1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ቀዉስና የመፍትሔ ፈላጊዉቹ ዉዝግብ

ሰኞ፣ ነሐሴ 20 2011

ሰባቱ መሪዎች የሚወክሏቸዉ ሐገራት ከዓለም ሐብት 60 ከመቶ ያሕሉን ይቆጣጠራሉ።317 ትሪሊዮን ዶላር።ከሰባቱ ሐገራት ሶስቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ናቸዉ።ፈረንሳይ፤ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ።እስካሁን ድረስ ከሰባቱ ሐገራት አራቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባላት ናቸዉ።ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ኢጣሊያና ብሪታንያ።

https://p.dw.com/p/3OWCF
G7-Gipfel in Frankreich
ምስል Reuters/C. Barria

ማኅደረ ዜና፦ቡድን 7 ወይስ ቡድን 6 +1

የዘንድሮዉ የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ አስተናጋጅ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ሰባታችን ከተስማማን አብዛኛዉን የዓለም ችግሮች ማቃለል አይገደንም አሉ።ሰባቱ መሪዎች ካንድ አዳራሽ የገቡት ግን ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ጦርነት ለመግጠም እንደተዛዛቱ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የዓየር ንብረት ለዉጥ ስምምነትን፣ የኢራን የኑክሌር ስምምነት ሕግን፣የዓለም ንግድ ዉልን በማፈራረሷ ምክንያት ከስድስቱ ወዳጆችዋ ጋር እንደተቃቃረች ነዉ።ጃፓን በኮሪያ ልሳነ-ምድር ቀዉስ ሰበብ አዩናይትድ ስቴትስ ላይ ያላትን ቅሬታ እንዳመቀች ነዉ።የብሪታንያና የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ሆድና ጀርባ ናቸዉ።በዚሕ መሐል ሰባቱ መሪዎች እንደ ጥሩ ወዳጅ እየተሞጋገሱ፣ ፈገግታ እየተለዋወጡ አንድ አዳራሽ ተሰበሰቡ።ዛሬ ይለያያሉ።የመሪዎቹን ጉባኤ አስታከን የዓለም ችግር ፈጣሪ-መፍትሄ ሰጪዉን ማንነት ላፍታ እንጠይቃለን።ብራችሁን ቆዩ።

የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በዚሕ ክፉ ቀን የልብ ወዳጅ የትገኛል ዓይነት አሉ -የካናዳዉን ጠቅላይ ሚንስትር ሲያነጋግሩ ትናንት።«በሁከት በምትናጠዉ ዓለም መሐል እንደ ጀርመንና ካናዳ  ያለ ወዳጅነት ሲገኝ በከፍተኛ ደረጃ ሊመሰገን ይገባል።ብዙ ግጭቶች ባሉባት በዚች ዓለም ሁለቱ ሐገሮቻችን (የሚቀራርቡ) በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ አይን ለአይን ልንተያይባቸዉ የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች አሉ-----»

ሊቢያ ፈርሳለች።ሶሪያ ወድማለች።የመን ትነፍራለች።አፍቃኒስታን ትተራመሳለች። ከዩክሬን እስከ ሕንድ-ፓኪስታን ድንበር፣ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ፋርስ ባሕለ ሰላጤ፣ከሩሲያ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ በወታደራዊ ፍጥጫ፣ ዛቻ፣ ፉከራ ይታመሳሉ።ከቬኑዜዌላ እስከ ሆንግኮንግ በፖለቲካ ቀዉስ ይተራመሳሉ።

G7-Gipfel in Frankreich
ምስል Getty Images/AFP/P. Wojazer

ዓለም በርግጥ በቀዉስ ተዘፍቃለች።

የዘንድሮዉን የቡድን 7 ጉባኤን ያስተናገዱት የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ዓለምን የሚያብጠዉን ቀዉስ ሰበብ ምክንያት በርግጥ አላጡትም።የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ሲቀበሉ እንዳሉት ግን ሰባቱ ከተስማሙ ቀዉሱን ማስወገዱ አይገዳቸዉም።

«በሊቢያ፣በሶሪያ፣በዩክሬይን፣በሰሜን ኮሪያና በኢራን ጉዳይ ላይ እንወያያለን።ከነዚሕ ቀዉሶች አብዛኞቹ ለመፍታት ጠንካራ ትብብር ያሻል።በተለይ የኢራን ጉዳይ መፍትሔ መስጠት አለብን።ብዙ ግንኙነት አድርገናል።ጠንክረን መስራት አለብን፣ ምክንያቱም ኢራን የኑክሌር ቦምብ መታጠቅ የለባትም በሚለዉ ሐሳብ የጋራ አቋም ነዉ ያለን።አካባቢዉ መረጋጋት እንዳለበትም ሁላችንም እናምናለን።ስለዓለም ምጣኔ ሐብትና ዓለም አቀፍ ሁኔታም በሰፊዉ እንወያያለን።እንደሚመስለኝ እኛ ሰባታችን ሁኔታዎችን ማስተካከል ከቻልን፣ የአብዛኛዉን ዓለም ችግር ማቃለል እንችላለን።»

ሰባቱ መሪዎች የሚወክሏቸዉ ሐገራት ከዓለም ሐብት 60 ከመቶ ያሕሉን ይቆጣጠራሉ።317 ትሪሊዮን ዶላር።ከሰባቱ ሐገራት ሶስቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ናቸዉ።ፈረንሳይ፤ ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ።እስካሁን ድረስ ከሰባቱ ሐገራት አራቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባላት ናቸዉ።ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ኢጣሊያና ብሪታንያ።

G7-Gipfel in Frankreich Kabore, Macron und Merkel
ምስል Getty Images/AFP/I. Langsdon

የእነዚሕ ሐገራት መሪዎች የዓለምን ችግር ለማቃለል አቅሙም፣ በዓለም አቀፉ ማሕበር የተሰጠ ኃላፊነትም አለባቸዉ።አቅም፣ኃላፊነታቸዉን ለመወጣት ግን ማክሮ እንዳሉት የጋራ ፍላጎትና አቋም መያዝ ግድ አለባቸዉ።

ግን አልያዙም።በተለይ አክራሪዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስን የመሪነት ስልጣን ከያዙ ወዲሕ ሰባቱ ሐገራት የጋራ አቋም መያዝ አይደለም የጋራ አቋም የያዙበትን፣በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያፀደቋቸዉን ስምምነቶች፤ ሕግና ዉሎች ማፍረሳቸዉ የዓለምን ቀዉስ የሚያወገዱ ሳይሆኑ ቀዉሱን የሚያባብሱ መሆናቸዉን እያስመሰከሩ ነዉ።

ትራምፕ አሽቀንጥረዉ ከጣሉት ዓለም አቀፍ ስምምነት አንዱ፣ ሜርክል በጥቅሉ፣ ማክሮ በዝርዝር የጠቀሱት የኢራን ጉዳይ የዘንድሮዉ ጉባኤ «ያልተጠበቀ» የተባለ ክስተት ነበር።የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ መጋበዛቸዉ በይፋ ሳይነገር በጉባኤዉ መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል።የዛሪፍ በጉባኤዉ መገኘት አዉሮጶች የዋሽግተን ቀኝ አክራሪ መሪዎችን አቋም የማለሳለሳቸዉ፣ የማግባባታቸዉ ወይም በግልፅ የመፃረራቸዉ ምልክት ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።

ጉብኝቱ የቴሕራን አክራሪ ፖለቲከኞችን ማስቆጣቱም አልቀረ።ለመገናኛ ዘዴዎችም «ያልተጠበቀ» ወይም «አስደናቂ» ከሚል ቅድመ ቅፅል ጋር ትልቅ ርዕስ ሆኗል።የፕሬዝደንት ትራምፕን የተናጥል እርምጃ ለማስቆም እና ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ ለማስገደድ ወይም ለማግባባት ግን በርግጥ የተከረዉ ነገር የለም።ዛሬፍ ራሳቸዉ እንደፃፉትም «መሞከሩ አይከፋም» ከማሰኘት በላይ የወደፊቱን ጉዞ ከባድነት አይለዉጠዉም።

ፍጥጫ፣ ቀዉሱ ይቀጥላል።

ክራይስስ ግሩፕ የተሰኘዉ አጥኚ ተቋም የፖለቲካ ተንታንታኝ ሮበርት ማሌይ እንደሚሉት ቡድን 7 በኢራንም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ወጥ አቋም እንዳይዝ ትልቁ እንቅፋት የአሜሪካዉ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ናቸዉ።ትራምፕ ከአፍራሽነታቸዉ በላይ ዛሬ ያሉና ያደረጉትን ነገ የማይደግሙት መሆናቸዉ ደግሞ የፖለቲካ አዋቂዉ እንደሚሉት ለየችግሮቹ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ይበልጥ  እንዲባባስ  እያደረጉ ነዉ።

ሰዉዬዉ ለዘንድሮዉ ጉባኤ ወደ ቢያሬትስ ከመጓዛቸዉ በፊት እንኳ አስተናጋጆቻቸዉ ላይ ዝተዉ ነበር።

 «ፈረንሳይ በኩባንዮቻችን ላይ ቀረጥ ጥላለች።ይህን ታዉቃላችሁ? ስሕተት ነዉ።ይሕን ማድረግ አልነበረባቸዉም።ከፈረንሳይ ዋይን ይልቅ የአሜሪካንን ዋይን አመርጣለሁ።ዋይን ባልጠጣም።የኛን ኩባንዮች የምንቀርጠዉ እኛ ነን።እነሱ አይደሉም።ፈረንሳዮች አሁን ቀረጥ ጥለዋል።ተዉ! ብያቸዉ ነበር።እናንተ ቀረጥ ከጣላችሁ እኔም በናንተ ዋይን ላይ ቀረጥ እጥላለሁ ብያቸዉ ነበር።ስለዚሕ ቀረጡን ለመጣል ተዘጋጅተናል።»

ፕሬዝደንት ማክሮ፣ የሚመሩት ጉባኤ ከሊቢያ እስከ ዩክሬን ያለዉን ቀዉስ ለመፍታት ይጥራል ማለታቸዉ ከዲፕሎማሲ ሽርደዳነት ባለፍ ፍሬ እንደሌለዉ አላጡትም።ትራምፕ ግን የፖለቲካ ተንታኝ ማሌይ እንዳሉት ከዋሽግተን ከመነሳታቸዉ በፊት ያሉትን ተቃራኒ እንጂ ቢያሬትስ ሲገቡ አልደገሙትም።

«አመሰግናለሁ ኢማኑኤል።በጣም ጥሩ ነዉ።-----ኢማንኤል ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሉን።የረጅም ጊዜ ወዳጆችም ነን።»

ቡድን ሰባት።የቀድሞዉ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ቫለሪ ጄስካርድ ደስታንግ በ1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሲጠነስሱት ያኔ ምዕራቡን ዓለም ያርበደበደዉን የአረቦች የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ማዕቀብን የሚቋቋሙበትን ስልት በጋራ ለመፈለግ ነበር።እስከ 1975 ድረስ 6 የነበሩት ሐገራት ወዲያዉ ሰባት ሆነ።

ከ1990ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ እስከ 2014 ድረስ ሩሲያን ጨምሮ አንድ ጊዜ ቡድን 7 ሲደመር አንድ፣ ሌላ ጊዜ ቡድን 8 ሲባል ነበር።ከ2015 በኋላ ሩሲያን ቀንሶ ቡድን 7 በሚል መጠሪያዉ ፀጥንቷል።ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ መሪ እስከሆኑበት እስከ 2017 ድረስ፣ አባላቱ ስድስትም፣ ሰባትም፣ ሆኑ ስምት፣ወይም መልሰዉ ሰባት፣ ለዓለም ሠላም ጠቀመም ጎዳ፣ «ዓለም አቀፍ» በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ያልያዙበት ጊዜ አልነበረም።

BG G7 Ehefrauen Programm
ምስል Getty Images/AFP/R. Duvignau

ትራምፕ ቡድኑን ከቀየጡ ወዲሕ ግን ቡድኑ የጋራ አቋም ኖሮት አያዉቅም።በለንደኑ ስኩል ኦፍ ኤኮኖሚክስ የዓለም አቀፍ  ግንኙነት አጥኚ ትሪስተን ኔይለር እንደሚሉት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ሆነ ዘንድሮ ስብሰቡ ከ7ነት ይልቅ 6 ሲደመር 1ነቱ የጎላ ነዉ።

«በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ በአየር ንብረት ለዉጥ፣በዓለም አቀፍ ንግር፣ በኢራን ጉዳይ በሰባቱ ኃያላን መካከል አንድነት የለም።አሁን ያለዉ ቡድን 6 ሲደመር አንድ የሚባል ዓይነት ነዉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ በተሳተፉባቸዉ ባለፉት ሁለት ጉባኤዎች ያየነዉ ይሕንን ነዉ።ባሁኑ ጉባኤም የሚቀየር ነገር አይኖርም።»

ጉባኤዉ ዛሬ ስለአየር ንብረት ለዉጥ ባደረገዉ ዉይይት ላይ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አልተከፋሉም።የተቀሩት ስድስቱ በተለይ የብራዚሉን የአማዞን ጫካ የሚያጋየዉ ሰደድ እሳት በዓለም የዓየር ንብረት ላይ የሚያሳድረዉን ጫና ለማቃለል ስለሚወስዱት እርምጃ ተነጋግረዋል።የትራምፕ ወንበር ግን ባዶ ነበር።

የጉባኤዉ ሰብሳቢ ኢማኑኤል ማክሮ ትራምፕ ባይኖሩም «ረዳቶቻቸዉ ተገኝተዋል» አሉ፣ አሉ ለተቀሩት ጉባኤተኞች።የሚሉት ቢጨንቃቸዉ።ማክሮ ትራምፕን ከማስታተመም በተጨማሪ የብራዚሉ ፕሬዝደንት ያየር ቦልሶናሮ ከብራዚሊያ ለሚተኩሱት የቃላት ጥያት፣ አፀፋ ተኩስ መስጠት ነበረባቸዉ።

አፍቃሬ ትራምፑ ቦልሶናሮ የአማዞን ጫካን በሚያጋየዉ ቃጠሎ ሰበብ የተሰነዘረባቸዉን ትችት መቋቋም ቢያቅታቸዉ የማክሮንን ባለቤት በፌስቡክ ማንጓጠጥ ይዘዋል።የብራዚሉ መሪ የ66 ዓመቷን የማክሮ ባለቤትን መልክ ከ37ት አመቷ የራሳቸዉ ባለቤት ጋር እያነፃፀሩ «ሰዉዬዉን አታዋርዱት-----» እያሉ በፈረንሳይ መሪ ላይ ተሳልቀዋል።ፌስ ቡክ የሚሉት የጤና አያናግር ይሆን? ብቻ ማክሮ የብራዚሉ አቻቸዉን ስድብ «አሳዛኝ» አሉት።«መጀመሪያ ለራሱ ለሰዉዬዉ፣ ቀጥሎ ለብራዚል፣ ሲያሰልስ ለብራዚል ሴቶች---በእንዲሕ ዓይነት ሰዉ ለሚመሩት።» አከሉ የፈረንሳይ መሪ።

G7-Gipfel in Frankreich Jawad Zarif
ምስል Reuters/R. Duvignau

ጉባኤተኞች ከዚሕ ቀደም እንደነበረዉ ሁሉ በተቃዉሞ ሰልፈኞች እንደተከበቡ ተሰብስበዉ፣ ተጀምሮ፣ በተቃዉሞ ሰልፈኞች እንደተወገዙ ማምሻዉን ይበተናሉ።ባለፉት ሁለት ጉባኤዎች እንደተደረገዉ ሁሉ ጉባኤተኞች የጋራ አቋም ስለሌላቸዉ «የሊቀመንበሩ መግለጫ» ከሚባል በስተቀር የጋራ የአቋም መግለጫ አይኖራቸዉም።ቢያሬትሶች «መጡ-ሔዱ» ይሉ ይሆናል።ነገ።

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋዓለም ወልደየስ