኪዎች የጨዋታው ገፀ-ባህሪያት ሲሆኑ  ትልልቅ ጭንቅላትና  ዓይኖች እንዲሁም ያልተመጣጠነ ትናንሽ አካላት ያላቸው የጨዋታ ገፀ-ባህሪያት ናቸው። የእነዚህ አሻንጉሊት መሰል  ገፀ-ባህሪያት ቅርፅ  ጨዋታውን ለልጆች አስደሳች ያደርገዋል።ከዚህ በተጨማሪ ገፀ ባህሪያቱ በቀለምም ሆነ በአለባበስ ራሳቸው ልጆቹን የሚመስሉና  እንዲሁም ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የሚያውቋቸው በመሆናቸው ለልጆቹ እንግዳ አይደሉም። 
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ አድዋን የሚመለከቱ ገፀባህሪያትን ማካተታቸውን የሚናገረው ናታን፤ ይህንን ማድረግ የፈለጉበት ዋናዉ ምክንያትም  አብዛኛዎቹ ዲጅታል የልጆች ጨዋታዎች  ከአፍሪቃዉያን  ነባራዊ ሁኔታ  ጋር ብዙም ቀረቤታ የሌላቸውና አካባቢውን የማይመስሉ በመሆናቸው ያንን ክፍተት ለመሙላት ነው።

Nathan Damitew
ምስል Privat

ናታን እንደሚለው «ቢብሎኪ»በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ መተግበሪያ ሲሆን በቅርቡም የተሻሉ ፅንሰ-ሀሳቦችንና ተጨማሪ ተግባራትን ያካተተ «ቢብሎኪ 4.0» በሚል መጠሪያ መተግበሪያውን አሻሽሏል። በዚህም የውስጠ-መተግበሪያ መማሪያ ፣ የወላጅ ቁጥጥር እና ሌሎች ማሻሻያዎች ተደርገውበታል።
 መተግበሪያው በአሁኑ ጊዜ  Google Play ላይ  በነፃ የሚጫን ሲሆን ፤እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ  ከ17,000  በላይ  የሆኑ ሰዎች እየተጠቀሙበት መሆኑን ናታን ገልጿል፡፡በሚቀጥሉት ከ5 እስከ 10 ባሉት ዓመታት ደግሞ ለ50 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች «ቢብሎኪ»ን ተደራሽ ለማድረግና በተለይም ለአፍሪካቃውያን መሠረታዊ የኮምፒዩተር ፕሮግራም ችሎታዎችን የማስጨበጥ ዕቅድ አለው። ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግም መተግበሪያው የተለያዩ የአፍሪቃ ቋንቋዎችንና ታዋቂ አፍሪቃዉያንን በገፀ ባህሪነት  እንደሚያካትት ይናገራል።
ልጆች በወደፊት ህይወታቸው  በየትኛውም  የሙያ መስክ  ቢሰማሩ አዳዲስ ነገሮችን  ፈጣሪዎች እንዲሆኑ የዲጂታል  ክህሎት በጣም አስፈላጊ ነው።ይሁን እንጅ ድሃ ሀገራት ከዚህ በጣም የራቁ ናቸው።በመሆኑም የዲጂታል ዕውቀት የእኩልነት ጥያቄ በመሆኑ የቴክኖሎጅ  ዕውቀትን መቅሰም  ዕድለኛ እና ልዩ መብት ላላቸው ጥቂት ልጆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም መዳረስ እንዳለበት አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያች ይከራከራሉ ። በዚህ ረገድ «ቢብሎኪን» የመሳሰሉ ሀገር በቀልና አካባቢያቸውን ችግር የተገነዘቡ  የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች  የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ